ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የቻምፒዮኖቹ ያለመሸነፍ ጉዞ በተገታበት እንዲሁም ለሁለተኝነት እና ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር በርትቶ በቀጠለበት 24ኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ነክ የትኩረት ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው። 

👉 የዐፄዎቹ ያለመሸነፍ ጉዞ መገታት

በ2ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ፋሲል ከነማዎች ከ45 ያላነሱ ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር በተጫወተው ኢትዮጵያ ቡና 3-1 የተረቱበት ጨዋታ በስተመጨረሻም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ለበቃው ቡድን ብዙ ነገሮችን የለወጠች የመጀመሪያዋ የማንቂያ ደውል ነበረች። ቡድኑ ከጥቂት ጨዋታ ሳምንታት በኋላ በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት እንዲሁም ለሁለት አጋማሾች የቀረበ ጊዜን በጎዶሎ ከተጫወተው ባህር ዳር ከተማ ጋር በመጨረሻ ደቂቃ ነጥብ ተጋርተው የወጡበት ጨዋታ እንዲሁ ከጨዋታዎቹ መጠናቀቅ በኃላ በተጫዋቾቹ ሆነ በአሰልጣኝ  ሥዩም ከበደ ላይ ያነጣጠሩ ከፍተኛ ተቃውሞዎች የተስተናገዱበት ነበር።                                              

ፋሲል ከነማ በ2ኛው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረታ ወዲህ ባደረጋቸው አስራ ዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ማለትም በአራቱ ጨዋታ ብቻ አቻ ወጥቶ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ድል በማድረግ ያስመዘገበው አስደናቂ ክብረወሰን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በደረሰባቸው ሽንፈት ሊገታ ችሏል። በድሬዳዋ ከተማ 3-1 አሸናፊነት በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታም ፋሲል የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ሽንፈት አስተናግዷል።
ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ በ2000 የሚድሮክ ሚሌኒየም ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወቅቱ 24 ጨዋታዎችን አድርጎ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ ያጠናቀቀበት እንዲሁም በ1991 የውድድር ዘመን እንዲሁ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን ሲያሸንፍ 18 ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈትን ካስተናገደበት አስደናቂ ግስጋሴ ቀጥሎ የፋሲል ከተማ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ተሸንፎ ሊጉን የሚጨርስ ከሆነ ሦስተኛው የሊጉ የአሸናፊነት ጉዞ ሆኖ በታሪክ ማኅደር የሚሰፍር ይሆናል። ያም ቢሆን ቡድኑ ከዚህም በላይ ያለመሸነፍ ጉዞውን በማርዘም አስደናቂ ታሪኮችን ለመስራት ዕድሉ እንደነበረው የብዙዎች እምነት መሆኑ ሽንፈቱን የኋላ ኋላ አስቆጪ የሚያደርገው ይመስላል።

ቡድኖች ውድድሮች ሳይቋጩ አሸናፊነታቸውን ማወጅ ሲችሉ ቀጣይ ፉክክራቸው ከሪከርዶች ጋር ሲሆን የመታየቱ ዕውነታ በፋሲል ዘንድ ትኩረት የተደረገበት አይመስልም። ፋሲል እስካሁን ከመጣበት መንገድ አንፃር ከዚህ በላይ ሪከርዶችን የማሻሻል እና ቁጥሮችን ከፍ አድርጎ የመስቀል ብቃት እንዳለው ፍንጮችን ሲሰጥ ቆይቷል። ከሁሉም በላይ በየጨዋታዎቹ ላይ ስብስቡ ያሳይ የነበረው ጉጉት እና ተነሳሽነት ለስኬቱ ዋነኛ ሚስጥር መሆኑን መናገር ይቻላል። ነገር ግን በድሬዳዋው ጨዋታ መጀመሪያ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርግም የቀደመ የሜዳ ላይ ትኩረቱ እየወረደ መጥቶ ግለሰባዊ ስህተቶች ጎልተው የቡድኑ ግብረ መልስም ተቀዛቅዞ ለሽንፈት መዳረጉ አስገራሚ ነበር። 

ይህ ከሽንፈቱ ባሻገር ሜዳ ላይ የነበረው መቀዛቀዝ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ከድሬዳዋ ጋር ተፎካካሪ በነበረው ወልቂጤ ከተማ ቅሬታ እንዲነሳበት ያደረገ ሆኗል። በዚህም ከክለቡ እና የደቡብ ክልል የእግርኳስ ፌዴሬሽን ይፋዊ የክስ ደብዳቤ የወጣ ሲሆን ፋሲል ከነማ ደግሞ በአሰልጣኙ ሥዩም ከበደ በኩል ትናንት በነበረው መግለጫ ላይ ክሱ መሰረተ ቢስ መሆኑና ቻምፒዮንነትን ካረጋገጡ በኋላ ሽንፈት ማስተናገድ በእግርኳስ አዲስ ነገር አለመሆኑን ሲነገሩ ተደምጧል።

👉 ማሸነፍ እንደተሳነው የቀጠለው ኢትዮጵያ ቡና 

በሊጉ የሁለተኛ ደረጃን ይዞዞ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ፉክክር የተሻለ ዕድል የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ከረታበት ጨዋታ በኃላ በነበሩት የጨዋታ ሳምንታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ተሸንፎ በተቀሩት ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ከተከታዮቹ ሰሞነኛ ተደጋጋሚ ነጥብ መጣል ጋር ተዳምሮ ልዩነቱን ሊያሰፋበት የሚችለውን አጋጢ አምክኖ ከ24ኛ የጨዋታ ሳምንት በኋላም በ38 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

አሰልጣኝ ካሣዬ ቡድናቸው በተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አለመቻሉን ተከትሎ ሀሳባቸውን ሲሰጡ እንደሚደመጡት ተጫዋቾቹ በተጠጋጋ የነጥብ ልዩነት ውስጥ ለሁለተኝነት እየተፎካከሩ መገኘታቸው ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው እና ይህም በተለይ በሜዳ ላይ ክፍት ቦታዎችን እና ሰዎችን ለማግኘት በሚያደርጉት ሂደት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ያነሳሉ። በእርግጥ በንፅፅር በፕሪምየር ሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች በትልቅ ደረጃ ብዙም መጫወት በሌላቸው ተጫዋቾች የተገነባው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ከተወሰኑት ተጫዋቾች ውጭ በዚህ ደረጃ ተፎካካሪ በነበሩ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አለማሳለፋቸው ይህ የፉክክር ሒደት የሚፈልገውን ጠንካራ የአዕምሮ ዝግጁነት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው ቡድኑ ፉክክር በጦዘበት በዚህ ወቅት በተወሰነ መልኩ እንዲቀዛቀዝ ስለማስቻሉ በግልፅ መናገር ያስችላል።

ይህም ተጫዋቹ ላይ ያሳደረው ከፍተኛ ጫና በጨዋታ ወቅት በተጫዋቹ ላይ ይነበባል። የቡድኑ የሜዳ ላይ ተጫዋቾችም ሆኑ በተጠባባቂነት የሚቀመጡት የቡድኑ አባላት በተደጋጋሚ የዳኞች ውሳኔዎችን በመቃወም የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪም የዚህ ጫና አንዱ መገለጫ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።

የኢትዮጵያ ቡና ችግር ግን ከዚህም ያልፋል። በተለይ ቡድኑ ከሚጠቀምባቸው አስራ አንድ ተጫዋቾች በተጨማሪ ከተቀያሪ እየተሱ የቡድኑን ውጤት መወሰን የሚችሉ ተጫዋቾች እጥረት ሌላኛው ጉዳዩ ሲሆን በጨዋታ መንገዳቸው ሳይለቁ አማራጭ የኳስ ምስረታ እንዲሁም የማጥቂያ ብሎም የመከላከያ መንገዶች አለመኖራቸው እንዲሁ ሌላው የቡድኑ መሠረታዊ ክፍተቶች መሆናቸውን እየተመለከትን እንገኛለን። አሁንም ቢሆን ይህን ፉክክር በራሳቸው ውጤት ላይ ተመስርተው መወሰን የሚችሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣይ ከሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ጋር ባሏቸው ሁለት ጨዋታዎች ነጥቦችን አስመዝግበው ከ2004 በኋላ ዳግም በአፍሪካ ውድድሮች ራሳቸውን የማሳተፍ ዕድሉ አላቸው።

👉 የባህር ዳር ከተማ የአፍሪካ መድረክ ተስፋ መምከን

በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት በአፍሪካ መድረክ የመሳተፍ ህልም የነበረው ባህርዳር ከተማ ከጅማ አባጅፋር ጋር ያደረገውን ጨዋታ ያለ ግብ በማጠናቀቁ የተነሳ ይህ ህልሙ መሉ ለሙሉ ከሽፏል።  ለሁለተኝነት እየተፎካከሩ ከሚገኙ ቡድኖች ቀደምው 23 ጨዋታዎችን የከወኑት ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸው 33 ላይ ይገኛል። ይህም በቀራቸው አንድ ጨዋታ እንኳን ድል ቢያደርጉ በአጠቃላይ የሰበሰቡትን ነጥብ ብዛት 36 ቢያደርሱም በዚህ ሳምንት አንድ ነጥብ ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ከወዲሁ 37 በመሆኑ የጣና ሞገዶቹ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ህልም ሳይሳካ ቀርቷል።

ጥሩ እምርታን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያሳዩት ባህር ዳር ከተማዎች እንደ አብዛኛዎቹ የሊጉ ቡድኖች ወጥ እንቅስቃሴን ከጨዋታ ጨዋታ ለማሳየት ተቸግረዋው ቢቆዩም በተለይ በመጨረሻ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ምንም ማሸነፍ አለመቻላቸው ቡድኑ በወሳኙ የውድድር ዘመን ክፍል ላይ ወገቤን ስለማለታቸው ማሳያ ነው። በእነዚሁ ጨዋታዎች በተለይ ዘንድሮ ጠንከራ የነበረበው በመናፍ ዐወል እና ሰለሞን ወዴሳ የሚመራው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላላ ብሎ መታየቱ ቡድኑ በቀላሉ ግቦችን እንዲያስተናግድ አስገድዶታል። በፍፁም ዓለሙ ላይ የተንጠለጠለው የጎል ማስቆጠር እና እድሎችን የመፍጠር ሒደት በሌሎች ተጫዋቾች አለመታጀቡም ተጋጣሚዎች አማካዩን በመቆጣጠር በቀላሉ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲገቱ ታይተዋል። 

በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ መሉ የውድድር ዘመኑን እያገባደደ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ ከአንድ ውድድር ዓመት ወደ ሌላው ፈጣን የሚባልን እምርታ እያሳየ የሚገኝ ቡድን እንደሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በግልፅ ያሳያል። በመሆኑም ቡድኑ በቀጣይ የውድድር ዘመን በተወሰነ መልኩ ራሱን አሻሽሎ የሚቀርብ ከሆነ የአፍሪካ ተሳትፎን የማረጋገጥ ህልሙ እውን የሚሆን ይመስላል።

👉 የ “አዲሱ ሀዲያ ሆሳዕና” ድል  

ከሰሞነኛው ትርምስ አንፃር በተወሰነ መልኩ የተረጋጋ የሚመስሉ ጥቂት ቀናትን ያሳለፉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የጊዜያዊ መፍትሔ አካል ለሆኑት ተስፈኛ ታዳጊዎች ከፍተኛ የሞራል መነሳሳት የሚፈጥርን ድል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ አስመዝግበዋል። 

ከ20 ዓመት በታች ካደጉት ተጫዋቾች መካከል አራቱን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ባስጀመሩበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አምበሉ ሄኖክ አርፊጮን ጨምሮ በቀደሙት ጊዜያት በቋሚነት ከሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች በድምሩ ሦስት ያህሉን በአሁኑ ወቅት እየተጠቀሙ መገኘታቸው ቡድኑ ለአዲስ ቡድን በቀረበ መልኩ ስለመለወጡ ግልፅ ማሳያ ነው።

በጨዋታው ከዚህ ቀደም አሰልጣኙ ሲሉም እንደተደመጠው ቡድኑ አዲስ እንደመሆኑ በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ላይ ጠቅጠቅ ብለው መከላከል በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህም ውጤታማ አድርጓቸዋል። በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ አምበላቸው ሄኖክ አርፊጮ መሪ ያደረገቻቸውን ግብ ማስቆጠር መቻሉ ቡድኑ በተቀሩት ደቂቃዎች ያገኛትን ግብ ለማስጠበቅ በጥሩ መንገድ ተከላክሎ በመውጣት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። 

ቡድኑ በቅርቡ በርከት ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን እንደማሳደጉ በተጫዋቾቹ ላይ የሚታየው እጅግ ከፍ ያለ የመጫወት ፍላጎት እና ተነሳሽነት በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በግልፅ የታየ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሁሉም የቡድኑ ተሰላፊዎች በመከላከሉ ወቅት የነበራቸው አበርክቶ እጅግ ድንቅ ነበር። 

ሆሳዕናዎች ለሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር በ35 ነጥቦች ከኢትዮጵያ ቡና በሁለት ነጥብ አንሰው ሲገኙ በቀጣዩ 25ኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ እንደመገናኘታቸው ጨዋታው ለሁለተኝነት በሚደረገውን ፉክክር የሚወስን ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

👉 ድምፁን አጥፍቶ የተሻሻለው ሰበታ ከተማ 

በመጀመሪያው ዙር እጅግ አስቸጋሪ ጊዜያትን ያሳለፉት ሰበታ ከተማዎች ቀስ በቀስ ግን መሻሻሎችን በማሳየት በአሁኑ ወቅት በ33 ነጥቦች በስድስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል። ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አዳማ ከተማን መርታት ችሏል። በዚህ የማንሰራራት ጉዞ ላይ በተለይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የፈፀማቸው ዝውውሮች ተፅዕኖ በቀላል የሚታይ አይደለም። በዝውውር መስኮቱ ባመጣቸው ተጫዋቾች እንደ ሰበታ ከተማ የተጠቀመ ቡድን አለ ብሎ መናገርም ይከብዳል። 

በአስቸጋሪው የመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ጉዞ ላይ በጉልህ ክፍተቶች በተስተዋሉባቸው የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ያዘዋወሯቸው ተጫዋቾች ቡድኑን በሚገባ አሻሽለውታል ብሎ መናገር ይቻላል። የማጥቃት ሂደታቸውን ለማሻሻል ጋናዊውን ኦሲ ማውሊን እንዲሁም የመከላከል ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ሁነኛ የተከላካይ አማካይ ያልነበረው ቡድኑ ዩጋንዳዊውን ክሪዚስቶም ንታምቢን ወደ ቡድኑ የቀላቀለባቸው ዝውውሮች ከቡድኑ መሻሻል በስተጀርባ በጎልህ የሚጠቀሱ ዝውውሮች ነበሩ።

ጥንቃቄ የተሞላባቸው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዝውውሮች በቡድኖች የሁለተኛ ዙር እንቅስቃሴ ላይ ስለሚፈጥሩት በጎ ተፅዕኖ የሰበታ ከተማ አካሄድ ለሌሎች ቡድኖች በምሳሌነት መቅረብ የሚችል ነው። ሰበታ ስለመሻሻል ሲነሳ ብዙ የተነገረለትን ወላይታ ድቻን ሁሉ በልጦ በሰንጠረዡ የያዘው ቦታ አድናቆት የሚገባው እምርታ ነው። ቡድኑ ቀደም ብሎ ጥቂት ነጥቦች ቢሰበስብ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ማግኘት የሚችልበት ዕድልም ከፍ ይል ነበር።