በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ መውረዱን ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ሀዋሳን አሸኝፏል።
አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ላሚን ኩማራ (ቅጣት) ፣ ትዕግስቱ አበራ፣ አሊሲ ጆናታን፣ ኤልያስ ማሞ፣ ሰይፈ ዛኪር እና በላይ ዓባይነህን አሳርፎ ጀሚል ያዕቆብ ፣ ደስታ ጊቻሞ፣ አሚን ነስሩ ፣ ደሳለኝ ደባሽ ፣ ሀብታሙ ወልዴ እና ኤልያስ አህመድን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካቷል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ሆሳዕናን ከረታው ቡድኑ ውስጥ በቸርነት አወሽ ፣ ዳዊት ታደሰ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ምትክ ተባረክ ሄፋሞ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና አለልኝ አዘነን ተጠቅሞ ጨዋታውን ጀምሯል።
ጨዋታው ከመጀመሩ ሀዋሳ ከተማ ከርቀት ቅጣት ምት ከተነሳ ኳስ በኤፍሬም አሻሞ እና አለልኝ አዘነ በተከታታይ ያደረጋቸው ሙከራዎች በግቡ ቋሚ እና አግዳሚ ተመልሶበታል። የሜዳ ላይ ግጭቶች በርከት ብለውበት በቀጠለው ጨዋታ ሀዋሳዎች ከመስመር በሚነሱ ተሻጋሪ ካሶች አዳማ ከተማዎች ደግሞ ለመልሶ ማጥቃት በቀረበ አጨዋወት ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። ነገር ግን ወንድምአገኝ ኃይሉ ከመስመር የመጡለትን ሁለት ኳሶች ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት በአዳማ በኩል አልፎ አልፎ አብዲሳ ጀማልን ያማካሉ ኳሶች ወደ ፊት ይላኩ ነበር።
ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን አብዲሳ ጀማል የበቃሉ ገነነን ወደ ቀኝ ያደላ ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማግባት አዳማ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ በኋላ አዳማዎች በእንቅስቃሴ ተረጋግተው ኳስ መስርቶ ለመውጣት ጥረት ማድረግ ቢጀምሩም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግብ አስተናግደዋል።
ሚሊዮን ሰለሞን ወንድምአገኝ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት መስፍን ታፈሰ በ36ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ነው ሀዋሳን አቻ ያደረገው። ቡድኖች ከዕረፍት በፊት ተጨማሪ የማጥቃት አጋጣሚዎችን ከፈጠሩባቸው ሌሎች ቅፅበቶች ውስጥ አዳማዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በሰነዘሩት ጥቃት ግብ አፋፍ ደርሰው ወደ ሙከራነት ያልቀየሩት ኳስ እና ከደቂቃ በኋላ መስፍን ከሄኖክ ድልቢ የተላከለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በግብ ጠባቂው በቀላሉ የተያዘበት ኳስ ይጠቀሳሉ።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ወዲያው ግብ አስተናግዷል። በ47ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በቃሉ ገነነ ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ ገጭቶ ቋሚ ሲመልስበት አብዲሳ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
እንደመጀመርያው ሁሉ ሁለተኛውንም ጎል ከቆመ ኳስ የተቆጠረባቸው ሀዋሳዎች በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት መላው የጠፋቸው በሚመስል መልኩ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አልተስተዋለም። በዚህም በረጅሙ ከርቀት በሚላኩ እና ተሻጋሪ ኳሶች ለማጥቃት ያደረጉት ሙከራ ጥሩ የግብ እድል ሳይፈጥርላቸው ቀርቷል። በ79ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር መስፍን ታፈሰ በጥሩ ሁኔታ ወደፊት በመሄድ ያሻገረውን ኳስ በግራ የሳጥኑ ክፍል ሆኖ ያገኘው ኤፍሬም አሻሞ በቀጥታ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበትም ብቸኛዋ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
በአጋማሹ ጅማሮ በድጋሚ ያገኙትን መሪነት የማስጠበቅ አላማ ያለው እንቅስቃሴ ያደረጉት አዳማዎች ተሳክቶላቸው መሪነታቸውን ወደ ድል የቀየሩ ሲሆን በተለይ ተቀይሮ የገባው ኤሊሴ ጆናታን ከተከላካዮች ፊት በመሆን የሰጠው ሽፋን የሚጠቀሰ ነበር።
አዳማ ከተማ ድሉን ተከትሎ ከአስረኛ ሳምንት በኋላ የመጀመርያ ድሉን ሲያስመዘግብ አሰልጣኝ ዘርዓይ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ የመጀመርያ ድል ሆኗል። ከበላዩ ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ አንድ አጥብቧል። ሀዋሳ በተቃራኒው ለሁለተኛ ደረጃ የመጠጋት ወርቃማ ዕድሉን አምክኖ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ተንሸራቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ