ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በርካታ የመነጋገሪያ ነጥቦች ተከስተውበት ሁለት አቻ ተጠናቋል።
የባህር ዳር ከተማ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኙ ሚኪያስ ግርማን በሳለአምላክ ተገኘ፣ ሳምሶን ጥላሁንን በበረከት ጥጋቡ እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝን በምንይሉ ወንድሙ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ቡና ዋና አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ በበኩላቸው ከመጨረሻ ጨዋታቸው አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል። በዚህም ሀብታሙ ገዛኸኝ በአቤል ከበደ ምትክ ወደ ቋሚ አሰላለፍ መጥቷል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው የታዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና በጊዜ መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ አሳርፈዋል። በዚህም በ10ኛው ደቂቃ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች አቡበከር ናስር ከታፈሰ ሰለሞን በተከላካዮች መሐል የደረሰውን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ በወጣው ሀሪሰን ሄሱ አናት ላይ በመላክ ግብ አስቆጥሯል። በተከላካይ መስመሩ የላላ አደረጃጀት እና በግብ ጠባቂው የወረደ ውሳኔ ግብ ያስተናገዱት ባህር ዳር ከተማዎች በ14ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል ለማግኘት ሙከራ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ኃይሌ ገብረትንሳይ ባወጣው ኳስ የተገኘውን የመዓዘን ምት መናፍ አወል ለመጠቀም ጥሮ ወጥቶበታል። ቡድኑ ይህንን ሙከራ ካደረገ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግን አቻ የሆነበትን ጎል ካልታሰበ አጋጣሚ አግኝቷል። በዚህ ደቂቃም ፍፁም ዓለሙ የመሐል ተከላካዮ ወንድሜነህ ደረጄን ያለአግባብ ኳስ በእግሩ ሲያቆይ ፈጥኖ በመሄድ ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ አቤል ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ወደ ጎል በመድረሱ በኩል ተሽለው የታዩት ባህር ዳር ከተማዎች በ31ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃም ምንይሉ ወንድሙ የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በድንቅ ሁኔታ ያመቻቸለትን ተንጠልጣይ ኳስ በመጠቀም በተረጋጋ ሁኔታ ኳስን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ከመምራት ተነስተው ወደ መመራት የተሸጋገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የያዙትን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በጎሎች ለማጀብ መታተር ቀጥለዋል። ቡድኑ በተለይ መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢፈልግም ግብ ካስተናገደ በኋላ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረውን የባህር ዳር የተከላካይ ክፍል ሰብሮ መግባት ተስኖት ታይቷል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተደረጉት ሦስቱም ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ወደ ጎልነት የተቀየሩበት የመጀመሪያውን አጋማሽም በባህር ዳር መሪነት ተገባዶ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
የተከላካይ ክፍል ስህተቶች በጉልህ የታየባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በቦታው ላይ ለውጥ አድርገው አጋማሹን ቢጀምሩም ውጥናቸው ወዲያው ሳይሰምር ቀርቷል። አጋማሹ በተጀመረ ገና በሦስተኛው ደቂቃም ምንተስኖት ከበደ የመጨረሻ ሰው ሆኖ ምንይሉ ላይ በሰራው ጥፋት የሁለተኛ ቢጫ ካርድ (በቀይ ካርድ) አይቶ ከሜዳው ተሰናብቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረን ተጫዋች (እንዳለ ደባልቄ) በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በሜዳ ላይ ያለን ተጫዋች በቀይ ካርድ ያጡት ቡናማዎቹ አሁንም በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው መንቀሳቀስ ይዘዋል። በተቃራኒው የሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ያገኙት የጣና ሞገዶቹ በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው በመታገዝ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ታትረዋል። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ በወሰኑ ዓሊ አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል።
ጨዋታው ቀጥሎም በ65ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡና የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አበበ ጥላሁን ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ወጥቶበታል። ከዚህ መከራ በተጨማሪም ቡድኑ በ70ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ አበበ ለዊሊያም አቀብሎት ዊሊያም ወደ ግብ በመታው ነገርግን ሀሪሰን ባከሸፈው ኳስ ሌላ ጥቃት ፈፅሟል።
ከደቂቃ ደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የልፋታቸውን ውጤት በ73ኛው ደቂቃ አግኝተው አቻ ሆነዋል። በዚህም አቡበከር ናስር ግርማ ዲሳሳ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ ያገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ቡድኖቹ መሪ ለመሆን ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ አንድ ነጥብ ለሁለት የተጋሩት ባህር ዳር እና ኢትዮጵያ ቡና በቅደም ተከተላቸው 32 እና 36 ነጥቦችን በመሰብሰብ 4ኛ እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
©ሶከር ኢትዮጵያ