ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በ24ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ጨዋታዎች የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉ትንሹ ልዑል ክብረወሰኑን በእጁ አስገብቷል 

ስለዚህ ታዳጊ የተሰለቹ የአድናቆት ቃላት መደርደር የእሱን የዘንድሮ አስደናቂ ብቃት ማሳነስ እንጂ እሱን ሊገለፅ የሚችል ቃል ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኗል። ይህ ከእድሜው በብዙ ርቀት የቀደመው በሳል አጥቂ በ2009 በጌታነህ ከበደ በ25 ግቦች ተይዞ የነበረውን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ክብረወሰን በዚህ የጨዋታ ሳምንት የኢትዮጵያ እግርኳስ የወቅቱ አንፀባራቂ ኮከብ በሆነ አቡበከር ናስር እጅ ገብቷል። 

ገና በእግርኳስ ህይወቱ የመጀመርያ ዓመታት ላይ የሚገኘው ትንሹ ልዑል አቡበከር ናስር ገና ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ አለኝ ያለቻቸው አጥቂዎች ያልደረሱበት ይህ ታላቅ እግርኳሳዊ ከፍታ ላይ ገና በለጋ እድሜው መድረሱ በሒደት ይበልጥ እየጎመራ ሲሄድ መድረሻው ምን ይሆን ብሎ ማሰብ ከዛሬ ይልቅ ነገን ለመመልከት አጥብቀን እንድንጓጓ የሚያደርግ ነው። 

ለጌታነህ ከበደ የ25 ጎሎች ክብረወሰን ሁለት ግቦች ብቻ ቀርተውት ወደ 24ኛ ጨዋታ ሳምንት ያመራው አጥቂው ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ሦስት አቻ በተለያየበት ጨዋታ የውድድር ዘመኑ አራተኛ ሐት-ትሪኩን በመስራት በአጠቃላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች መጠን ወደ 27 አድርሶ የሊጉ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን በቅቷል። አጥቂው በዚህ ሳምንት ያስቆጠራቸው ጎሎች ላይ ያሳየው ቅፅበታዊ ውሳኔ እና ቅልጥፍና (የመጀመርያው)፣ ፍጥነት እና የአጨራረስ ቴክኒክ (ሁለተኛው) በሌሎች ጨዋታዎች ላይ እንዳስቆጠራቸው ጎሎች ሁሉ ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ሲሆን የፍፁም ቅጣት ምቱም ቢሆን በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘ ነበር። 

በእግርኳሱ ዙርያ የሚገኙ በሙሉ የአድናቆት ቃላት ያጡለት አቡበከር ሊጉ ከመጠናቀቁ በፊት ገና ሁለት ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ከግምት ውስጥ ሲገባ ይህን ክብረወሰን በቅርቡ እንዳይደርስበት አድርጎ ከፍ አድርጎ ሊሰቅለው የሚችልበት እድል እጅግ ሰፊ ነው።

👉 የጀማል ጣሰው ዕንባ 

በ24ኛው የጨዋታ ሳምንት በዝናባማው ጨዋታ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ከሀዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን አድርገው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም የወልቂጤ ከተማው አምበል ጀማል ጣሰው እያነባ ሜዳውን ለቆ ሲወጣ ተመልክተነዋል። 

ጀማል ጣሰው በተሰበረ ስሜት አቀርቆሮ እያነባ ከሜዳው ሲወጣ በሜዳው ጠርዝ የነበሩት የቡድኑ አዲሱ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ አቅፈው ሊያፅናኑ ቢሞክሩትም ተጫዋቹ ግን ሀዘን ባጠላበት ስሜት ሜዳውን ለቆ ሊወጣ ችሏል። 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቾች ላለመውረድ በሚያደርጉት ጥረት ትልቅ ዋጋ በነበረው ጨዋታ በጥቃቅን ስህተት ያሰቡትን ማሳካት ባለመቻላቸው ክፉኛ ስለማዘኑ ሲነገር ተደምጧል።

👉 ደካማ ቀን ያሳለፈው ሀብታሙ ተከስተ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጫዋችነት ከታጩት መካከል የፋሲል ከነማው አማካይ ሀብታሙ ተከስተ ይጠቀሳል። ሀብታሙ የፋሲል የአማካይ ክፍልን በመምራት ግሩም ጊዜ ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ከተክለ ሰውነቱ አንፃር ከፍተኛ የአካል ብቃት እንደሚጠይቅ በሚታመንበት የተከላካይ አማካይ ስፍራ አብዛኞቹን ጨዋታዎች በቦታው ያለተጨማሪ ተጣማሪ በመጫወት ወጥ አቋሙን ሲያሳይ ቆይቷል። 

ባለፈው ሳምንት በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው አማካዩ በዚህ ሳምንት ቡድኑ በድሬዳዋ ከተማ 3-1 ሲሸነፍ ወደ አሰላለፉ ቢመለስም እጅግ የተዳከመ ዕለት አሳልፎ ወጥቷል። ከምንም በላይ ቡድኑ ከመሪነት ወደ ተመሪነት የተሸጋገረባቸው ሁለት ጎሎች ከተከላካይ አማካዩ ስህተት የመነጩ ነበሩ።

እርግጥ ነው በየትኛውም የእግርኳስ ደረጃ ላይ ያሉ ምርጥ ተጫዋቾች መጥፎ ቀናት ይገጥሟቸዋል። ሀብታሙም አጠቃላይ የፋሲል ዕለታዊ አቋም በወረደበት ጨዋታ በግሉም መጥፎ ቅፅበቶች ገጥመውታል። ቡድኑ ከኋላ ኳስ መስርቶ እንዲወጣ በማስቻል የራሱ ሚና የነበረው ተጫዋቹ ከእሱ እግር ቁጥጥር ውጪ በወጡ ኳሶች ተጋጣሚው ድሬዳዋ ግቦችን ሲያስቆጥር መልሶ ለማስጣል ያደረገው ጥረትም እጅግ ደካማ ሆኖ ታይቷል። በዋልያዎቹ ስብስብ ጭምር በቦታው የመጀመሪያ ተመራጭ መሆን የቻለው ሀብታሙ በቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ቀደመ ትኩረት እና ቅልጥፍናው መመለስ ይኖርበታል።

👉የሥዩም ተስፋዬ ምሳሌያዊ ተግባር 

ከቡድን በተቃራኒ በተወሰኑ ውሳኔዎች ሁሉ ዳኛን የመክበብ እና የማዋከብ አባዜ በተጠናወተው ሊጋችን ጥፋት ፈፅመው የሚፀፀቱ ብሎም ከማዋከብ ተቆጥበው ውሳኔዎችን በፀጋ የሚቀበሉ ተጫዋቾችን ማግኘት በቀላሉ የሚቻል አይደለም። 

በ24ኛ ሳምንት ጅማ አባጅፋር ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የጅማ አባጅፋሩ አንጋፋ የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው ሥዩም ተስፋዬ ለብዙዎች በምሳሌነት የሚጠቀስን ተግባር ፈፅሟል። በዚህም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመሰናበት የተገደደው ተጫዋቹ ጥፋቱን አምኖ የጨዋታውን አርቢትር ከውሳኔው በኃላ ጨብጦ የወጣበት መንገድ እጅጉን የሚበረታታ ተምሳሌታዊ ተግባር ሆኖ የሚወሳ ይሆናል። 

ከዚህ ቀደምም በዘንድሮው ውድድር ባህር ዳር ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ እንዲሁ ኳስን በግብ ክልል ውጭ በእጅ በመንካቱ በቀይ ካርድ ሲሰናበት በተመሳሳይ ስህተቱን አምኖ ዳኛውን ጨብጦ የወጣበት መንገድ በተመሳሳይ ብዙ አድናቆት ሲቸረው አስተውለናል። እንደ ሥዩም ተስፋዬ አይነት እና ሌሎች ባለልምድ ተጫዋቾች መሰል ተምሳሌታዊ ተግባራትን በመፈፀም ለሌሎች ታዳጊ ተጫዋቾች አርዓያ መሆን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

👉 የሚካኤል ጆርጅ ትክክለኛ ቦታ ይህ ይሆን ?

ተጫዋቾች በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚታወቁበትን ዋነኛ የጨዋታ ሚና ሲቀይሩና ውጤታማ ሲሆኑ መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ከቀድሞዎቹ ይልማ ተስፋዬ እስከ እስማኤል አቡበከር ፣ ከአዳነ ግርማ እስከ አዲስ ህንፃ እንዲሁም እስከ ቅርቦቹ ሙጂብ ቃሲም ድረስ በርካታ ተጫዋቾች በአሰልጣኞች ውሳኔ ወይም በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚና ለውጥ አድርገው የቀድሞ የሜዳ ውስጥ ኃላፊነታቸውን ሲያስረሱ አስተውለናል።

ሁለገብነትን በሚያበረታቱት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስር በተለያዩ ክለቦች ከዋነኛው የአጥቂነት ሚናው በተጨማሪ በተለያዩ ሚናዎች ሲጫወት የተመለከትነው ሚካኤል ጆርጅም ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን ባጣበት ባለፉት ሦስት ሳምንታት በአማካይ ስፍራ እጅግ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን ችሏል። በትልቅ ደረጃ የመጫወት ልምድ ከሌለው ወጣቱ ክብረአብ ያሬድ ጋር በአማካይ ስፍራ የተጣመረው ሚካኤል በመከላከል ወቅት ለተከላካይ ሽፋን ሲሰጥ ፣ የመልሶ ማጥቃት ሲያስጀምር፣ ከሳጥን ሳጥን ሜዳ ሲያካልል እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ለተመለከተው ይህን ሚና ለረጅም ጊዜ የተወጣ አስመስሎታል። 

በሙገር እና ሲዳማ ቡና ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ባሉት ዓመታት በተጓዘባቸው ክለቦች እንደ አጥቂ ጎሎችን ለማስቆጠር ተቸግሮ የቆየውና በሒደትም የመሰለፍ ዕድል አጥቶ የነበረው ሚካኤል በአዲሱ ሚናው እንደ አዲስ የተወለደ ተጫዋች ይመስላል። በአጥቂነት ተቀይሮ በገባባቸው ጨዋታዎች ሳያደርገው ቢቆይም ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ግብ አስቆጥሮ ለሌላኛው ግብ ደግሞ መንስኤ ሲሆን ተመልክተነዋል። በዚህም ሳምንት እንዲሁ ድንቅ የጨዋታ ዕለትን ማሳለፍ ችሏል። ከውጤታማነቱ ባሻገር በእነዚህ ጨዋታዎች በእንቅስቃሴዎቹ ወቅት የሚታይበት ከፍተኛ ተነሳሽነትም የተሰጠው ኃላፊነት ምቾት ሰጥቶት እየተገበረው እንደሆነ የሚገልፅ አንዱ ማሳያ ነው። ይህንን ለተመለከተ ተጫዋቹ ከፊት አጥቂነት ይልቅ አማካይ ክፍል ላይ በመጫወቱ ቢቀጥል ውጤታማ ሊሆን ይችላል ብሎ ቢያስብ ስህተት አይሆንም። የዛኑ ያህል በቡድኑ ላይ አስገዳጅ ለውጦች ለመደረጋቸው ምክንያት የሆነው ችግር አልፎ ክለቡ በቂ ተጫዋቾች ኖረውት ወደ ቀደመ መረጋጋቱ ሲመለስ ተጫዋቹ በቀደመ ቦታው ላይ ዳግም ተሰይሞ ልነመለከተውም እንችላለን። ያም ሆነ ይህ ግን አማካዩ ሚካኤል ሰሞኑን እያሳየ ያለው ብቃት በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም። 

በመሰል ተጫዋቾቹ የተለየ ወቅታዊ ብቃት በመታገዝ ያበቃለት መስሎ የነበረው የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎን ለማግኘት ዕድሉን ያሰፋው ሀዲያ ሆሳዕናም ይህን ተሳትፎ ለማሳካት ከኢትዮጵያ ቡና በሚጠብቀው ወሳኝ ፍልሚያ ላይ አዲሱ አማካይ እንዳለፉት ጨዋታዎች ድንቅ አበርክቶ የሚኖረው ከሆነ ምናልባትም ቀጣይ የእግርኳስ ህይወቱን በአዲስ ምዕራፍ የሚመራበት መንደርደርያ ሊሆነው ይችላል።

👉 ተክለማርያም ሻንቆን ያስረሳው አቤል ማሞ 

የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ግብጠባቂ የሆነው ተክለማርያም ሻንቆ በክለቡ ኢትዮጵያ ቡና በድንገት በተመለከተው ቀይ ካርድ መነሻነት በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የመሰለፍ እድል ባገኘው አቤል ማሞ ቦታውን ከተነጠቀ ሳምንታት ተቆጥረዋል። 

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጠባቂ የነበረው እና በሂደት ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጭ የሆነው አቤል በኢትዮጵያ ቡና ቤት አሁን ላይ እያገኘ የሚገኘውን የመጫወት እድል በሚገባ እየተጠቀመበት ይገኛል። ተጫዋቹ ከመሰረታዊ የግብጠባቂ ክህሎቶች ባለፈ ከኳስ ጋር እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴ ድንቅ ነው። 

በሁለቱም እግሮቹ የተመጠኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ እያደረሰ የሚገኘው ተጫዋቹ እያሳየ ከሚገኘው ሰሞነኛ አስደናቂ ብቃት አንፃር ተክለማርያም ሻንቆ በቋሚዎቹ መሀል አለመኖሩ እንዲዘነጋ እያደረገ ይገኛል። በዚህ ሂደት የሚቀጥልም ከሆነ ከራቀበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ የመመለሻው ጊዜ እጅጉን የቀረበ ይመስላል።

👉የድሬዳዋ የውጭ ዜጋ አጥቂዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል 

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በድሬዳዋ ከተማ ደረጃ የግብ እድሎችን የሚፈጥር ነገር መጠቀም የተሳነው ቡድን አለ ማለት አይቻልም። ይህ ችግር ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ለሚገኝበት የወራጅነት ስጋት አይነተኛ ምክንያት ነው። 

ሦስት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን አጥቂዎችን በስብስቡ ያካተተው ቡድኑ ከእነዚህ ተጫዋቾች በሚፈልገው ልክ ተጠቅሟል ብሎ ለመናገር እጅግ አስቸጋሪ ነው በንፅፅር ጁንያስ ናንጂቡ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ የሪችሞንድ አዶንጎ እና ኤታሙና ኬይሙኒ አበርክቶ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። 

ነገርግን በ23ኛው እንዲሁም በ24ኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ውጤትን አጥብቆ በሚፈልግበት በዚህ ወቅት ከፍ ያለ ትችት ያስተናግዱ የነበሩት ሁለት አጥቂዎች ለቡድኑ ግቦችን አስቆጥረዋል። በውድድር ዘመኑ ምንም ግብ ሳያስቆጥር የከረመው ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ ባለፈው ጨዋታ ወልቂጤን ሲረቱ ሁለት እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንድ ግብ ሲያስቆጥር ናሚቢያዊው አጥቂ ኤታሙና ኬይሙኒ ደግሞ በዚህኛው ሳምንት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ጎሉን ከ18 ጨዋታ በኋላ ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎቹ እጅግ ዘግይተውም ቢሆን ቡድኑ ጎሎችን በሚፈልግበት ወሳኝ ሰዓት ለቡድናቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ለድሬዳዋ ተስፋ የሚሰጥ አጋጣሚ ሆኗል።