“ሁሌም ለጨዋታ ራሴን አዘጋጅ ነበር” – ሳላዲን በርጌቾ

ከ15 ወራት በኋላ በዛሬው ዕለት ለመጀመርያ ጊዜ መጫወት የቻለው ሳላዲን በርጌቾ ስላሳለፈው ጊዜ ይናገራል።

ሳላዲን በርጌቾ በ2005 ከኢትዮጵያ መድን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በክለቡም ሆነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀዳሚ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ሆኖ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል። ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙት ጉዳቶች ምክንያት እድገቱን ጠብቆ በሚፈለገው ደረጃ በወጥ አቋም መዝለቅ እንዳይችል አድርጎታል። በእግርኳስ ህይወቱ በተለይ በቅርብ ዓመታት ፈታኝ ውጣ ውረዶችን ያለፈው ተጫዋቹ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ ከሜዳ ርቆ ቆይቷል። ተጫዋቹ ከወራት በፊት አገግሞ የነበረ ቢሆንም በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ፈረሰኞቹ አዳማ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ ዳግም ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ተጫውቶ መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ለሳላዲን ሰዒድ ጎልም ኳስ ማመቻቸት ችሏል። ሳላዲን ስላሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ እና ስለ ቀጣይ ዕቅዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” ከምትወደው ሙያ ራቅ በጣም ከባድ ነው። በዙርያዬ ብዙ የሚያግዙኝ ሰዎች በመኖራቸው ወደ ጨዋታ መመለስ ችያለው። በተለይ ከባህር ዳር ድሬዳዋ ጀምሮ ለጨዋታ ዝግጁ ነበርኩ። ለዚህም አሰልጣኙን እንዲያጫውተኝ ጠይቄው ነበር። ሆኖም የኔን እንቅስቃሴ አይቶ የማውያቅ ስለነበር እንዲሁም የቡድናችን ውጤት ጥሩ ያልነበረ በመሆኑ ዕድሉን ሳላገኝ ቀርቼ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ብዙ ቆይቼ ነበር። አላህ የፈቀደው ነው የሚሆነው ዛሬ ለመጫወት ችያለሁ።

” አሁን ከጉዳቴ ድኛለው። ዐምናም ቢሆን ተሽሎኝ እንቅስቃሴ ስጀምር ኮሮና መጥቶ ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ ከጉዳቴ ድኜ ነበር። ያም ቢሆንም ለዘንድሮ ውድድር በዝግጅት ወቅት ዳግም በመጎዳቴ ከጨዋታ ርቄ ብቆይም ከጅማው ውድድር ጀምሮ በተጠባባቂ ወንበር በመግባት ራሴን ለጨዋታ ሳዘጋጅ ቆይቻለሁ።

” ሁሌም ራሴን አዘጋጅ ነበር። ቅድም እንዳልኩህ አሰልጣኜ እንዲጠቀምብኝ እና ቡድኔን ማገልገል እንድችል ደጋግሜ እጠይቅ ነበር። አሰልጣኜም ቆይ ትንሽ ጠብቅ ከጉዳት ስለመጣህ በቪዲዮም ያንተን እንቅስቃሴ ስላላየው በአንዴ እድሉን መስጠት አልችልም ይለኝ ነበር። እኔ ግን ሁሌም ዕድሉን እስካገኝ ድረስ ራሴን በሚገባ ለጨዋታ አዘጋጅ ነበር። ለዛም ነው ዛሬ ከፈጣሪ ጋር ወደ ጨዋታ ተመልሼ ጥሩ ጊዜ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ማሳለፍ የቻልኩት።

” ብዙዎች እኔን ድሮ ወደምታወቅበት አቋም እንድመጣ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አውቃለሁ። እነርሱም ብቻ ሳይሆን እኔም ወደሚፈለገው ትክክለኛ አቋሜ መመለስን በሚገባ እፈልጋለሁ። እድሜዬም ገና ነው፤ ኳስ የማቆምበት አይደለም። አሁን ውድድሩ አልቋል፤ አንድ ጨዋታ ነው የቀረው። በሚቀጥለው ዓመት ከወዲሁ ራሴን አዘጋጅቼ ክለቤን በምችለው አቅም ለማገልገል አስባለሁ።”