በ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ ያልነበሩት መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ስሑል ሽረ በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር እንዲመለሱ በማሰብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከክለቦቹ ጋር ግንኙነት መጀመሩ ተገልጿል፡፡
በ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ በትግራይ ክልል የሚገኙት ሦስቱ ክለቦች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሊጉ ሳይሳተፉ በመቅረታቸው ውድድሩ በአስራ ሦስት ክለቦች ብቻ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል። በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ሳይሳተፉ የቀሩት ክለቦች በ2014 ዳግም ወደ ሊጉ ተመልሰው መጫወት እንደሚችሉ ከዚህ በፊት መገለፁ የሚታወስ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ከክለቦቹ ጋር ግንኙነት መጀመሩን የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው “ከሥራ አስፈፃሚዎች ጋር በጋራ በመሆን ከክለቦቹ ጋር ግንኙነት ጀምረናል። በምላሻቸው እንደሚመለሱ ነግረውናል። ግንኙነታችንን አሁንም አጠናክረን ቀጥለናል። ሊመለሱ የሚችሉበት መንገድም የሰፋ ነው።” በማለት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የሊግ ካምፓኒው የትግራይ ክልል ሦስቱ ክለቦች የማይሳተፉ ከሆነ ከከፍተኛ ሊግ በሦስቱም ምድብ ሁለተኛ ሆነው የጨረሱ እና ከፕሪምየር ሊጉ የወረዱ ሦስቱ ክለቦች ጋር የመለያ ጨዋታ (Play off) ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴው ስኬታማ ሆኖ ወደተሳታፊነታቸው ከተመለሱ ይህ እቅድ የማይተገበር ይሆናል፡፡ ባገኘነው መረጃ መሠረት የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ሦስቱም ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ በጀት እንዲመደብ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ሰምተናል፡፡