ከከሰዓቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ
በመጨረሻ ደቂቃ ግብ አስቆጥረው ስለማሸነፋቸው?
እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ከነበረብን የስነ-ልቦና ችግር አንፃር ዛሬ ያገኘነው ውጤት ቀጣይ ለምናደርጋቸው ጨዋታዎች እጅግ የሚያነሳሳን ነው። በአጠቃላይ እንደውም እኔ የዛሬውን ውጤት ወርቃማ ድል ብዬ ነው የምገልፀው።
በጨዋታው ስለነበራችው ጥንካሬ?
ዛሬ ለእኔ ጠንካራ ጎናችን በመከላከሉ ረገድ የነበረን ነገር ነው። በማጥቃቱ ላይ ግን ብዙ አልተሳተፍንም። በዚህ ዓመት ካደረግናቸው ጨዋታዎች ትንሽ የወረደ እንቅስቃሴ ያደረግንበት ጨዋታ የዛሬው ጨዋታ ነወ። ይህ ደግሞ ትምህርት ሆኖን በቀጣይ የምናስተካክለው ይሆናል። እንዳልኩትም ማጥቃት ላይ የነበረን ተሳትፎ ደከም ያለ ነበር። ሁለቱንም ጎል ያስቆጠርነውም በእንቅስቃሴ ሳይሆን በቆመ ኳስ ነው። ይህንን እናርማለን።
ዛሬም ዱሬሳ በመጨረሻ ሰዓት ግብ ስለማስቆጠሩ?
ዱሬሳ ወጣት እና ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው። ከሁሉም በላይ ተጫዋቹ የሚነገረውን ነገር ማዳመጡ እና ያንን ነገር ሜዳ ውስጥ ለመተግበር ያለውን መስጠት መቻሉ ያስደስተኛል። ለእንደዚህ አይነት ወጣቶች እድሉን መስጠት ዛሬ እኛ ያገኘነውን ፍሬ እንዲገኝ ያደርጋል።
ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) – ሀዲያ ሆሳዕና (ምክትል አሠልጣኝ)
ስለ ተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ?
ከተጫዋቾቹ ከምፈልገው በላይ አግኝቻለሁ።
በቋሚነትም ሆነ ቀይሮ ስላስገባቸው ወጣት ተጫዋቾች?
ዛሬ ሦስት ተጫዋቾች ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ መጥተው ቋሚ ሆነዋል። እንደታየውም በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የተጫወቱ ተጫዋቾችም አይመስሉም። አጨዋወታቸውም የሚያሳየው ይሄ ነው። ይዘን የገባነውን ነገር ተግብረዋል። ሁለት ቀይረን ያስገባናቸውም ተጫዋቾች ከ20 ዓመት ቡድኑ የመጡ ናቸው። እነሱም የሚጠበቅባቸውን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቀው በላይ ብቃት አሳይተዋል። በአጠቃላይ ግን ወጣቶቹ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጫዋቾች ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። እንደ ክፍተት ግን ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ካለማድረግ የመጣ ችግር ጎሎችን እንድናስተናግድ አደረገን እንጂ ተጫዋቾቹ ከሚፈለግባቸው በላይ አድርገዋል። ለዚህም ደግሞ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።
ተሸናፊ የሆኑበት ጎል ባለቀ ሰዓት ስለመቆጠሩ?
የዛሬውን ጨዋታ እንቅስቃሴ ስትመለከት እኛ ማሸነፍ ይገባን ነበር። ግን ማሸነፍ እየተገባህ አቻ የምትወጣበትን ዕድል እንኳን ስታጣ ትንሽ ስሜትህ ይጎዳል። ምንም ማድረግ ስለማይቻል ግን ውጤቱን ተቀብለናል።
2ኛ ደረጃን ይዞ ስለማጠናቀቅ?
አሁንም አልራቅንም። ቡድናችን ተስፋ እንዳለው ያሳያል። ግን ዕድሉ ትንሽ ጠበብ ያለ ይመስላል። ለማንኛውም ፉክክር ውስጥ ስለሆንን የምንችለውን እናደርጋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ