የ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ፋሲል ከነማ በሁለት ሺህ ደጋፊዎች ፊት ዋንጫውን ከፍ እንደሚያደርግ ታውቋል።
የዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ያለ ደጋፊዎች ሲደረግ ቆይቷል። እርግጥ በውድድሩ መሐል የየክለቦቹ 10 ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም ከቫይረሱ ስርጭት አንፃር ክልከላው ዳግም ተጥሎ ሊጉ ያለ ደጋፊ እየተከወነ ይገኛል። የሊጉን ዋንጫ ቀድመው ማግኘታቸውን ያተጋገጡት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ ዋንጫውን ሲረከቡ 5 ሺ ደጋፊዎቻቸውን በስታዲየሙ እንዲገኙ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ይሄንን ጥያቄም በሲዳማ ክልል ለተቋቋመው ኮሚቴ (ከጤና ቢሮ፣ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ፖሊስ የተወጣጡ ግለሰቦች ያሉበት) የመራው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ለክለቡ ምላሽ መስጠቱ ተሰምቷል።
በዚህም ቅዳሜ የሊጉ አሸናፊ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የስታዲየሙ ተመልካች የመያዝ አቅም ተጠንቶ 2 ሺ ደጋፊዎች ጥንቃቄ እና ርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ ስታዲየም እንዲታደሙ መፈቀዱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።