ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

የ23ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ መርሐ-ግብር የሆነውን የአዳማ እና ሀዋሳን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በዛሬው ዕለት ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው አዳማ ከተማ (ምናልባት የትግራይ ክለቦች በቀጣይ ዓመት ካልተሳተፉ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሊተርፍ ይችላል) የተጣላው ከሚመስለው ድል ጋር ለመታረቅ ብቻ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል። ቀስ በቀስ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ፉክክር ራሱን የከተተው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ሲረከብ ያሳየውን ምርጥ ብቃት ለመድገም እና በአሸናፊነት ለመዝለቅ ድልን እያለመ ለጨዋታው ይቀርባል።

ለወትሮ በአስጊው ቀጠና (ወራጅ ቀጠና) የማይገኘው አዳማ ከተማ ዘንድሮ በተለየ መንገድ በወራጅ ቀጠናው ሲዛክር ከርሟል። በዛሬው ዕለት ግን ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ ማግኘቱን ተከትሎ ቡድኑ 2007 ላይ ወደ ሊጉ ካደገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን መውረዱን አረጋግጧል። ዘንድሮ ሁለት አሠልጣኞች (አስቻለው እና ዘርዓይ) ተፈራርቀው የመሩት አዳማ ከተማ ከአስከፊው የሊጉ አጀማመር ለማገገም በሁለተኛ ዙር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቢቀላቅልም ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል። እርግጥ አዲሶቹ ተጫዋቾች በተወሰነ መልኩ ቡድኑ የተሻለ ብቃት እንዲያሳይ ቢያደርጉም በወሳኞቹ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ውስጥ (የራሱ እና የተጋጣሚ) የተደራጀ እንቅስቃሴ አለማስመልከቱ እና ዘግይቶ መንቃቱ ለደረሰበት ደረጃ አብቅቶታል። ከምንም በላይ ደግሞ ጎል ፊት መፍትሄ ያለው የማይመስለው ቡድኑ በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን በራሱ ወስኖ በአሸናፊነት እንዳይወጣ አድርጎታል።

የአዳማ ከተማ ጉዳይ በሂሳባዊ ስሌቶች ያከተመለት ቢመስልም የትግራይ ክልል ክለቦች የቀጣይ ዓመት ተሳትፎ ነገር በውል አለመታወቁ በሊጉ ለመቆየት የመጨረሻ ዕድል ሊሰጠው ይችላል። ይህ እስኪረጋገጥ ድረስ ግን ቡድኑ ቀሪዎቹን የሊጉ መርሐ-ግብሮች በውድድር ዓመት አጋማሽ የመጡትን ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር በደንብ አዋህዶ ለጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹን ለመቅረብ ሊጠቀምበት ይችላል። ከዚህ ውጪ “እንወርዳለን? አንወርድም?” የሚል ጫና ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ የነበሩት ተጫዋቾች በመጥፎም ቢሆን ሀሳባቸው መቋጫ በማግኘቱ በነፃነት በቀሪ ጨዋታዎች ሊጫወቱ ይችላሉ። ከምንም በላይ ደግሞ በቅርብ ጨዋታዎች የፊት መስመር ተጫዋቾች ላይ ሲታይ የነበረው እና ከበዛ ጉጉት የመነጨ እንደሆን የሚታሰበው የጎል ፊት አይናፋርነት ሊቀረፍ ይችላል። ይህ ደግሞ ለሀዋሳ ከተማ ፈተናን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል።

ከሲዳማው አስደንጋጭ ሽንፈት ውጪ ተከታታይ ድሎችን ሲያስመዘግብ የነበረው የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳ ከተማ በመቀመጫ ከተማው ያገኘውን የአሸናፊነት መንገድ በቀላሉ የሚለቅ አይመስልም። በተለይ ከሰሞኖኑ ቡድኑ ካለበት ጥሩ የተነሳሽነት ስሜት መነሻነት ጨዋታዎችን በአዎንታዊ መንገድ ሊቀርብ ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ በሀዲያው ጨዋታ ቡድኑ የነበረው የማጥቃት ፍላጎት ድንቅ ነበር። በጨዋታውም ከመስመር ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ባለፈም መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶች በርከት ብለው ታይተዋል። ነገም በተመሳሳይ በዚሁ የማጥቃት አስተሳሰብ ወደ ሜዳ በመግባት የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ላይ ጫና ለማሳደር እንደሚታትር ይገመታል።

እርግጥ ቡድኑ በሆሳዕናው ጨዋታ ጥሩ የነበረው የተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ አግኝቶ እንደነበረ ቢታሰብም ነገም ከተጋጣሚው (አዳማ ከተማ) ደካማ ብቃት አንፃር ተመሳሳይ ብልጫ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። በዚህም በቁጥር በዝቶ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባት አዎንታዊ ነገሮችን ለማምጣት ይጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ግን የመስፍን ታፈሰ ወደ ጎል አስቆጣሪነት መመለስ ለቡድኑ መልካም ነው። ተጫዋቹም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ከጎል ጋር መታረቁ ያለውን የራስ መተማመን ያሳድግለታል። ይህ ደግሞ ሀዋሳን ይጠቅማል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ ለ38 ጊዜያት የመገናኘት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በድምሩ 84 ግቦችን አስቆጥረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 45ቱ በሀዋሳ ከተማ 39ኙ ደግሞ በአዳማ ከተማ ተመዝግበዋል። ጠንከር ያለ የሜዳ ላይ ፉክክር በሚያስተናግደው ጨዋታቸውም ሀዋሳ 18 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ በ9 ጨዋታዎች ድል ቀንቶት 11 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ