“ስሜታዊ በመሆን ላደረኩት ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ” – አምሳሉ ጥላሁን

ዐፄዎሉ በታሪክ የመጀመርያ የሊግ ዋንጫቸውን ባነሱበት ዕለት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስለተፈጠረው ጉዳይ አምሳሉ ጥላሁን አስተያየቱን ሰጥቷል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጠናቀቁ ከአንድ ጨዋታ አስቀድሞ ዛሬ የዋንጫ አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት በፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ላይ ሲከናወን በአቻ ውጤት ተለያይተው ዐፄዎቹ የድል ዋንጫቸውን ከፍ አድርገው ማንሳታቸው ይታወቃል። በዕለቱ ጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ለሀዋሳ የፍፁም ቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ ባጋጣመው ጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ በመሆን በክቡር ትሪቡን ተቀምጦ ጨዋታውን ሲከታተል የቆየው የዐፄዎቹ የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ወደ ዕለቱ ዳኛ በመሄድ ያልተገባ ግብግብ መፍጠሩ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ባደረገው ነገር እንደተፀፀተ በዚህ መልኩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

” ጨዋታውን አሸንፈን ዋንጫውን ለማንሳት ካለኝ ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ በጨዋታው ሊጠናቀቀ ሰከንድ ሲቀረው ፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥብን በጣም ስሜታዊ በመሆን ወደ ሜዳ በመግባት ያደረኩት ነገር በኋላ ሳስበው ተገቢ አለመሆኑን ተረድቻለሁ። ላሳየሁት ያልተገባ ባህሪ እንዲሁም ስሜታዊ በመሆን ላደረኩት ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ።”