​ሪፖርት | የዱሬሳ ሹቢሳ ጎል ሀዲያ ሆሳዕናን አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጎታል

በከሰዓቱ ጨዋታ ያልተጠበቀ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ሀዲያ ሆሳዕና በሰበታ ከተማ 3-2 ተሸንፏል።
ዋና አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለን ከኃላፊነት በማንሳት በምክትሉ ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) እየተመራ የገባው ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳው ሽንፈት አንፃር ተጎድቶ ወጥቶ የነበረው ተዘራ አቡቴን በደስታ ዋሚሾ ሲተካ ክብረአብ ያሬድም ከአዲስ አዳጊዎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች መሀል የመሰለፍ ዕድል አግኝቷል። 

በሰበታ ከተማ በኩል ከሲዳማ ቡና ነጥብ ከተጋራው ስብስብ መሳይ ጳውሎስ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ፉዓድ ፈረጃ በአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ ናትናኤል ጋንቹላ ፣ ክሪዚስቶም ንታምቢ እና ከቅጣት የተመለሰው አዲስ ተስፋዬ ተተክተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው ባልተጠበቀ ሁኔታ የሄደበት ነበር። የተጫዋች ክፍተቶቻቸውን በታዳጊዎች አሟልተው ወደ ሜዳ የገቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከሰበታ ከተማ በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ ተሽለው ታይተዋል። እንደሁል ጊዜው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ሰበታዎች አብዛኛውን ደቂቃ በራሳቸው ሜዳ ላይ ሆነው ለማሳለፍ ተገደዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በመጠኑ ተሽለው ቢታዩም ከዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ሳጥን ይላኩ የነበሩ ኳሶች በሀዲያዎች የመከላከል ትኩረት እና በረዳት ዳኛው የተሳሳቱ የጨዋታ ውጪ ውሳኔዎች ልዩነት መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአመዛኙ ቅርፃቸውን ሳይለውጡ ተጋጣሚያቸው ወደ አደጋ ክልል እንዳይደርስ በማድረግ አልፎ አልፎም በራሱ ሜዳ ላይ ለማፈን በመጣር ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወደ ፊት ገፍቶ በማጥቃቱም አልሰነፉም። 13ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከረጅም ርቀት ያደረገው የቅጣት ምት ወደ ውጪ ከወጣበት በኋላም በፈጣን ሽግግር ደጋግመው ወደ ሰበታ ሳጥን መድረስ ችለዋል። ቡድኑ 34ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ የገባበት የማጥቃት ሂደትም አዲሱ ተስፋዬ በደስታ ዋሚሾ ላይ ጥፋት ሰርቶ አቋርጦታል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ አቅርቦ ሳይፀድቅለት ቀርቷል።

በዳዋ ሆቴሳ ታታሪነት የታጀበው የቡድኑ የማጥቃት ሂደት 37ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ዳዋ ከቀኝ መስመር ሞክሮት የተመለሰበትን ኳስ አሳልፎለት በሰበታ ተከላካዮች መሀል ራሱን ነፃ አድርጎ የነበረው ሚካኤል ጆርጅ በቀጥታ መትቶ አስቆጥሯል።

ሀዲያዎች በቀኝ መስመር የነበራቸው አስፈሪነት 43ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ እንዲያስቆጥሩ በር ከፍቶም ነበር። ዱላ ሙላቱ በዛው አቅጣጫ ገብቶ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ እንዳለ አባይነህ መትቶ ፋሲል ገብረሚካኤል አድኖበታል። ሰበታዎች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ ሲቃረብ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ሀዲያ ሳጥን ለመቅረብ ባደረጉት ጥረት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አጥቂው ኦሰይ ማዎሊ ከኢብራሁም ከድር የተላከለትን ኳስ ለመቆጣጠር ሲሞክር በበረከት ወልደዮሃንስ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን ይህን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ለውጦ ጨዋታውን አቻ አድርጎታል። 

ሁለተኛው ረጋማሽ ሲጀምርም ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአምስት ደቂቃ ሁለት አደገኛ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ከዳዋ ሆቴሳ እና ከሚካኤል ጆርጅ ከተነሱት ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች መካከልም የመጀመሪያው በእንዳለ አባይነህ እና ደስታ ዋሚሾ ጥቅም ላይ ሳይውል ሲቀር ሁለተኛውን ዳዋ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ወደ ላይ ወጥቷል። ዳዋ 59ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ከባድ ሙከራ ሲያደርግ ለማዕዘን ምቱ ምክንያት የሆነውን ኳስም ከቀኝ መስመር ለደስታ እና እንዳለ አመቻችቶ ወጣቶቹ አጥቂዎች በድጋሚ አባክነውት ነበር። 

ሰበታዎች በዚህ መልኩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም 62ኛው ደቂቃ ላይ በኦሰይ ማዎሊ ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አግኝተዋል። የዕለቱን ዳኛን ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ክስተት ደግሞ የሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ስንታየሁ ታምራት ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሀመድን የአየር ላይ ኳስ በተቆጣጠረው ኦሰይ ማዎሊ ላይ የሰራው ጥፋት ነበር። ሆሳዕናዎች መመራት ከጀመሩ በኋላም ወደ ፊት ጫና ፈጥረው ማጥቃታቸውን አላቋረጡም። ከዚህ መነሻነት ያገኟቸው የነበሩ ተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን ግን ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም። ልፋታቸው ውጤት እንዲያስገኝም እስከ 82ኛው ደቂቃ ድረስ መታገስ ነበረባቸው። 

ሀዲያዎች በረጅሙ የላኩት ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ሚካኤል ጆርጅ ከርቀት አክርሮ ሲመታ ፋሲል ሲያድነው ዳዋ ሆቴሳ አመቻችቶለት አዲስ አዳጊው ደስታ ዋሚሾ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ቢሆን ሰበታ ከተማዎች የወትሮው ኳስ የመቆጣጠር ባህሪያቸው ሳይታይ የሆሳዕናዎች አልሞት ባይ ተጋዳይነት እስከመጨረሻው ቀጥሏል። ነገር ግን ከተጠባባቂነት በመነሳት በሰበታ ከተማ ተፅዕኖ ሲፈጥር የሚታየው ዱሬሳ ሹቢሳ ጨዋታው ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ከኦሴይ ማዎሊ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ አሳርፏል። ይህች ጎልም ሰበታ ከተማን ሦስት ነጥብ ስታስጨብጥ ሀዲያ ሆሳዕናን ግን አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጋለች። 

ሰበታ ከተማ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 30 አድርሶ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ሦስተኝነት ከፍ ሊል የሚችልበትን ዕድል አጥቷል።