በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ፍልሚያው ውስጥ ልዩነት ፈጣሪው ጨዋታ ላይ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
የሊጉ የአንደኝነት ቦታ በፋሲል ቁጥጥር ስር ከሆነ ቢቆይም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመሰታፍ ዕድልን የሚሰጠው የሁለተኛ ደረጃ ግን የተፈለገ እስከማይመስል ድረስ በቡድኖች እየተገፋ ነው። ቦታውን በጥሩ የነጥብ ልዩነት መያዝ ይችሉ የነበሩ ተፎካካሪ ክለቦች ባለቡት በመቆማቸውም የሁለተኝነት ተስፋ ያላቸው ቡድኖች ቁጥር ሰባት ደርሷል። ከእነዚህ ክለቦች ውስጥ ደግሞ በተደጋጋሚ ማምለጥ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ያባከኑት ባህር ዳር እና ኢትዮጵያ ቡና ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ።
ከተጋጣሚው አንፃር የአራት ነጥብ የበላይነት ያለው ቡና ወቅታዊ ሁኔታው በውጤት ከባህር ዳር የተሻለ ቢመስልም ከተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመራቅ የነገውን ዕድል ካልተጠቀመ የቀጣይ ጨዋታዎቹን ጫና ከፍ ያደርጋል። 31 ነጥቦች ላይ የቆመው ባህር ዳርም ማሸነፍ ካልቻለ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመንሸራተት ራሱን ያመቻቻል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ ለሁለቱም አልፎ ተርፎም ለሌሎቹ የደረጃው ፈላጊዎች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መናገር ይቻላል።
በመቀመጫ ከተማው ባደረጋቸው ጨዋታዎች እንዲሁም ድሬዳዋ ላይ ባደረገው ቀዳሚ ጨዋታ አራት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገበው ባህር ዳር በመቀጠል ሁለት ተከታታይ አቻዎች እና ሦስት ሽንፈቶች አግኝተውታል። ይህ ግራ የሚያጋባ መንሸራተት በሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ውስጥ በጉልህ ይታያል። በተለይም እንደ ፍፁም ዓለሙ ባሉ ተጫዋቾች የግል ብቃት ላይ የተንጠለጠለው የቡድኑ የማጥቃት ዕድሎችን የመፍጠር መንገድ ለተጋጣሚዎቹ ቀላል የሆነ ይመስላል። ውጤቱ ጥሩ በነበረባቸው ጨዋታዎች ላይ በግብ አስቆጣሪዎች ስብጥር እና ዕድሎችን በመፍጠሪያ ዕቅዱ ዓይነቶች መበረካት ተስፋ ቢሰጥም ዳግም ችግሩ አገርሽቶበት ታይቷል።
የዚህ ድምር ውጤትም እንደቡድን ሜዳ ላይ ያለው የማሸነፍ ስሜት ሊያውም የደረጃ እና የነጥብ መሻሻልን በሚያመጡ ጨዋታዎች ላይ እጅግ ወርዶ እንዲታይ መንስዔ የሆነ ይመስላል። በመሆኑም በወሳኝ ቅፅበቶች ላይ ክፍቶትችን በአግባቡ መዝጋት እየተሳነው ግቦችን በማስተናገድ ሲቸገር ተመልክተናል። ከነገው ተጋጣሚው አንፃር ሲታይ ደግሞ ክፍተት የመስጠት እና የትኩረት መውረድ ችግሮች ይበልጥ ዋጋ ሊያስከፍሉት እንዳይችሉ ያሰጋል። ያም ቢሆን በሥነ ልቦናው ረገድ ተጠናክሮ ከተመለሰ ከባድ ጨዋታዎችን አሸንፎ ለመውጣት አዲስ እንዳለመሆኑ መጠን ውጤት ይዞ ለመውጣት ዕድሉ ይኖረዋል። በተለይም በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ቡናን አጨዋወት ከጅምሩ በማፈኑ ረገድ ያሳየውን ውጤታማ የጨዋታ ዕቅድ ከጥሩ ትኩረት ጋር ዳግም ከተገበረ ግብ የማግኘት ዕድሉ የሰፋ ነው።
በኢትዮጵያ ቡና በኩልም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋላሉ። በሊጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግቦችን ከማስቆጠር አንፃር ከቻምፒዮኑ ፋሱል ከነማ ጋር የሚገዳደረው ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ ኳስ እና መረብን ካገናኘ ሦስት ጨዋታዎች አልፈዋል። በተለይም በመከላከል አደራጃጀታቸው ደከም ካሉ ተጋጣሚዎች ጋር ደጋግሞ ግብ ሲያስቆጥር ይታይ የነበረው ቡና ተፎካካሪዎቹ ስህተታቸውን በቀነሱ ቁጥር በትዕግስት ኳስ ይዞ በመጫወት ቀዳዳን ፈልጎ የማግኘት ጥንካሬውን እያጣ መጥቷል። ያንን ተከትሎም በተለመደው አኳኋን የጨዋታ የበላይነትን ይዞ ቢታይም ይሄ ነው የሚባል አስፈሪነት ሳይታይበት ጨዋታዎችን እየጨረሰ ይገኛል።
ይህን መሳዩ የቡድኑ አኳኋንም የተሰላፊዎቹን የተናጠል ብቃት እና የቡድን መናበብ የቀነሰው ሲሆን በአጠቃላይ ሜዳ ላይ የሚታይበትም ተነሳሽነት እንዲሁ ፈዘዝ ብሏል። ያለፉት ሁለት ተጋጣሚዎቹ ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻ በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ መቆየትን ምርጫቸው በማድረጋቸውም የተነሳሽነቱ መቀነስ ለተደጋጋሚ ጥቃት አላጋለጠውም። ነገር ግን የነገ ተጋጣሚው ምንም እንኳን ጥሩ ጊዜ ላይ ቢሆንም ዳግም ጠንካራ ጎኑን ካገኘ ቡና ከሜዳው ኳስ መስርቶ የሚወጣበትን ሂደት የማወክ እና የማስጨነቅ ዕድል ሊኖረው ይችላል። ይህን ተቋቁሞ ወደ ፊት መሄድ እና ምንአልባትም ካለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ሁኔታ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ክፍተቶች በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ከቡና ይጠበቃል።
በጥቅሉ ተጠባቂው ጨዋታ ባለፉት ሳምንታት እነሱን አልመስል ያለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን ለማረም በሁለቱ ተጋጣሚዎች በኩል የሚደረግ ብርቱ ፉክክር ይወጣዋል ተብሎ ይጠበቃል። የተኛው ቡድን የቁርጥ ቀን ተጫዋቾቹን ብቃት መልሶ ያገኛል ? ማን ፊት ላይ የነበረውን አስፈሪነት መልሶ ያገኛል ? የትኛው ቡድንስ ራሱን ከስህተት ጠብቆ ውጤት ይዞ ይወጣል ? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስም ነገ ረፋድ የምናየው ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በእስካሀኑ ሦስት ግንኙነታቸው ተመጣጣኝ ውጤት ያላቸው ቡና እና ባህር ዳር አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ የመጨረሻ ጨዋታቸው ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና ሰባት እንዲሁም ባህር ዳር ሦስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
©ሶከር ኢትዮጵያ