​የአሠልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-0 አዳማ ከተማ

በሰበታ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የከሰዓቱ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ከአሠልጣኞች ተቀብሏል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ዛሬ ቡድናችን ከሥነ-ልቦና ጫና ነፃ ስለነበረ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥሮ ነበር። በዚህም የምንፈልገውን ውጤት ይዘን ወጥተናል። ጨዋታውም በምንፈልገው መልኩ ሄዷል። ነገርግን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ትንሽ የመቻኮል ሁኔታ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በአማካይ እና በአጥቂ ክፍሉ መካከል የነበረው ግንኙነት ትንሽ የሳሳ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ግን ከዚህ በተገላቢጦሽ ነበር። በሁለቱ ቦታዎች ያለው ጨዋታ እና ቅርርቦሽ መልካም ስለነበር ሁለት እና ሦስት ያለቀላቸው ኳሶችን አግኝተን ነበር። ግን አልተጠቀምንባቸውም። በቀጣይም ይሄንን በሚገባ አስተካክለን እንመጣለን። ግን ደረጃችንን እና ነጥባችንን ከፍ የሚያደርግ ውጤት ስለነበረ ተጫዋቾቼን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።

2ኛ ደረጃን ይዞ ስለማጠናቀቅ?
መንገዱ ክፍት ነው። ቡድኖች እየጣሉ ከመጡ እና እኛ እያሸነፍን ከመጣን ተስፋ አለ። ዞሮ ዞሮ ግን እኛ ደረጃችንን አሻሽለን ቀጣዮቹን ጨዋታዎች እያሸነፍን በጥሩ ሁኔታ ሊጉን ማጠናቀቅ ነው ሀሳባችን።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች?

በቀጣይ ጨዋታ ዛሬ እንዳደረግነው ተተኪ ተጫዋቾችንም እያስገባን እንጫወታለን። ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ ሙሉ ሃላፊነት አንሰጣቸውም። ምክንያቱም ደረጃው ለእኛም ስለሚያስፈልገን።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለተቆጠረባቸው ጎል እና ስለ ጨዋታው?

በግብ ጠባቂያችን እና በተከላካያችን የኳስ ቅብብል ስህተት ነው ግቡ የተቆጠረብን። ሰበታዎች አጋጣሚውንም ተጠቅመዋል። ከእረፍት በኋላ ግን እኛ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ወደ ጎልም የተሻለ ደርሰናል። ግን በአጠቃላይ ቡድናችን ጥሩ አልነበረም።

ታዳጊ ተጫዋቾችን ስለመጠቀሙ?

አዎ ታዳጊ ተጫዋቾችን እንጠቀማለን። ዛሬም ለማየት ሞክረናል። ሌሎችንም ደግሞ በቀጣይ እንሞክራለን።

የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ስለሆነው አቡበከር ናስር ብቃት እና ስለ አብዲሳ ጀማል?

አቡበከርን የቡድኑም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አግዘውታል። ዞሮ ዞሮ የተጫዋቹ አቅም ምንም ጥርጥር የሌለው ነው። ትልቅ ተጫዋች ነው። ከዚህም በላይ ትልቅ ቦታም ይደርሳል ብዬ አስባለሁ። በእኔ ቡድን ውስጥ አብዲሳ አለ። አብዲሳም በራሱ ጥረት እዚህ መድረሱ ራሱ አቅሙን ያሳያል። ስለዚህ የሁለቱ ተጫዋቾች ቡድንም እነሱ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ ግን አቡበከርን ትልቅ አጥቂ ነው ብዬ ነው የምገልፀው።