በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እንዲህ አሰናድተናል።
የጎል መረጃዎች
– በዚህ ሳምንት በስድስት ጨዋታዎች 15 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህ ሳምንት ካለፈው የጨዋታ ሳምንት በሁለት ከፍ ያለ የጎል ቁጥር ተመዝግቦበታል።
– ከተቆጠሩት 15 ጎሎች መካከል ስምንት ግቦች ከእረፍት በኋላ ሲቆጠሩ ሰባት ጎሎች ከእረፍት በፊት ተቆጥረዋል።
– አንድ የፍፁም ቅጣት ምት በዚህ ሳምንት ተቆጥሯል። የሀዋሳው ብሩክ በየነ የብቸኛው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ባለቤት ነው።
– አስር ተጫዋቾች ለቡድኖቻቸው ጎል ማስቆጠር ሲችሉ አንድ በራስ ላይ ተቆጥሯል። ኦኪኪ አፎላቢ ሦስት ጎሎች አስቆጥሮ ቀዳሚ ሲሆን አቡበከር ናስር እና ቸርነት ጉግሳ ሁለት ግብ አስቆጥረዋል።
– የወልቂጤ ከተማው ቶማስ ስምረቱ ብቸኛው ራሱ ላይ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
– አማኑኤል ተርፉ እና ዓለምብርሀን ይግዛው በዚህ ሳምንት የመጀመርያ የውድድር ዘመን ጎላቸውን አስቆጥረዋል።
– አቡበከር ናስር እና ይገዙ ቦጋለ ተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታ ላይ ጎል ማስቆጠር ችለዋል።
– የሲዳማ ቡናው ኦኪኪ አፎላቢ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ሐት ትሪኩን ሰርቷል።
የሳምንቱ ስታቶች
(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)
ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ
ከፍተኛ – ሀዋሳ ከተማ (7)
ዝቅተኛ – ጅማ አባጅፋር (1)
ጥፋቶች
ከፍተኛ – ወላይታ ድቻ (28)
ዝቅተኛ – ጅማ አባ ጅፋር (10)
ከጨዋታ ውጪ
ከፍተኛ – ጅማ፣ ሆሳዕና እና ቡና (3)
ዝቅተኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (0)
የማዕዘን ምት
ከፍተኛ – ሲዳማ ቡና (10)
ዝቅተኛ – ወልቂጤ ከተማ (0)
የኳስ ቁጥጥር ድርሻ
ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (75%)
ዝቅተኛ – ሀዲያ ሆሳዕና (25%)
የዲሲፕሊን ቁጥሮች
– በዚህ ሳምንት 21 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ ምንም ቀይ ካርድ አልታየም።
– የዚህ ሳምንት የቢጫ ካርድ ቁጥር ካለፈው ሳምንት በ1 ዝቅ ያለ ነው።
– ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ አምስት ቢጫ ካርዶች ተመዘውበታል። ይህ ከዚህ ሳምንት ጨዋታዎች ከፍተኛው ነው።
– ፋሲል ከነማ በአምስት ቢጫ የሳምንቱ ቀዳሚ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ (0) ዝቅተኛውን ቁጥር አስመዝግቧል።
– የፋሲል ከተማው ሽመክት ጉግሳ፣ የወልቂጤ ከተማው ሀብታሙ ሸዋለም እና የጅማ አባ ጅፋሩ ኤልያስ አታሮ የውድድር ዘመኑን አምስተኛ ቢጫ ያዩ እና ቀጣይ ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው። ሦስት ጨዋታ የተቀጣው የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁንም የመጨረሻው ጨዋታ የሚያመልጠው ተጫዋች ነው።
ከቡድኖችም በላይ – አቡበከር ናስር
እጅግ አስደናቂ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር 28ኛ እና 29ኛ የሊግ ጎሉን አስቆጥሯል። ይህም አቡበከር እንደ ቡድን ቢቆጠር ከሊጉ ክለቦች አምስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጥ ነበር። በሊጉ ከአቡበከር በላይ ጎል ማስቆጠር የቻሉት የሚጫወትበት ኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ብቻ መሆናቸው አስገራሚ ያደርገዋል።
ከጎል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ቡና ካስቆጠራቸው 43 ጎሎች መካከል በ33 ጎሎች ላይ (29 ጎል እና 4 አሲስት) ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው አቡበከር ያለፉት 11 ተከታታይ የኢትዮጵያ ቡና ጎሎችን ማንንም ጣልቃ ሳያስገባ አስቆጥሯል።
SUPER SUB – ይገዙ ቦጋለ
– የሲዳማ ቡናው አጥቂ ይገዙ ቦጋለ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሏል። ቡድኑ ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተቀይሮ በመግባት ያስቆጠረው ይገዙ በዚህ ሳምንትም ጅማ አባ ጅፋር ላይ ተቀይሮ በገባ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ይህንኑ ለሦስተኛ ተከታታይ ደግሞታል።
ኦኪኪ አፎላቢ
በዚህ ሳምንት ብቸኛ ሐት ትሪክ ሰሪው አጥቂ የሆነው ናይጄርያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በኢትዮጵያ ቆይታው ለአራተኛ ጊዜ በጨዋታ ሦስት አስቆጥሯል። በ2010 የውድድር ዘመን በጅማ አባ ጅፋር ሁለት፣ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ደግሞ በመቐለ ይህን የፈፀመው ኦኪኪ አሁን ደግሞ በሲዳማ ቡና ቆይታው አሳክቷል።