ሁለተኛ ደረጃን ለማግኘት ወሳኝ የነበረው ፍለልሚያ በቡና አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለጨዋታው እና ውጤቱ
የነበረው ነገር ጥሩ ነው። የገመትናቸው ነገሮች ነበሩ ከእነሱ የስነ ልቦና ዝግጅት አንፃር፤ ጊዮርጊስን አሸንፈው ነው የመጡት ከዛ አንፃር። ሁለተኛ እነሱም ለሁለተኝነት ዕድል ነበራቸው። ስለዚህ ለማግባት መጫወት ነበረባቸው። እንደገና ደግሞ ለእኛ ቡድን የሚሰጡትም ግምት አለ። ስለዚህ ከእነዚህ ስነ ልቦናዎች አንፃር የትኛው ላይ ያርፋሉ በሚለው እርግጠኛ ስላልነበር አመጣጣቸው ከዛ አንፃር የተቃኘ ስለሚሆን ቡድናችን በሦስቱም በኩል በስነልቦና እንዲዘጋጅ ነበር ያደረግነው። ከሦስቱ በአንዱ በገመትነው መጥተዋል። የእኛ ተጫዋቾች ምላሽ ጥሩ ነበር።
በተከላካይ መስመር ያሉ ስህተቶች እየተቀረፉ ስለመሆኑ
ጨዋታው ራሱ ስህተቶችን በቀላሉ ለማየት ዕድል የሚሰጥ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስህተቶቹ ጎልተው የሚነገሩት ጨዋታው ራሱ ስህተቶችን በቀላሉ ለማየት የሚጋብዝ በመሆኑ ነው፤ ያ ታሳቢ መሆን አለበት። ለምሳሌ የመጀመሪያው ጎል ሲገባብን የእኛው ካስ ነበር፤ አማኑኤል ኳስ ለመቆጣጠር ሲሞክር ከእግሩ አምልጦት ነው። ያው በምንጫወትበት ጊዜ መክፈት ግድ ነው። የኳስ ባለቤት ስለሆነ በዛ አጋጣሚ የተገኘ ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ሁሌም የምንለው የትኛውም ቦታ ላይ ያለ ተጫዋች ቦታውን እንዲያጠብ ነው። እና ላይ ትንሽ ዝግ የማለት ነገር ነበር ። ብዙ በከፈትናቸው ክፍተቶች ያን ያህል ተጠቃሚ ነበሩ ብዬ አላስብም።
ስለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ
አዎ፤ ቡና ሁሌም ለቻምፒዮንነት የሚጫወት ቡድን ነው። እሱን ታሳቢ አድርገን ሁሌም እዛ ደረጃ ውስጥ ለመገኘት ነው ጥረት የምናደርገው። ያ ደግሞ በራሱ ለኮንፌዴሬሽንም ለሌላውም ውድድር ይዞህ ይሄዳል። እና ሁልጊዜ ከዛ ውስጥ ላለመውጣት ነው የምንፈልገው።
የኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ
የመረጥኩት አቡበከር ፣ አቤል ማሞ እና ሽመክትን ነው።
ኢያሱ መርሐፅድቅ – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለ ጨዋታው
“ተጫዋቾች የነገርካቸውን ነገር እየተገበሩ በመሐል ወጣ ያለ ነገር ሲኖር ዋጋ አስከፍሎን የመጀመሪያው ጎል ገባ። ከዛ በተረፈ ግን መሥራት የሚገባቸውን አንዳንዴም መሥራት ከሚገባቸው በላይ ሰርተዋል። ማመስገን ነው የሚጠበቅብን።
አበበከርን ስለተከላከሉበት መንገድ
ይሄ ግልፅ ነው፤ አቡበከር ናስር ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች ነው። በግሉ የሚያደርጋቸው ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ። ከጓደኞቹም ጋር ሆኖ እንደዛው። ስለዚህ እንዳጠቃላይ እንደቡድም ለማቆም ዕቅዱ ነበረን። ግን በተወሰነ መልኩ አልተሳካልንም። እሱም ወጤታማ ሆኗል፤ ቡድኑም አሸናፊ ሆኗል። እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፤ ጥሩ ነበሩ። ኳሱን ተቆጣጥረውታል፤ ያ ግልፅ ነበር ሲጀመርም።
ስለቡድኑ የዓመቱ ጉዞ
አላለቀም፤ አንድ ጨዋታ ይቀራል። የትኛውን ደረጃ ይዘን እንደምንጨርስ አላወቅነውም። ግን ስንጀምርም ደረጃ ውስጥ ሆነን ለመጨረስ ነበር ዕቅዳችን። አሀንም ደረጃ ውስጥ ነው ያለነው አልራቅንም። ካሉብን የውስጥ ችግሮች አንፃር ወጣ ገባ ነበረው እንጂ አሁን ላይ እየተገበርን ያለውን ነገር ወይም ወፊት ስንመጣ የነበረን ጥሩ ነገር አዲስ አበባ ላይ መጀመሪያ በነበረን አቋም ልክ ነበር። ስለዚህ መልካም ነው፤ ዝም ብለን ደረጃውን ብቻ ካየን በጠበቅነው ልክ ነው ብለን መናገር እንችላለን።
በወጣቶቹ ደስተኛ ስለመሆናቸው
የሚገባ!