ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ25ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ25ኛው ሳምንት በተካሄዱት ስድስት ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝ ተከታዮቹን ምርጥ አስራ አንድ መርጠናል።

አሰላለፍ: 3-5-2

ግብ ጠባቂ

ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ክለብ የግብ ዘብ የሆነው ሚኬል ሳማኬ ከሁለት ጨዋታ እረፍት በኋላ በተሰለፈበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድንቅ ጊዜ አሳልፏል። ቡድኑ ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አንድ ለአንድ ሲለያይም ተጫዋቹ እንደተለመደው ምርጥ ብቃቱ ላይ ነበር። በተለይም ግብ ጠባቂው ፈጣኖቹ የሀዋሳ አጥቂዎች ወደ ግብ የሰነዘሯቸውን እና ቅልጥፍና፣ ትኩረት፣ ፍጥነት እንዲሁም ጥሩ የጊዜ አጠባበቅ የሚጠይቁ ኳሶችን ሲያመክን ታይቷል። በጨዋታው ያለቀላቸው የግብ ማግባት ሙከራዎችን ከማዳኑ ባለፈም ሳማኬ ቡድኑን ከኋላ ሲመራበት የነበረው መንገድ አድናቆት የሚያስቸረው ነበር።

ተከላካዮች

ዳንኤል ዘመዴ – ፋሲል ከነማ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታ የጀመረው ዳንኤል ዘመዴ በጨዋታው ያሳየው ብቃት ያልተጠበቀ ነበር። ተጫዋቹ በመጀመሪያ ጨዋታው የሀዋሳን ተጫዋቾች ጥቃት ለመመከት ያደረገው የግሉ ጥረት መልካም ነበር። ከዚህ ውጪ ጨዋታውን ሲያነብ የነበረበት መንገድ፣ ከአጣማሪው (ያሬድ ባየ) ጋር የነበረው መስተጋብር እና ቅልጥፍና ጥሩ ነበር። ምንም እንኳን በዚህ ጨዋታ ፋሲል የጠሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ቢሰነዘሩበትም ዳንኤል በግሉ በጨዋታው ጎሎቶ መውጣት ችሎ ነበር።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከተማን ረቶ ደረጃውን ሲያሻሽል የተረጋጋው የቡድኑ የኋላ መስመር ወሳኝ ነበር። ቡድኑን የተረጋጋ የተከላካይ ክፍል ባለቤት ያደረገውም ደጉ ደበበ ነው። በጨዋታው ከሁለት የተለያዩ አጣማሪዎች ጋር የተጫወተው ደጉ ቡድኑን በመምራት፣ ኳሶችን በማቋረጥ እና የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ የሆነውን ተሻጋሪ ኳሶች በማሳለጥ ጥሩ ቆይታ ነበረው። እርግጥ የባህር ዳር የማጥቃት እንቅስቃሴ ያን ያህል ያየለ ባይሆንም ስክነት በተሞላበት አጨዋወቱ የኋላ ክፍሉን የተቆጣጠረበት መንገድ የሚደነቅ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሁለተኛውን ጎል ቸርነት ጉግሳ ሲያስቆጥር ከአጋሩ (ቸርነት) ጋር የተግባባበት እና የተጋጣሚን ተከላካዮች አቋቋም ያስተዋለበት መንገድ እንዲሁም የተመጠነ ኳስ ማቀበሉ እንዲሞካሽ አድርጎታል።

ሳልሀዲን በርጊቾ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከ14 ወራት በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው የመሐል ተከላካዩ ሳልሀዲን በርጊቾ ከሜዳ የራቀ እስካይመስል ድረስ በጨዋታው ጥሩ ሆኖ ተጫውቷል። በሦስት ተከላካዮች ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑም ወደ ቀኝ አዘንብሎ ሲከላከል ከነበረው ሳልሀዲን ብዙ ሲጠቀም ነበር። እርግጥ አዳማ ከተማ በማጥቃቱ በኩል ያን ያህል ተሽሎ ባለመገኘቱ ሳልሀዲን በመከላከሉ ረገድ ሥራዎች በዝተውበት ባይታይም ለግብ የሚሆኑ ቀጥተኛ ኳሶችን ከኋላ ሆኖ ሲያስጀምር የነበረበት መንገድ ድንቅ ነበር። በዋናነትም ረጃጅም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ በመላክ ግብ የማስቆጠሪያ አማራጭ ሲሆን ነበር። በዚህ ሒደትም ቡድኑ የጨዋታውን የመክፈቻ ጎል እንዲያስቆጥር ረድቷል።

አማካዮች

አማኑኤል እንዳለ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠበትን ድል ጅማ ላይ ሲቀዳጅ አማኑኤል እንዳለ የነበረው ብቃት ምርጥ ነበር። ተጫዋቹ ክፍተቶችን ለመዝጋት ተቀራርበው (ወደ ፊትም ሆነ ወደ ጎን) ሲጫወቱ የነበሩትን የጅማ ተጫዋቾች ለመበታተን እና ለመዘርዘር መስመሩን ታኮ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ዋጋቸው ከፍተኛ ነበር። የመጀመሪያውን ጎል ኦኪኪ እንዲያስቆጥርም የእርሱ የመስመር ላይ ሩጫ እና የመጨረሻ ኳስ አስፈላጊ ነበር። በተጨማሪም ከሁለተኛው ጎል ውጪ የተቆጠሩት ቀሪዎቹ ጎሎች ላይም አማኑኤል ተሳትፎ አድርጎል።

አለልኝ አዘነ – ሀዋሳ ከተማ

ቁመተ መለሎው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አለልኝ አዘነ ቡድኑ ከሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበር። የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ በአመዛኙ ወደ ኋላ እየተሳበ ሲጫወት የነበረው አለልኝ ወደ ፊት በሄደባቸው ጊዜያትም አደጋ ፈጥሮ ሲመለስ ነበር። በተለይ ከሳጥን ውጪ የሚያገኛቸውን ኳሶችም ወደ ግብነት ለመቀየር ሲጥር ታይቷል። በአጠቃላይ እንደ አማካይ ከኳስ ጋር ቡድኑ ጠጣር እንዲሆን እና የፋሲል ተጫዋቾች በተከላካይ እና አማካይ ተጫዋቾች መካከል ክፍተት እንዳያገኙ ከኳስ ውጪ የነበረው የሜዳ ላይ ቆይታም ሸጋ ነበር።

ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ድንቅ ጊዜን ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ዳዊት ተፈራ ነው። ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማው እና ደፋር የሆነው ዳዊት ቡድኑ ጅማ ላይ ካስቆጠራቸው ጎሎች ገሚሱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው። በተለይም ሲዳማ በኳስ ቁጥጥር ብዙውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንዲያሳልፍ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ከጥልቅ ቦታ በመነሳት ሲያደርገው የነበረው ጥረት መልካም ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ተጫዋቹ አላማ ያላቸው ኳሶችን በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመላክ የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ጋር ሲያገናኝ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም ምርጥ ቡድናችን ውስጥ አካተነዋል።

ታፈሰ ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ቆይታን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ቁልፍ ተጫዋች የሆነው ታፈሰ ሀዲያ ላይ ቡድኑ ላገኘው ድል ቀጥተኛ ተሞጋሽ ነው። በሙሉ 90 ደቂቃው የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው ተጫዋቹም አደጋቸው ከፍ ያሉ ኳሶችን በተደጋጋሚ ከእግሩ ሲያወጣ ታይቷል። በተለይም አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመከላከል ላይ ያሳለፈው ሀዲያ ሆሳዕናን ለማስከፈት ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ለአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ሲያቀብል ነበር። ከምንም በላይ የአንደኛው ጎል ሒደት ላይ ጉልህ ተሳትፎ ሲያደርግ የሁለተኛው የአቡበከር ጎል እንዲቆጠር የመጨረሻ ኳስ ያቀበለበት መንገድ ደግሞ በውድድር ዓመቱ ከታዩ ድንቅ አሲስቶች ግምባር ቀደሙ ነበር።

ቸርነት ጉግሳ – ወላይታ ድቻ

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ምርጥ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ቸርነት ጉግሳ ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስቻሉ ሁለት ጎሎችን በጨዋታ ሳምንቱ አስቆጥሯል። ቸርነት በተሰለፈበት መስመር የሚያደርገው ፍጥነት የታከለበት ሩጫ ልዩ ነው። በተለይ ደግሞ ተጫዋቹ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት የተጫዋቹን ብቃት የሚመሰክሩ ናቸው። በባህር ዳሩም ጨዋታ ከመስመር ሰብሮ እየገባ ተከላካዮችን ሲረብሽ ተስተውሏል። የመጀመሪያውም ጎል ሲቆጠር የግል ጥረቱን ያሳየበት ሁለተኛውን ኳስ ከመረብ ሲያሳርፍ ደግሞ የቦታ አያያዝ እንዲሁም የተከላካዮችን አቋቋም ያነበበበት መንገድ የሚያስደንቅ ነበር። ከተጫዋቹ ታታሪነት አንፃር በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን የግራ መስመር ላይ አካተነዋል።

አጥቂዎች

ኦኪኪ አፎላቢ – ሲዳማ ቡና

ፈርጣማው የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ ቡድኑ በሊጉ እንዲተርፍ አስተዋጽኦ ያደረገ ሐት ትሪክ ጅማ አባጅፋር ላይ ሰርቷል። በጨዋታው በብዙ መስፈርቶች ጥሩ የነበረው ተጫዋቹ ባሳየው ብቃት የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ገብቷል። ከምንም በላይ ደግሞ በአስረኛ ጨዋታ አስር ግቦች ላይ ተሳትፎ ያደረገበትን ዕለት ያሳለፈው ተጫዋቹ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር የሚያመቸውን ቦታ አፈላለጉ፣ ኳስ አገፋፉ እና የአጨራረስ ብቃቱ ከፍ ያለ ነበር።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

ከጨዋታ ጨዋታ የስፖርት ቤተሰቡን ማስደመም የቀጠለው አቡበከር ናስር በዚህ የጨዋታ ሳምንትም እንደለመደው ጎሎችን አስቆጥሯል። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ በቀጣይ ዓመት በኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ላይ ቀጥተኛ ተፎካካሪው የሆነው ሀዲያ ሆሳዕናን ለማሸነፍ አስፈላጊ ነበር። ወሳኞቹን ጎሎችንም ሲያስቆጥር ያሳየው ብቃት እጅግ አስገራሚ ነበር። በዋናነት ደግሞ በጨዋታው ከቡድን አጋሮቹ ጋር ያለው መስተጋብር ከፍተኛ ነበር። ከዚህ ውጪ ከአቻነት ጎል በኋላ የማጥቂያ ክፍተት ነፍጎ ሲከላከል የዋለው ሆሳዕና የተከላካይ ክፍልን ትኩረት ወደ መስመር እና ወደ አማካዮች እየወጣ ሲበታትን የነበረበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

አሠልጣኝ

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

በ25ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወሳኝ ከነበሩ መርሐ-ግብሮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ግንባር ቀደሙ ነው። በቀጣይ ዓመት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያሳትፈውን ደረጃ (2ኛ) ለመያዝ በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም የኢትዮጵያ ቡናው ዋና አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ በጥሩ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ በመግባት ወሳኝ ሦስት ነጥብ አግኝቷል። ከምንም በላይ ወደ መከላከሉ አዘንብሎ በቁጥር በዝቶ የሚጫወተው የሀዲያ ሆሳዕና ጠጣር የኋላ መስመር ለመክፈት መፍትሄ የነበራቸው አሠልጣኙ በጥሩ ብልጫ ጨዋታውን ከውነው በበላይነት አጠናቀዋል። ይህንንም ተከትሎ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን የአሠልጣኝነት ቦታን እንዲይዙት አድርገናል።

ተጠባባቂዎች

ተክለማርያም ሻንቆ (ኢትዮጵያ ቡና)
ጌቱ ኃይለማርያም (ሰበታ ከተማ)
አማኑኤል ተርፉ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ዳዊት እስጢፋኖስ (ሰበታ ከተማ)
እንድሪስ ሰዒድ (ወላይታ ድቻ)
ዊልያም ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)
መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)
ሳላዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)