የሲዳማ ቡናን ደካማ የውድድር ዓመት ጉዞ መቀልበስ ከቻሉ ዋና ተጫዋቾች መካከል አንዱ ከሆነው ኦኪኪ አፎላቢ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በሀገራችን እግርኳስ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ተሳትፎ በብዛት መታየት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በሊጉ ለሌሎች ዜጎች የተሰላፊነት ዕድል መስጠቱ የሀገሪቷን ወጣቶች ዕድል ከመሻማቱ አንፃር ሲተች በተሻለ የብቃት ደረጃ ላይ ያሉ ተጫዋቾችን ከውጪ ማምጣቱ ልምድ ለመውሰድ እና የሊጉን ደረጃም ከፍ ከማድረግ አንፃር ጠቀሜታ እንዳለው ይነሳል። ነገር ግን ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያ የሚሆኑ በትክክልም ያላቸው ብቃት ጎላ ብሎ የሚታዩ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ተጫዋቾች በቁጥር በርካታ ነው ማለት አይቻልም። በችሎታቸው ከፍ ብለው ቢታዩ እንኳ ለረጅም ጊዜ በወጥነት የማገልገል ችግር የሚስተዋልባቸውም ጥቂት አይደሉም። በሌላ በኩል ከአንድ በላይ ዓመታትን በሊጉ የቆዩ እና አቋማቸውን ጠብቀው በውጤታማነት የሚዘልቁ ለፕሮፌሽናሊዝም ምሳሌ መሆን የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ። አሁንም በሊጉ ውስጥ ከሚገኙ እና በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ ተጫቾች ውስጥም ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ አንዱ ነው።
ግዙፉ የፊት መስመር ተሰላፊ በ2010 የውድድር ዓመት ነበር ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመጣው። በመጣበት ዓመትም በ23 ግቦች ከፍተኛ ግብ አግቢ ሲሆን ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስቷል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት ደግሞ በግብፁ ኢስማዒልያ እና ዳግም በጅማ አባ ጅፋር ቆይታ አድርጎ 2012 ላይ መቐለ 70 እንደርታን በመቀላቀል አሳልፏል። ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስም 7 ግቦችን ማስቆጠር ችሎ ነበር። የኮቪድ ወረርሺኝ መከሰት እና ከእግር ኳስ እንቅስቃሴው መቆም በኋላ የዘንድሮው ውድድር ሲጀመር ግን ኦኪኪ በኢትዮጵያ አልነበረም። ይልቁኑም ውድድሩ ከተጋመሰ በኋላ የመውረድ ስጋት አንዣቦበት የነበረው ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሏል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ባሳለፍነው ቅዳሜ የሰራውን ሐት ትሪክ ጨምሮ በአስር ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻችቷል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በዚህ የእርሱ ብቃት ጭምር የታገዘው ሲዳማ ቡና ለከርሞው በሊጉ መቆየት ችሏል። ተጫዋቹ በዚህ እጅግ መደሱቱን ሲገልፅ የቀድሞው ክለቡ ጅማ አባ ጅፋር መውረድ ለጅማ ካለው ፍቅር አንፃር እንዳሳዘነውም አልሸሸገም። ትኩረት ሳቢው ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍ ያለ ስም ያለው ኦኪኪ ወደ ሜዳ ሲመለስ ላለመውረድ የሚታገል ቡድንን ምርጫው ማድረጉ ነው። ብዙዎች እንደሚገምቱትም በሁለት ክለቦች ከአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጋር አብሮ መስራቱ ለዚህ መነሻ ሆኖታል። “ቡድኑ በሊጉ ላይ እንደሚቆይ በፈጣሪዬ እምነት ነበረኝ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ በአሰልጣኜ ላይ ዕምነት ነበረኝ።” የሚለው አስተያየቱ እንዲሁም የተጫዋቹ እና አሰልጣኙ ለሦስተኛ ጊዜ መገናኘት በራሱ በመሀላቸው ያለው ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። “አሰልጣኝ ገብረመድኅንን እንደአባቴ ነው የማየው። እኔ በሥራዬ ታማኝ ነኝ። አንድ ነገር እንድሠራ ካዘዘኝ መቶ ፐርሰንት አቅሜን እጠቀማለሁ። ለዛም ነው ሁሌም ከአሰልጣኜ ጋር ተግባብቼ መስራት የቻልኩት።” ሲልም ከፈጣሪ ቀጥሎ ዕምነት ስላሳደረባቸው አሰልጣኙ ይናገራል።
ኦኪኪ በሲዳማ ቡና መለያ 16ኛው ሳምንት ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ አዲሱን ክለቡን ማገልገል ጀምሯል። ጨዋታው ለቡድኑ አምስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ሆኖ ቢመዘገብም የናይጄሪያዊው ተፅዕኖ በቀጣይ ሳምንታት ከፍ ብሎ ሊታይ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነበር። እውነትም ቡድኑ ቀስ በቀስ ድሎችን እያስመዘገበ መዝለቅ ቻለ። ኦኪኪም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም። ግቦችን ከማስቆጠር ባለፈ የቡድኑን አጠቃላይ የማጥቃት ሂደት መምራት ጀመረ። ከጎኑ ካሉ አጥቂዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ በመሳብ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ቶሎ ቶሎ በቅብብሎች ይገናኛል ፣ ኳስ እየገፋ ተጫዋቾች ይቀንሳል ፣ ከኳስ ውጪ በእንቅስቃሴ ለቡድን አጋሮቹ ክፍተት ይፈጥራል ፣ ሳጥን ውስጥ ሲገኝም የወትሮው አስፈሪነቱ አብሮት ይታያል። ለወራት ከውድድር ርቆ የተመለሰ ተጫዋች 15 ሳምንታትን በዘለቀ ሊግ ውስጥ በዚህ ፍጥነት ተፈላጊው የጨዋታ ዝግጁነት ላይ ሆኖ መታየቱ ምን ያህል ታታሪ ስለመሆኑ ምስክር ነው። “እኔ ሁሌም ሥራ ላይ ነኝ። የዕረፍት ጊዜ እንኳን ቢሆን ከቤተሰቦቼ፣ ከልጄ ጋር እሰራለሁ። እያንዳንዱን ቀን ወደ ጂም እሄዳለሁ። ከሜዳ ርቄ በመቆየቴ ጨዋታ ላይ እንዲደክመኝ አልፈልግም። ለዛም ነው ወደ ጨዋታ ስመልስ እምብዛም ያልከበደኝ። ሊጉ ጠንከር ብሏል። ግን ሥራ ላይ ከቆየክ በተለየ ሁኔታ አይከብድህም። ጠንካራ ሆኖ ቢጠብቀኝም ለእኔ እንደሁልጊዜው ነው።”
ኦኪኪ በ17ኛው ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታውን ከአዳማ ከተማ ጋር ሲያደርግ እና 3-0 ሲያሸንፍ የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ቻለ። በቀጣዮቹ ጨዋታዎችም የግቦቹ ቁጥር ከፍ እያሉ እና በቡድኑ ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ ሄዷል። በዚህ ውስጥም ከሌላኛው የቡድኑ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ጋር ያለው ጥምረት ለተጋጣሚ ቡድኖች ስጋት የመሆኑ ነገር ከቀን ወደ ቀን እያደገ መጥቷል። አንዳቸው ሳጥን ውስጥ ሲገኙ ሌላኛቸው ኳስ ከኋላ ተቀብለው የሚያመቻቹበት እና የሚናበቡበት ሒደት በትክክልም በደካማ የፊት መስመር ጥምረት ይተች የነበረው ሲዳማን የአስፈሪ የአጥቂ መስመር ባለቤት አድርጎታል። ኦኪኪ በአግቢነት እና በአቀባይነት ከተሳተፈባቸው አስር ጎሎች ውስጥም አምስቱ ከሲዲቤ ጋር የከወናቸው ነበሩ። “ከሲዲቤ ጋር በጅማም አብረን የመጫወቱ ዕድል ስለነበረን ሜዳ ላይ በደንብ እንግባባለን። ከልምምድ በኋላም በራሳችን እንሰራለን ለዛም ይመስለኛል ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር አለን።” ሲል የጥምረቱ ስኬት ምስጢርን አብራርቷል።
አሁን ለሲዳማ ቡና መልካም ጊዜ መጥቷል። አስፈሪ የነበረው የመውረድ ስጋት አልፎ በቀጣይ ዓመት ወደ ቀደመ ጠንካራ ተፎካካሪነቱ ለመመለስ ማሰብ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። በሁለቱ ዙሮች የተላያየ መልክን በያዘው የቡድኑ ጉዞ ውስጥ ያልነበረ አሁን ደግሞ ለውጤታማነታቸው ዋነኛ ምክንያት ስለሆነው ነገርም የኦኪኪ ሀሳብ “ጥሩ ህብረት አለን ሁሉንም ነገር እንደ ቤተሰብ ነው የምናደርገው። መጀመሪያ ውጤት እንዳይኖር ያደረገውም ያ ይመስለኛል። ከዛ በኋላ ብዙ ስብስባዎች አድርገናል። ያለን ግንኙነትም እየተሻሻለ ውጤቱም ጥሩ እየሆነ ሄዷል። ደጋፊዎቻችን በእኛ ላይ ስለነበራቸው ዕምነትም ማመስገን እፈልጋለሁ። ስለሰጡን ድጋፍ ሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል።”