ብሔራዊ ስታዲየምን የተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

የሁለተኛ ዙር ምዕራፍ ግንባታ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ ስታዲየምን የተመለከተ ጉብኝት እና ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ተከናውኗል።

በሀገራችን ትልቁ እና ዘመናዊው ብሔራዊ ስታዲየም በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ገርጂ አካባቢ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በመገባት ላይ ይገኛል። የግንባታው ባለቤት የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ከቻይናው ስቴትስ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ግንባታው ለማከናወን ውል አስሯል። የግንባታውን ጥራት ለመቆጣጠር ደግሞ ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ በማማከር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የስታዲየሙ የመጀመሪያ ዙር የግንባታ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ መጋቢት 14 ቀን 2012 ላይ የሁለተኛ ዙር ግንባታውን ለማስጀመር ከግንባታ ተቋራጩ ድርጅት ጋር የፊርማ ሥነ-ስርዓት ተካሂዶ ወደ ስራ እንደተገባም ይታወቃል። የመጨረሻው ምዕራፍ በ900 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ቢገለፅም በተለያዩ ምክንያቶች ስታዲየሙ በታሰበለት ጊዜ እየተገነባ አይገኝም። በዛሬው ዕለት ደግሞ የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ስታዲየሙ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለብዙሃን መገናኛ አባላት አስጎብኝቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

62 ሺ ተመልካች በወንበር የማስተናገድ አቅም ያለው ስታዲየሙ 7 ልዩ ልዩ የክብር እንግዶች ክፍል (VIP)፣ 2 የክብር እንግዶች ብቻ የሚጠቀሙበት ካፍቴሪያ፣ 2500 እንግዶችን በአንዴ ማስተናገድ የሚያስችል አዳራሽ፣ 200 ስፖርተኞችን መያዝ የሚያስችል የመታጠቢያ ክፍል፣ 2500 ተመልካች በአንዴ የሚያስተናግድ ካፌ እና ሬስቶራንት፣ 1000 ተመልካቾች የሚጠቀሙበት የመፀዳጃ ክፍሎች፣ 7 ትላልቅ የገበያ አዳራሾች፣ 620 በስታዲየም ዙርያ የሚገኙ ሱቆች፣ 2 ደረጃውን የጠበቀ ጂምናዚየም፣ 6 ደረጃቸውን የጠበቁ የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሎች እንዲሁም አንድ የቮሊቦል፣ የቅርጫት ኳስ፣ የባድሜንተን፣ የቴኒስ ሜዳ እና አንድ አምፊ ትያትር እንዲሁም የሰው ሰራሽ ሀይቅ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ከ4:30 ጀምሮ በነበረው የመስክ ጉብኝት ላይ በስታዲየሙ የግንባታ ሂደት ላይ ያን ያህል እድገት ባናይም ከዋናው ስታዲየም ዙርያ ያሉ መሠረተ ልማቶች ከፍታኛ ስራ እየተሰራባቸው እንደሆነ ታዝበናል። ለመጀመሪያው ዙር ምዕራፍ 2.47 ለሁለተኛው ዙር ምዕራፍ ደግሞ 5.57 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገለፀው ስታዲየሙ ለ30 ደቂቃዎች ያክል ከዙሪያው ያሉት ስራዎች እንዲታዩ ከተደረገ በኋላ በስብሰባው አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውንም የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር የሰጡ ሲሆን ኮሚሽነሩም ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ ስራዎችን ለመስራት አዳጋች መሆኑን አውስተው መንግሥት ግን በቁርጠኝነት የስታዲየሙን ግንባታ ለማገባደድ እየለፋ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ የስፖርት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተፅእኖ ውስጥ ገብቶ ነበር። ግን ከወረርሽኙ ጋርም ቢሆን ጥሩ ስራዎች ሲሰሩ ከርመው ስኬቶች መጥተዋል። ውድድሮችንም በኮቨድ-19 ፕሮቶኮል እንዲከናወኑ አድርገናል። ስልጠና እና ውድድሮች እንዲመለሱ ከማድረግ ጎን ለጎንም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በተደረጉ ውድድሮች ውጤት መጥቷል። ከዚህ ውጪ ዘንድሮ የታየው የስፖርታዊ ጨዋነትም ጥሩ ነው። ይሄ እንዳለ ሆኖ የስፖርት የስልጠና ማዕከላትን እና ማዘውተሪያ ቦታዎችን በተለየ ትኩረት ስንሰራ ነበር። የተጀመሩትንም ለማጠናቀቅ ሞክረናል። በተለይ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ስታዲየሞችን ለማስተካከል ስፖርት ኮሚሽናችን ጥረት አድርጓል። በአፋጣኝ ሥራ የሚፈልጉትንም ለይተን አውጥተን ክትትል እያደረግን ነው።

“ዛሬ የጎበኛችሁት ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፍ እንዲሰራ ሆኗል። እርግጥ የመጀመሪያው ዙር ምዕራፍ ቆይቶ ነው የተጠናቀቀው። ይሄ ዙር አልቆም የሁለተኛው ምዕራፍ ስራዎች ተጀምረዋል። ግን ስምምነቱን ልንፈፅም ስምል ኮቪድ መጣ። በዚህም ምክንያት መንጓተቶች ተከስተዋል። ግን ኮቪድ ቢመጣም እኛ ስራ አላቆምንም። በሽታው ኢ-ተገማች በመሆኑ እና ጊዜው ከተራዘመ የገበያው ዋጋ እንደሚጨምር ተረድተን ውሉን ይዘን ወደ ስራ ገብተናል። በዚህም ብዙ አትረፈናል።

“ውል ይዘን የመጨረሻውን ምዕራፍ ከጀመርን በኋላም ኮቪድ ተፅእኖ አድርጎብናል። ባለሙያዎች ከውጪ እንዳይመጡ ሆኗል፣ የሲሚንቶ ምርት እጥረት ችግር ተከስቷል እንዲሁም ለዚህ ዙር የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን በሚፈለገው መልኩ ያለማግኘት ችግር ነበር። ይሄ ሁሉ ቢኖርም ግን እኛ ስራችንን በጥሩ ትኩረት ስንሰራ ነበር። ሌላው እና ዋነኛው የተሰራው ስራ ስታዲየሙ አካባቢ የነበረውን ህገ-ወጥ ግንባታ የማቆም ስራ ነው። ይሄንንም ችግር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግረን እንዲፈታ አድርገናል። በዚህም የከተማውን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ማመስገን እንፈልጋለን። ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስታዲየሙ ጥራቱን ጠብቆ እየተገነባ መሆኑን ነው። በአሁኑ ሰዓት ጣራ ተሸካሚ ኮለኑ እያለቀ ነው። የጣራ ብረቶቹም ቻይና እየተመረቱ ነው። በአጠቃላይ ስታዲየሙ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በከፍተኛ ጥራት እየተገነባ ነው።” ብለዋል።