አምስት ግቦች ከተስተናገዱበት ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።
ገብረመድኅን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው?
በጨዋታው ብልጫ እንደሚኖረን አስቤ ነበር። በዚህ ጨዋታ ሁሉንም ነገር ማጠናቀቅ ነበረብን። ጎልም ያስፈልገን ነበር። ሲዳማ ያለፉትን አስር ጨዋተዎች ጥሩ አመጣት ነው የመጣው። ዛሬ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ምን እንደሚመስልም ማሳየት ነበር ፍላጎታችን። ይሄንንም ለማሳየት ጫና ፈጥረን መጫወት ነበረብን። ይህንንም አድርገናል።
ወደ ቡድኑ ከመጡ በኋላ ስላደረጉት መሻሻል?
ቡድኑ የተወሳሰቡ ብዙ ችግሮች ነበሩበት። ከተጫዋች ምልመላ ጅምሮ እስከ ዲሲፕሊን ድረስ እንዲሁም ከአጨዋወት መንገድ ጋርም ተያይዞ ችግሮች ነበሩበት። ይሄንን ወደ ራሴ መንገድ ለማምጣት ትንሽ ጊዜ ወስዶብኛል። ከድሬዳዋ ጀምሮ እስከ ዛሬው ጨዋታ ድረስ አስር ጨዋታ አድርገናል። በእነዚህ ጨዋታዎች ደግሞ 20 ነጥብ አግኝተናል። በአጠቃላይ የነበሩብን ችግሮች ትንሽ ይከብዱ ነበር ግን በጥሩ ሁኔታ ተወተነዋል።
ስለ ኦኪኪ አፎላቢ ብቃት?
ኦኪኪ በደንብ ጠቅሞናል። እንዲጠቅመንም ነው ያመጣሁት። የወረቀት ስራዎች ቶሎ ስላላለቁ ዘግየት ብሎ ነው የተቀላቀለን። ግን ተጫዋቹ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ዛሬም ሆነ ባለፉት ጨዋታዎች ያገባቸው ጎሎች ምስክሮች ናቸው። በአጠቃላይ ኦኪኪ አንድ ለአንድ ተጫዋቾችን የማሸነፍ አቅሙም በጣም ጥሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አጨራረሱም ጥሩ ነወ። ስለዚህ ቡድኑን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሟል።
በውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጫዋች ማን ነበር?
ሙሉ ዓመቱን እኔ አልነበርኩም። ባልነበርኩበት ሊግ ምርጫ ማድረግ አልችልም። ምርጫም አልመረጥኩም። ረዳቶቼ ናቸው ምርጫውን ያከናወኑትም። ብዙ የተከታተልኩት ነገር ስለሌለ መምረጥ ይከብደኛል። ግማሹን የውድድር ዓመት አልነበርኩም። ስለዚህ ኮከቡን መምረጥ አልችልም።
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር
ስለዘጠና ደቂቃው የቡድኑ እንቅስቃሴ?
ዛሬ በተቻለን መጠን አስራ ሁለተኝነታችንን ለማረጋገጥ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው በሜዳ ላይ የነበረን የመከላከል አደረጃጀት ግን ጥሩ አልነበረንምበዚህም ልምድ ያላቸውን የሲዳማ ቡና አጥቂዎችን መቆጣጠር አልቻልንም።በነበራቸው ብልጫ ተሸንፈን በመውጣታችን ውጤቱን በፀጋ እንቀበላለን።
የተመስገን ግብ ስትቆጠር ስለነበረው ስሜት?
ሁለት ለአንድ ከሆንን በኃላ በአንድ ደቂቃ ነበር ሶስተኛ ግብ የገባብን ሀያ ደቂቃዎች እየቀሩን ሶስተኛ ግብ ማስተናገዳችን ጨዋታውን መሉ ለሙሉ አበላሽቶብናል። ሶስተኛውን ሳናስተናግድ ተጨማሪ ደቂቃዎችን መቆየት ብንችል 2-2, 3-2 ልናሸንፍ የምንችልበት እድል ነበር።በቀረን አንድ ጨዋታ የተቻለንን አድርገን በጥሩ መልኩ ለማጠናቀቅ እንሞክራለን።
ስለውድድር ዘመኑ ምርጦቹ?
በእኔ ምርጫ አንደኛ ያሬድ ባዬ ነው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደግሞ አቡበከር ናስር እና ፍፁም ዓለሙ ናቸው።