ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ፋሲል ከነማ ቀድሞ የግሉ መሆኑን ያረጋገጠውን ዋንጫ የሚረከብበትን የነገ ረፋድ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ ከደረሰበትን ሽንፈት ለማገገም፣ አሁንም በጥንካሬው ላይ እንደሚገኝ ለማሳየት እና የዋንጫ ርክክብ መርሐ-ግብሩን በድል ለማሳጀብ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ የተሻለ ደረጃን ለመያዝ እና በሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የጀመሩትን የዘንድሮ የውድድር ዘመን በሁለት ተከታታይ ድሎች ለማጠናቀቅ ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይገመታል።

ከ19 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ግስጋሴ በኋላ በድሬዳዋ ከተማ የተረቱት ፋሲል ከነማዎች ሦስት ነጥብ ባስረከቡበት ጨዋታ ያሳዩት ብቃት እጅግ የወረደ ነበር። ዓመቱን ሙሉ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ድንቅ የነበረው ቡድኑም በየመጫወቻ ቦታው ተዳክሞ ታይቷል። እርግጥ በዓለም ላይም አሸናፊነታቸውን ቀድመው ያረጋገጡ ቡድኖች እንደዚህ አይነት የወረደ ብቃት ሲያስመለክቱ ይታያል። በድሬዳዋውም ጨዋታ ቡድኑ ላይ የታየው ይሄ ነው። በተለይ ደግሞ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሦስት ግቦችን አስተናግዶ የሚያቀው እና የሊጉ ምርጡ የተከላካይ ክፍል የሆነው የቡድኑ የኋላ መስመር ላይ የታዩ የቦታ አያያዝ፣ የትኩረት ማነስ እና የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያልተለመዱ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ ኳስ ከኋላ መስርቶ ለመውጣት የሚጥርበት መንገድ እጅግ በስህተቶች የተሞላ ነበር። ይህ ችግር ደግሞ ነገም የሚኖር ከሆነ ፈጣኖቹ የሀዋሳ ከተማ አጥቂዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በኋላ ነገ በርካታ ደጋፊዎቹን (2000 ደጋፊዎች) በሜዳ የሚያገኘው ፋሲል ከነማ ጥብቅ ቁርኙነት ከክለቡ ጋር ያላቸውን ደጋፊዎቹን ለማስፈንደቅ ታትሮ እንደሚጫወት ይታሰባል። በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና በመቀጠል የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ቡድኑ ነገ ከጎል ጋር ያለውን ግንኙነት እጅግ እንደሚያጠናክር ይገመታል። በዚህም ሙጂብ ቃሲም በተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ፣ ሽመክት ጉግሳ እና በረከት ደስታ ደግሞ በሁለቱ መስመሮች ላይ እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸው ከአጥቂ ጀርባ በሚገኘው ቦታ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለሀዋሳ እንደሚፈትኑ ይታሰባል።

ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ ለነገው ጨዋታ እየተዘጋጁ የሚገኙት ሀዋሳዎች በመቀመጫ ከተማቸው እያደረጉት የሚገኙትን ጨዋታ በጥሩ አፈፃፀም በመጨረስ የተሻለ ደረጃም ማግኘት እንደሚፈልጉ ይታመናል።
እርግጥ በወልቂጤው ጨዋታ ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ ጊዜ አልነበረውም። በተለይ ቡድኑ መስፍን ታፈሰ በተሰለፈበት የግራ መስመር ላይ ያጋደለ ጥቃት ለመሰንዘር ቢንቀሳቀስም ያን ያህል ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። ከዚህ ውጪ በጨዋታው በተከላካይ እና በአማካዮች መሐከል የነበረው መስተጋብር ቀዝቀዝ ብሎ ታይቷል። ከዚህም መነሻነት የወልቂጤ የአጥቂ አማካዮች እና የመስመር ተጫዋቾች በመስመሮች መሐከል እየገቡ በጎ ነገሮችን ለቡድናቸው ለማምጣት ሲጥሩ ነበር። ይሄ ሂደት ደግሞ በነገው ጨዋታ የሚደገም ከሆነ ቡድኑ ምህረት በማያውቁት የፋሲል ተጫዋቾች ሊቀጣ ይችላል።

በሽግግሮች ላይ ድንቅ የሆነው የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድኑ ነገም በእነዚህ ሁለት ወሳኝ እንቅስቃሴዎች ራሱን አዘጋጅቶ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። በተለይ ደግሞ ፍጥነት ያላቸውን የአጥቂ እና የመስመር ተጫዋቾች ለመጠቀም ከመከላከል ወደ ማጥቃት አደገኛ የሆነ ሽግግር ሊከውን ይችላል። ከዚህ ውጪ ታታሪዎቹ የቡድኑ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች የፋሲልን የኳስ ቅብብሎሽ ለማቋረጥ ተጭነው እንደሚጫወቱ ይታሰባል። አልፎ አልፎም የቆሙ ኳሶችን ለመጠቀም ዘለግ ያለ ቁመት ያላቸው የቡድኑ የተከላካይ እና የአማካኝ መስመር ተጫዋቾች ቡድኑ ከሚያገኛቸው የማዕዘን እና የቅጣት ምቶች ግብ ለማስቆጠር እንደሚታትሩ ይገመታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ከ2009 በኋላ ቡድኖቹ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሀዋሳ ከተማ 11 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል ከነማ ደግሞ 10 ኳሶችን ከመረብ ጋር አዋህዷል።

ያጋሩ