ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማን በማሸነፍ ለሁለተኝነት ያለውን ተስፋ አለምልሟል

በ25ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ በከሰዓቱ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አዳማ ከተማን በመርታት ነገ ከሚጫወተው ቡና ጋር ነጥቡን አስተካክሏል።

በአዳማ ከተማ በኩል በሰበታ ከተማ ከተሸነፈው ስብስባቸው የአምስት ተጫዋች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ጀሚል ያዕቆብ፣ ላሚን ኩማሬ፣ በላይ ዓባይነህ፣ ብሩክ መንገሻ እና ሰይፈ ዛኪር በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሲጀምሩ በአንፃሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን አማኑኤል ተርፉ እና ሳላዲን በርጊቾ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድልን አግኝተዋል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች በተለይ በመከላከሉ ወቅት የነበራቸውን ደካማ ትኩረት መነሻ ያደረጉ ሁለት ጎሎችን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ማስቆጠር ችለዋል።

የመጀመሪያ ግቡን ለማስተናገድ ብዙም ያልዘገየው ጨዋታው በ2ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታውን በቋሚነት የጀመረው ሰልሀዲን በርጌቾ ከራሳቸው የሜዳ ክልል በረጅም ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን የቅጣት ምት ኳስ ተጠቅሞ ሰልሀዲን ሰዒድ ቡድኑን መሪ ያደረገችን ግብ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
በተመሳሳይ በ13ኛው ደቂቃ እንዲሁ አቤል ያለው ያሻማውን የማዕዘን ምት ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አማኑኤል ተርፉ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑ ገና በጊዜ 2-0 እንዲመራ አስችሏል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ ፈጥነው ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ምንም እንኳን በአንድ አጋጣሚ በላይ ዓባይነህ ከርቀት ወደ ግብ ከላካት እና እንደምንም ባህሩ ነጋሽ ካዳነበት ኳስ ውጭ ተጠቃሽ ሙከራዎችን ማድረግ ባይችሉም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጨዋታውን በመቆጣጠር ወደ ፊት ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኤልያስ ማሞን ቀይረው ያስገቡት አዳማ ከተማዎች ይበልጥ መሀል ሜዳ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ማሳደግ ቢችሉም ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎችን ግን እንደመጀመሪያው ሁሉ ተቸግረው ተስተውሏል ። በሁለተኛው አጋማሽ በጭማሪ ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት እንዲሁም ላሚኑ ኩማሬ በጨዋታ ያደረጉት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስቀድመው የቤት ሥራቸውን እንደመጨረሻቸው በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄን አክለው በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ደግሞ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ያሰቡ ይመስል ነበር።

በዚህ ሒደት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአጋማሹን ሁለት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ሳልሀዲን ሰኢድ ከመስመር የተሻገለትን ኳስ ወደ ግቡ ሞክሮ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም ሀይደር ሸረፋ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሞክሮ ካማራ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው በፈረሰኞቹ የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 37 በማሳደግ ሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በማስተካከል ከነበሩበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ከፍ ማለት ሲችሉ መውረዱ አስቀድሞ ያረጋገጠው አዳማ ከተማ በ13 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።