ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው የ25ኛ ሳምንት የመዝጊያ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ሁለቱ የሸገር ክለቦችን በተከታታይ ያስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያገኙትን ድል በሌላኛው የመዲናችን ክለብ ለመድገም እና የሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁበትን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ጠንክረው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። ሦስት ነጥብ ካገኙ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከድል ጋር ለመታረቅ እና በእጃቸው ያለው የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎ ደረጃን አጥብቆ ለመቀጠል ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይታሰባል።

ከሜዳ ውጪ በነበሩ ችግሮች ያልተረጋጋ ዓመት እያሳለፈ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ዋና አሠልጣኙን እና ወሳኝ ተጫዋቾቹን (15) ካጣ በኋላ እያሳየ ያለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እጅግ ግሩም ነው። በተለይ ከ20 ዓመት በታች የሚገኙ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ከቀላቀለ በኋላ ከፍተኛ ፍላጎት እና መታተር ይታይበታል። በዋናነት ደግሞ ለመከላከል ቅድሚያ እየሰጠ ወደ ሜዳ የሚገባው ስብስቡ ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን እጅግ ምቾት የማይሰጥ ሆኗል። ከምንም በላይ በቁጥር በዝቶ በራሱ ሜዳ የሚከላከል፣ ወደ ጎንም ሆነ ወደ ፊት እጅግ ግጥግጥ ያለ እና አካላዊ ጉሽሚያዎችን የሚያዘወትር ቡድን እየሆነ መጥቷል። ከዚህም መነሻነት ነገም ቡድኑ በዚሁ የጨዋታ አስተሳሰብ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል።

ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ፍላጎት የሌለው ሀዲያ ነገም ከኳስ ጀርባ በመሆን የቡናን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማምከን እንደሚታትር እሙን ነው። ይህ ቢሆንም ግን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ሽግግር ስል ነበር። ይህንንም መነሻ በማድረግ ቡድኑ ነገም በዚህ ፈጣን እና ስል ሽግግር ተጋጣሚው (ቡና) ላይ አደጋ ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ ውጩ ተጫዋቾቹ ላይ የሚታየው የተጋይነት እና ያልሸነፍ ባይነት ስሜት በጎ ነገሮችን ይዞለት ሊመጣ ይችላል።

ከአራት የአቻ ውጤቶች በኋላ ነገ ወደ ሜዳ የሚገቡት የአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ተጫዋቾች በደረጃ ሰንጠረዡ ከስራቸው የሚገኙ ክለቦች ነጥብ ጣሉ እንጂ ለረጅም ጊዜ የተቀመጡበትን የ2ኛ ደረጃ ያጡ ነበር። ከሁለቱ ጨዋታዎች በፊትም የሊጉ ሦስተኛው ትንሽ ግብ ያስተናገደ ክለብ የነበረው ቡድኑ በሁለቱ ጨዋታዎች ብቻ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል። ይህ እየላላ የመጣው የኋላ መስመሩም ስህተቶችን እንደ ቡድንም ሆነ በተናጥል እያመስመለከተ ይገኛል። ነገም እነዚህ ክፍተቶች ካልታረሙ ቡድኑ በቀጥተኛ ተፎካካሪው (2ኛ ደረጃን ለመያዝ) ሊቀጣ ይችላል። ከምንም በላይ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲሸጋገር በተደራጀ መንገድ መሆን ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ ከኋላ በሚኖር የኳስ መስረታ ወቅት ተጫዋቾች ከስህተት መራቅ ይጠበቅባቸዋል።

የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (41) የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ነገም ተጋጣሚውን ተጭኖ በመጫወቱ ረገድ ብልጫ ሊኖረው ይችላል። ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚገመተውን ሀዲያ ሆሳዕናንም በኳስ ቁጥጥር እና ሙከራዎች ሊበልጠው እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ ደግሞ በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ በቁጥር በዝቶ በመገኘት ከግብ ጋር ለመገናኘት እንደሚጥር ይገመታል። ከዚህ ውጪ ጠጣሩን የሀዲያ የኋላ መስመር ለመዘርዘር የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ሊበረክቱ ይችላሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘንድሮ የውድድር ዘመን 27 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው አቡበከር ናስር የቡድኑ የጎል ማስቆጠሪያ ምንጭ ሊሆን ይችላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሁለቱን ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል። በአንዱ ግንኙነታቸው (ዘንድሮ) ደግሞ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።