ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ መጠናቀቁ ቃርቧል። ከመጨረሻው ሳምንት አስቀድሞ በተካሄደው የ25ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸውን ከለቦች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችንም በተከታይ መልኩ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 ዐፄዎቹ በመጨረሻም ዋንጫውን ከፍ አድርገዋል

በ22ኛ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ያለግብ መለያየትን ተከትሎ ከወልቂጤ ከተማ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ሳያደርጉ የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት ፋሲል ከነማዎች የቀናት ሽግሽግ በተደረገበት መርሐግብር በመጨረሻም በ25ኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ሺህ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተረክበዋል።

ፍፁም የተለየ የውድድር ዘመን ያሳለፉት ዐፄዎቹ በሊጉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባልተለመደ መልኩ ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት እየቀሩ የሊጉ አሸናፊ ለመሆን መብቃታቸው በራሱ ከተፎካካሪዎቻቸው አንፃር በምን ያህል ርቀት የተሻሉ እንደነበሩ ምስክር ነው። ባለፉት ዓመታት እስከመጨረሻው የጨዋታ ዕለት ይዘልቅ የነበረው የአሸናፊነት ፉክክር ከእግርኳሳዊ ፉክክሮች ባለፈ በርከት ላሉ ውዝግቦች እና የሴራ ንድፈ ሀሳብ ትንተናዎች በር የከፈቱ ነበሩ። ነገርግን ፋሲል ከነማ ቀሪ አንድ የጨዋታ ሳምንት እንኳን ቢቀር ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለው የአስራ ሶስት ነጥብ ልዩነት በራሱ አስደናቂ የውድድር ዘመን ያሳለፉት ፋሲል ከነማዎች ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ መካከል በእግርኳሳዊ መመዘኛ ስለመላቃቸው ምስክር ነው።

ዋንጫውን ባነሱበት የ25ኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሀዋሳን ሲገጥም አምስት ያክል ተቀዳሚ ተሰላፊ ተጫዋቾችን በወጣት ተጫዋቾች ተክቶ በቀረበበት እና ድንቅ የሜዳ ላይ ፉክክር ባስመለከተን ጨዋታ ዓለምብርሃን ይግዛው በመጀመሪያው አጋማሽ በሀዋሳ ተከላካዮች ስህተት የተገኘችውን ኳስ አስቆጥሮ ቡድኑ የሚሞሸርበትን ዕለት ይበልጥ ለማድመቅ ቢቃረብም የጨዋታው መጠናቀቂያ ሰከንዶች ላይ ወጣቱ ተከላካይ ሄኖክ ይትባረክ ኳስ በእጅ በመንካቱ ሀዋሳዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ብሩክ በየነ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የፋሲል ተጫዋቾቹ የደስታ ስሜት ላይ በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ እንዲል አስገድዷል።

በስተመጨረሻም ዐፄዎቹ ያለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት ህልማቸው የነበረው የፕሪምየር ሊጉን ዘውድ በዓመታት ያልተቋረጠ ቁርጠኝነት እና ጥረት በእጃቸው አስገብተዋል።

👉ሩቅ አልመው ቅርብ ያደሩት ሠራተኞቹ

በ2011 ክረምት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸውን ካረጋገጡ ወዲህ ድፍረት እና ብስለት በተሞላ አመራር ቡድኑን ወደፊት ለማራመድ የሚረዱ በርከት ያሉ እርምጃዎች ለመራመድ ሲውተረተር የሰነበተው ቡድኑ ሜዳ ላይ ግን በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ውጤት ርቆት በስተመጨረሻም ከሊጉ መውረዱ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ተረጋግጧል።

ከጅምሮ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ እንደሌሎች አዳጊ ክለቦች “የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኝ” ከመሾም ይልቅ በከፍተኛ ሊግ በወቅቱ በነበሩበት ምድብ ጠንካራ እና የራሱ መገለጫ የነበረው የተፎካካሪያቸው ኢኮሥኮ አሰልጣኝ የነበረቡት እና በከፍተኛ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ ያልነበራቸው ደግአረገ ይግዛውን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ማስገረማቸውን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቢቀርም በሩቅ ምስራቅ መቀመጫውን ካደረገው “ማፍሮ ስፖርት” ከተሰኘ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ስምምነት ያሰሩበት እንዲሁም በትልቁ የሚነሳው ክለቡ መቀመጫውን ባደረገበት ወልቂጤ ከተማ ከስታዲየማቸው ዙርያ በተረከቡት መሬት ለታዳጊዎች ስልጠና የሚሆን የእግርኳስ አካዳሚ አስገንብተው ማስመረቃቸው፣ በቅርቡም ቢሆን የቡድኑን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የቡድኑ አመራሮች ክለቡን ከኃላ ቀር አደረጃጀት በማላቀቅ ቡድኑን በአክሲዮን ማኅበር ለማዋቀር ሥራዎች መጀመራቸው እንዲሁ የቡድኑ አመራሮችን ለማድነቅ የሚያስገድድ እርምጃዎች ነበሩ።

የመጀመሪያ ተሳትፎን በፕሪምየር ሊጉ ባደረጉ በተሰረዘው የውድድር ዘመን በአስደናቂው የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ እየተመሩ ወድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ በሰንጠረዡ አጋማሽ ቢገኙም በተለይ ቡድኑ በሊጉ ምርጥ መከላከል ከነበራቸው ቡድኖች አንዱ ነበር። የዘንድሮው የውድድር ዘመን አስቀድሞ ቡድኑ የነበሩትን የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች በሙሉ ለቆ አሰልጣኙ መጫወት ለሚፈልጉት የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመውሰድ የሚረዱ ሀገር በቀል ተጫዋቾች በመሰብሰብ ከተሰረዘው የውድድር ዘመን ቡድኑ የተሻለ ጥራት ያለውን ቡድን አሰባስበው ወደ ውድድር መግባታቸው ይታወሳል።

ቡድኑ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በርከት ያሉ የአጥቂ አማካዮችን በመጀመሪያ ተመራጭነት በማሰለፍ የተሻለ እንቅስቃሴን በማድረግ በሊጉ ጥሩ አጀማመርን ማድረግ ችለው ነበር። ነገርግን በሁለተኛው ዙር በተወሰነ መልክ የቡድኑ ገራገር የሆነው ታክቲካዊ አቀራረብ ዋጋ ማስከፈል ጀምሯል፤ ኳስን ተቆጣጥሮ በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በዝቶ ለማጥቃት በሚያደርገው ጥረት የማጥቃት ሂደታቸው ስልነት ከማጓደሉ ጋር ተያይዞ ተጋጣሚዎች አድብተው በጥቂት የመልስ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጤት ሲወስዱባቸው ተስተውሏል።

በሒደት እየተንሸራተተ የመጣው ቡድን በስተመጨረሻ በብዙ አለመረጋጋቶች ውስጥ ሆኖ ከሊጉ የመውረዱ ነገር እርግጥ ሆኗል። ተራማጅ እና ደፋር አመራርን ያስመለከቱን ሠራተኞች ዋነኛ ፈተና የሚጀምረውም አሁን ይመስላል። የረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅዶችን ነድፎ ለመንቀሳቀስ ይሞክር የነበረው ቡድኑ አሁን ከፕሪምየር ሊጉ ተሰናበቷል። ታድያ ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የማይኖር ከሆነ የቡድኑ አመራሮች ከያዙት መልካም መንገድ ሳይወጡ ቡድኑን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ይመልሱት ይሆን አልያም በሌሎች ክለቦች እንደተስተዋለው ይህ ተነሳሽነት ከስሞ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ይቸገር ይሆን የሚለው ጉዳይ በትኩረት የሚጠበቅ ነው።

👉 ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በሊጉ ይሰነብታሉ

አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር አስቀድመው ከፕሪምየር ሊጉ መውረዳቸውን ተከትሎ ሌላኛውን ወራጅ ክለብ ላለመሆን ባለፉት የጨዋታ ሳምንታት በሲዳማ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ መካከል ከፍ ያለ ፉክክር ሲደረግ ቢሰነብትም በስተመጨረሻም ወልቂጤ ከተማዎች ከሊጉ የመውረዳቸው ነገር እርግጥ ሆኗል።

በሊጉ በመጨረሻም ቢሆን መትረፋቸውን ያረጋገጡት ድሬዳዋ ከተማም ሆነ ሲዳማ ቡና በተለይ የአሰልጣኝ ለውጦችን ካደረጉ ወዲህ በጉልህ በሚታይ መልክ በሜዳ ላይ ባለፉት የጨዋታ ሳምንታት እያሳዩ ከነበረው መሻሻል አንፃር በሊጉ መቆየታቸው የሚገባቸው ነው።

ድሬዳዋ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አራፊ የነበረ ቢሆንም አስቀድሞ ከሰሞኑ በሰበሰበው ነጥብ ታግዞ ወልቂጤ ከተማ በሰበታ ከተማ መሸነፉን ተከትሎ አስቀድሞ በሊጉ መሰንበታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።

በሊጉ ለመሰንበት አንድ ነጥብ ብቻ በቂያቸው መሆኑን አውቀው ጅማ አባጅፋርን የገጠሙት ሲዳማ ቡናዎች አራት ለአንድ በማሸነፍ በሊጉ መቆየታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።

በሊጉ መልካም አጀማመርን ማድረግ ያልቻሉት ሁለቱ ቡድኖች በተለይ በሁለተኛው ዙር ባሳዩት አስደናቂ መሻሻል ለከረሞው በሊጉ መቆየታቸውን በስተመጨረሻም አረጋግጠዋል። የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ፣ ላለመውረድ ተልዕኮው የሚሆኑ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የቡድኑን የስብስብ ጥራት ከፍ በማድረግ ሁለቱ ቡድኖች የፈፀሙት ተግባር ስኬታማ ሆኖ ታይቷል ማለት ይቻላል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና ወደ አፍሪካ መድረክ ለመመለስ ከጫፍ ደርሷል

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ለሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ለሥፍራው እየተፎካከረ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በመርታት ለሁለተኝነት ያለውን እድል አስፍቶ መውጣት ችሏል። በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን የሚገጥመው ቡድኑ ከጨዋታው አንድ ነጥብ የሚያገኝ ከሆነ ከ2004 በኃላ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አፍሪካ መድረክ የሚመልሰውን ውጤት የሚያስመዘግብ ይሆናል።

በሁለተኛው ዙር በተለይ በመጨረሻ ጨዋታዎች ለማሸነፍ ተቸግረው ተስተዋለ እንጂ የካሣዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና በንፅፅር ከፋሲል ከነማ ቀጥሎ የተሻለ ወጥ ብቃት ማሳየት የቻለው ቡድን ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። ታድያ በዚህ ውጣውረዶች በበዙበት የውድድር ዘመን በራሳቸው የጨዋታ መንገድ የተሻለ የውድድር ጊዜያትን ያሳለፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የውድድር ዘመናቸውን “በስኬት” ለማጀብ የመጨረሻውን የጨዋታ ሳምንት ይጠባበቃሉ።

በአሰልጣኙ መንገድ ቡድኑን ወደ ከፍታ ለመምራት የረጅም ጊዜያትን ውጥን የያዘው ቡድኑ አሰልጣኙ በመጀመሪያው መሉ የውድድር ዘመን ይህን የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎን ማሳካት ከቻለ በቀጣይ የውድድር ዘመናት የቡድኑ አመራሮች ይበልጥ ድጋፍ እንዲያደርጉለት የሚያስገድድ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የተሻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር ቀጥተኛ ተፎካካሪ በሆነው ሀዲያ ሆሳዕና ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተገዱት ፈረሰኞቹ የሁለተኝነት ስፍራን ይዘው ለማጠናቀቅ ያላቸው ተስፋ የደበዘዘ ቢመስልም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አዳማ ከተማን በመርታት በሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር በሂሳባዊ ስሌትም ቢሆን የሚያቆየውን ውጤት አስመዝግቧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ ለወትሮው ከሚጠበቅበት የተጫዋቾች አደራደር በተወሰነ መልኩ ለውጦችን በማድረግ ወደ 3-4-3 ለውጥ ያደረጉበት ነበር። በዚህም በተለይ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በበቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ይበልጥ ከመስመር መነሻቸውን በማድረግ ወደ ውስጥ እያጠቡ በመግባት ተሳትፎ እንዲያደርጉም ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለባዶ አዳማን በረታበት ጨዋታ ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩት ከቆሙ ኳሶች ሲሆን የመጀመሪያው ሳልሀዲን በርጌቾ በራሳቸው የግብ ክልል ከተገኘ የቅጣት ምት ከአዳማ ከተማ ተከላካዮች ጀርባ በጣለው ኳስ እንዲሁም ሁለተኛው ደግሞ አቤል ያለው ካሻማው የማዕዘን ምት የተገኙ ሲሆን ሳልሀዲን ሰዒድ እና አማኑኤል ተርፉ ደግሞ የግቦቹ ባለቤት ነበሩ።

ቀጥተኝነት ይበልጥ በተስተዋለበት የቡድኑ አጨዋወት አዲሱ የተጫዋቾች አደራደር ይበልጥ እየዳበረ የሚሄድ ከሆነ የቡድኑን የማጥቃት ሆነ የመከላከል ጨዋታ በማሳደግ ቡድን ሊያሻሽለው እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ጨዋታ ነበር።

ያጋሩ