ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረታችንን የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዓበይት አስተያየቶች የሦስተኛው ትኩረታችን ክፍል ናቸው።

👉 ባለውለታውን በክብር ያመሰገነው ሙሉጌታ ምኅረት

የወቅቱ የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ የሆነው የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ አማካይ ሙሉጌታ ምህረት በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድን ከፋሲል ከነማ ጋር ካደረገው ጨዋታ ጅማሮ አስቀድሞ ለቀድሞው አሰልጣኙ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ የሆኑት አሰልጣኝ ከማል አህመድን በክብር አመስግኗል።

በ1996 ሀዋሳ ከተማ የአዲስ አበባ ክለቦች ተፅዕኖ የጎላበት የነበረውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ቡድን ሆኖ ሀዋሳ ከተማ ዋንጫውን ሲያነሳ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ከማል አህመድ ከሊጉ ዋንጫ ባለፈ ሙሉጌታ ምህረት እና አዳነ ግርማን ጨምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖን ማሳረፍ የቻሉ ታዳጊዎች ማፍራት ችለዋል።

እኚሁ ግለሰብ አሁን ድረስ ከእግርኳሱ ሳይለዩ በሀዋሳ እና በሌሎች የደቡብ ክልል ከተሞች አሁንም ድረስ ታዳጊዎችን ለማፍራት የእግርኳስ አካዳሚን ከፍተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ታድያ እኚህን አሁን ድረስ ለሀገራቸው በሙያቸው ያላቸውን እየሰጡ የሚገኙት እና የተዘነጉት የእግርኳሳችንን ጀግና አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በይፋ ከወገቡ ጎንበስ ብሎ ያመሰገነበት እና ታሪካዊው የ1996 የሀዋሳ ከተማ ስብስብን የሚያሳይ ምስል በስጦታ መልክ ያበረከተበት አጋጣሚ የሳምንቱ ልዩ ክስተት ነበር።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሀሳቡን ለሱፐር ስፖርት የሰጠው ሙሉጌታ ምህረት ስላበረከተው ማስታወሻ ይህንን ብሏል።

“ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ ከልጅነቴ ጀምሮ አሁን እስካለሁበት ጊዜ ድረስ መሰረቴ እሳቸው ስለሆኑ ነው። አጋጣሚውም አብሮ ሄዶልኛል፤ ቡድናችን ሁለት ጊዜ ቻምፒዮን ሲሆን ከእሳቸው ጋር ነው። ዛሬም ፋሲል ቻምፒዮን ሲሆን በውቧ ከተማ ላይ ስለሆነ ነው። ለእሳቸው ያለኝን ክብር ለመግለፅ ነው። እኔን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እነ ዘውዱ በቀለ ፣ ገረሱ ፣ አፈወርቅ ፣ ሹሬ ፣ አዳነ ፣ ሽመልስ ፣ በኃይሉ በጣም ብዙ ተጫዋቾችን ያፈሩ ናቸው። እና በእኔ አቅም በዚህ መድረክ ላይ ከእሳቸው ጋር ለመገናኘት ፈልጌ ነው።”

👉 በጫና ውስጥ ሆነው ቡድኑን ባለድል ያደረጉት ሥዩም ከበደ

ገና ከሹመታቸው አንስቶ በቀደሙት ክለቦቹ ያስመዘገባቸው መጥፎ ውጤቶች እየተመዘዙ ሹመቱን ጥያቄ ውስጥ ለመክተት የሞከሩ ብዙዎች ናቸው። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድን በተለይ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፉበት ጨዋታ በኃላ በነበሩ ቀናት አሰልጣኙ ከፍ ያለ ተቃውሞን ከየአቅጣጫው አስተናግደዋል። ነገርግን በዚህ ሒደት ውስጥ እጅ ሳይሰጡ አሰልጣኝ ሥዩም በስተመጨረሻ ፋሲል ከነማን ከሚያልመው የሊጉ ዋንጫ ጋር አገናኝተዋል።

ይሰነዘሩ የነበሩ ትችቶችን ተገቢነት ወደ ጎን ትተን አሰልጣኙ ፋሲል ከነማን በሚያህል ከፍተኛ የደጋፊዎች ፍላጎት ባለበት ክለብ በመሰል ከፍተኛ ጫናዎች ውስጥ ሆኖ ለዚህ ክብር መብቃታቸው ከምንም በላይ ክብር ይገባቸዋል። አሰልጣኙ በትችቶች ሳይንበረከክ ትኩረቱን ቡድኑ ላይ ብቻ በማድረግ የተንገራገጨ አጀማመር ያደረገውን ቡድን በሒደት በማስተካከል ወደ ክብር መርተውታል።

ለሊጉ ክብር አዲስ ያልሆኑት አሰልጣኙ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ የኢትዮጵያ ዋንጫን እንዲሁም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በማንሳት በኢትዮጵያ እግርኳስ መዝገብ ላይ ስማቸውን በወርቅ ካፃፉ አሰልጣኞች አንዱ መሆን ችለዋል።

👉 ቡድኖቻቸውን አሻሽለው በሊጉ ያቆዩት አሰልጣኞች

በእግርኳስ የአሰልጣኞች ለውጥን ተከትሎ ቡድኖች አዎንታዊ የውጤት መነቃቃት ማሳየታቸው የተለመደ ጉዳይ ነው። በዚህ ሒደት ይህን ጊዜያዊ የሚመስልን መነቃቃት በቀጣይነት ማስቀጠል መቻሉ የአዳዲሶቹ አሰልጣኞች ዋነኛ ፈተና መሆኑ ሳይዘነጋ ማለት ነው።

የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ድሬዳዋ እና ሲዳማ ቡና ፍፁም በተለያየ መንገድ ውስጥ ሆነው ነበር የጀመሩት። ድሬዳዋ ከተማዎች ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የሚያሳይ፤ ነገር ግን የግብ እድሎችን አብዝቶ በማምከኑ ከጨዋታዎች ውጤት ይዞ ለመውጣት የተቸገረ ቡድን ሲሆን በአንፃሩ አዲስ ግደይን ብቻ ያጣው ሲዳማ ቡና በሁሉም ረገድ ፍፁም የተዳከመ ቡድን ሆነው ነበር ሊጉን የጀመሩት።

በዚህ ደስተኛ ያልሆኑት የየክለቦቹ አመራሮች በውድድር አጋማሽ አካባቢ የአሰልጣኝ ለውጥ ለማድረግ ተገደዋል። በዚህም ድሬዳዋ ከተማዎች በአሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ምትክ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ሲቀጥሩ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ዓመታት ድንቅ ጊዜያትን አብሯቸው ባሳለፈው ዘርዓይ ሙሉ ምትክ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሁለት የውድድር ዘመናት አሸናፊ በነበሩት ገብረመድኅን ኃይሌ ተክተዋል።

ሁለቱም አሰልጣኞች አዲሱን ሥራቸውን ሲጀምሩ በተወሰነ መልኩ ተቸግረው ነበር። ነገርግን በተለይ በሁለተኛው ዙር ውድድር ከተጀመረ ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች በሚታይ ደረጃ መሻሻሎችን ማሳየት ጀምረዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን በተለይ በሁለተኛው ዙር ወደ ስብስባቸው በቀላቀሏቸው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ እና ግብጠባቂው ፋቢያን ፋርኖሌ ዝውውር ታግዘው ቡድኑን ሌላ መልክ አላብሰውታል። በሁለተኛው ዙር የነበረውን የሲዳማ ቡናን እንቅስቃሴ ለተመለከተ ቡድኑ በሰንጠረዡ አናት የሚፎካከር እንጂ ላለመውረድ የሚታትር ቡድን ፍፁም አይመስልም። ሌላው በመሰረታዊ የሚጠቀሰው የተሻሻለው ጉዳይ ቡድኑ ቀድሞ ይታወቅበት የነበረውን የመልሶ ማጥቃት አስፈሪነት ዳግም እንዲያገኝ ብሎም የራስ መተማመናቸው ወርዶ የነበረውን የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎችን ማሻሻል መቻላቸው ቡድኑን በሊጉ እንዲቆይ አስችሏል።

በተቃራኒው ውስን ዝውውሮችን የፈፀሙት እና ከዳንኤል ኃይሉ እና ዐወት ገብረሚካኤል ውጭ የሚጠቀስ ይህ ነው የሚባል ወደ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ሰብሮ መግባት የቻለ ተጫዋች ማዘዋወር ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአጠቃላይ አጨዋወታቸው ላይ በሒደት ግልፅ መሻሻሎችን አሳይተዋል። በጀብደኝነት በተጋጣሚ አጋማሽ ኳስን ለመንጠቅ የሚሞክረው ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ከግብ ፊት አሁንም ስል መሆን ባይችሉም ከተለያዩ ተጫዋቾች ግቦችን በወሳኝ ሰዓት ማግኘት በመቻላቸው በሊጉ ለመትረፍ በቅተዋል።

በሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመሰንበታቸው የሁለቱ አዳዲስ አሰልጣኞች ሚና ላቅ ያለ ነበር ። በቀጣይ ዓመት አሰልጣኞቹ በቡድኖቹ የሚቆዩ ከሆነ ዘንድሮው ያሳዩትን መሻሻል በቀጣይ በምን ያክል መጠን ጠንካራ ቡድን ወደ መገንባት አሸጋግረውት እንመለከታለን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉ዓበይት አስተያየቶች

*ሥዩም ከበደ ስለዓመቱ ውጣ ውረዶች እና በልዩነት ስለሚነሱ ተጫዋቾች

“ሥልጠና ዓለም ላይ ከባድ ከሚባሉ ሥራዎች አንዱ ነው። አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር ከፍታ እና ዝቅታ ነበረው። በዛ መካከል ውስን ደጋፊዎች ያደርጉት የነበረው ጫና ለሥራችን ብዙ እንቅፋት ነበረው። ያን ተወጥተን ግን ዛሬ ላይ ደርሻለሁ። በዚህ አጋጣሚ በጣም የደገፋችሁኝም የተቃወማችሁኝም አሁን አንድ ላይ ለፋሲል ሁላችንም የታሪክ ባላደራ ስለሆንን ሁላችሀንም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ”

“ሁሉም በዓመቱ ያሳዩት ብቃት ደስ የሚል ቢሆንም በተለይ አምበሎቻችን እነ ያሬድ እነ ሳኛ ዓይነቶቹ ቡድኑን በማያያዝ በማፋቀር እኛ ጋር ሳይደርስ ነገሮችን እየያዙ ለቡድኑ መንፈስ የከፈሉት ዋጋ በጣም ትልቅ ነው። የእነዚህ ድምር ውጤት ሁሉ ለቡድኑ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል ብዬ አስባለሁ።”

*አብርሃም መብራቱ የተጋጣሚያቸው ወቅታዊ ሁኔታን ሳይመለከት ቡድን ስለመጫወቱ

“በትክክል ወልቂጤ ላለመውረድ ነው የሚጫወተው ግን ለእና 12ቱም የሊጉ ቡድኖች እኩል ናቸው ፤ የእግርኳስ ሙያው የሚፈቅደው አቅምህ የፈቀደውን በሙሉ ሜዳ ላይ አድርገህ የተገኘውን ውጤት በፀጋ መቀበል ነው።ዛሬ በነበረን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተሸንፈን ከሜዳ ብንወጣ እንኳን ወልቂጤን እንኳን ደስ አላችሁ ብዬ ተጫዋቾች አመሰግን ነበር ፤ እንደትምህርት ሊወሰድ የሚገባው ነገር ለሁሉም ቡድኖች እኩል ግምት ሰጥቶ ለማሸነፍ መንቀሳቀስ ከሁሉም ክለቦች ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ።”

*ዘላለም ሽፈራው ስለቸርነት ጉግሳ ብቃት?

“ቸርነት ለእኔ ቡድን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው። ቸርነት የመስመር ተጫዋች እንደሆነ ይታወቃል። ከፍተኛ ኳስ የመግፋት ብቃት፣ ግብ የማስቆጠር ችሎታ እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን የማቀበል ብቃት አለው። በእኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ ከአንድ የመስመር ተጫዋች ከሚገባው በላይ ነው። ስለዚህ ቸርነት እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ እና ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው። ነገርግን አሁንም በርትቶ መስራት አለበት። አሁን ያለውን ውዳሴ መውሰድ ብቻ ሳይሆን በደንብ መስራት ያስፈልገዋል።”

*ፋሲል ተካልኝ በውድድር ዘመኑ ቡድኑ ላይ ስለነበረ ክፍተት?

“ድሬዳዋ ላይ በተከታታይ ነጥብ ጥለን ወደ ሀዋሳ ስንመጣ ከዛ ችግር ቶሎ አለመውጣታችን ትልቁ ክፍተታችን ነበር። እርግጥ በየጨዋታው የአቅማችንን ሞክረናል። ጨዋታዎችንም የምናሸንፍባቸውን ዕድሎችም ሁል ጊዜ ሜዳ ላይ እናገኛለን። እነዛን ግን አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል። ብዙ ጨዋታዎች ከእኛ አቅም በላይ አልነበሩም። እኛ እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግለሰብ የምንሰራቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍሎናል።”

*ካሣዬ አራጌ በተከላካይ መስመር ያሉ ስህተቶች እየተቀረፉ ስለመሆኑ

ጨዋታው ራሱ ስህተቶችን በቀላሉ ለማየት ዕድል የሚሰጥ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስህተቶቹ ጎልተው የሚነገሩት ጨዋታው ራሱ ስህተቶችን በቀላሉ ለማየት የሚጋብዝ በመሆኑ ነው፤ ያ ታሳቢ መሆን አለበት። ለምሳሌ የመጀመሪያው ጎል ሲገባብን የእኛው ካስ ነበር፤ አማኑኤል ኳስ ለመቆጣጠር ሲሞክር ከእግሩ አምልጦት ነው። ያው በምንጫወትበት ጊዜ መክፈት ግድ ነው። የኳስ ባለቤት ስለሆነ በዛ አጋጣሚ የተገኘ ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ሁሌም የምንለው የትኛውም ቦታ ላይ ያለ ተጫዋች ቦታውን እንዲያጠብ ነው። እና ላይ ትንሽ ዝግ የማለት ነገር ነበር ። ብዙ በከፈትናቸው ክፍተቶች ያን ያህል ተጠቃሚ ነበሩ ብዬ አላስብም።

*ገብረመድኅን ኃይሌ ወደ ቡድኑ ከመጡ በኋላ ስላደረጉት መሻሻል?

“ቡድኑ የተወሳሰቡ ብዙ ችግሮች ነበሩበት። ከተጫዋች ምልመላ ጅምሮ እስከ ዲሲፕሊን ድረስ እንዲሁም ከአጨዋወት መንገድ ጋርም ተያይዞ ችግሮች ነበሩበት። ይሄንን ወደ ራሴ መንገድ ለማምጣት ትንሽ ጊዜ ወስዶብኛል። ከድሬዳዋ ጀምሮ እስከ ዛሬው ጨዋታ ድረስ አስር ጨዋታ አድርገናል። በእነዚህ ጨዋታዎች ደግሞ 20 ነጥብ አግኝተናል። በአጠቃላይ የነበሩብን ችግሮች ትንሽ ይከብዱ ነበር ግን በጥሩ ሁኔታ ተወተነዋል።”