ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በ25ኛው የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የመጨረሻው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 የደጋፊዎች መመለስ

በ25ኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት እና ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት ዐፄዎቹ በይፋ ዋንጫውን በተረከቡበት የጨዋታ መርሐግብር በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ቡድናቸውን የተመለከቱበት ጨዋታ ነበር። ለረጅም ወራት በአጠቃላይ እግርኳሱ ናፍቋቸው የነበሩት ደጋፊዎች በሜዳ መገኘታቸውም ታሪካዊውን ጨዋታ የተለየ መልክ አላብሶት ነበር።

የዘንድሮው ውድድር እስከ ድሬዳዋው ውድድር የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ድረስ ውስን ቁጥር ያላቸው የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ ፍቃድ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም በሀገራችን ዳግም ስርጭቱ እያገረሸ በሚገኘው የኮቪድ ስርጭት ምክንያት ደጋፊዎች ሙሉ ለሙሉ እንዳይገቡ መታገዳቸው ይታወሳል። ታድያ ይህ የጨዋታዎችን መንፈስ ከፍ ባለ ደረጃ እንደጎዳ ያለፉት ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ምስክር ነበሩ።

አሁንም ቢሆን ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየሞች ለመመለስ ጊዜው ገና ቢሄንም የደጋፊዎች በሜዳ መገኘት ግን በጨዋታዎች አጠቃላይ የፉክክር ደረጃ ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ የፋሲል እና የሀዋሳ ጨዋታ በቂ ማሳያ ነው።

👉 ግርግር የበዛበት የዋንጫ አሰጣጥ ሥነስርዓት

ፕሪምየር ሊጉ ከፌደሬሽኑ ተላቆ በአክሲዮን ማኀበር መተዳደር ከጀመረ አንስቶ ይህ የመጀመሪያ ሙሉ የውድድር ዘመን እንደመሆኑ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም አክሲዮን ማኅበሩ ግን ከሚጠበቅበት በላይ እየሠራ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

በቀደሙት ዓመታት የሊጉ መገለጫ የነበሩትን በኋላ ቀር እሳቤዎችን እና አሰራሮችን በማስወገድ በንፅፅር ከቅሬታ የፀዳ የሚባል የውድድር ጊዜን ማሳለፍ ተችሏል። ታድያ ይህን የመዝጊያ መርሃግብር ለማድመቅ የዋንጫውን ይዘት ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መቆየታቸው በተደጋጋሚ ሲገለፁ አድምጠናል። ፋሲል ከነማ ዋንጫውን በተረከበበት የቅዳሜ ረፋዱ መርሃግብር ላይ ግን በተወሰነ መልኩ ከቀደሙት ጊዜያት የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም ለዕይታ ምቾት የማይሰጡ ነገሮችን ተመልክተናል።

በቅድሚያ በደቡብ አፍሪካ እንደ አዲስ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጾ የነበረው የሊጉ ዋንጫ አስቀድሞ ይደርሳል ከተባለበት ጊዜ እንኳን በርካታ ቀናት ተቆጥረው ዋንጫው ለቅዳሜው መርሃግብር ሊደርስ ባለመቻሉ ፋሲል ከነማዎች ጊዜያዊ ዋንጫ እንዲወስዱ የተደረገበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ነው። እርግጥ በጉዳዩ ላይ የነበሩት ሒደቶች በግልፅ ቢታወቁ ሊግ ካምፓኒው አልያም ዋንጫውን ለመሥራት የተስማማው አካልን ተጠያቂ ለማድረግ አመቺ ቢሆንም በአጠቃላይ በተባለው ቀን አለመድረሱ እንደ ድክመት የሚቆጠር ነው።

ሌላው በፕሮግራሙ ላይ የተመለከትነው ክፍተት በተዘጋጀው ጊዜያዊ መድረክ ላይ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የክብር እንግዶች ሜዳልያ ለመስጠት ቢደረደሩም የፋሲል ከነማ የቡድን አባላት ወደ በመድረኩ ሜዳሊያ እየተቀበሉ እንዲያልፉ የተደረገበት መንገድ ትክክለኛ ባለመሆኑ የክብር እንግዶቹ በእጃቸው የያዙት ሜዳሊያ ለመስጠት ከፋሲል ከነማ የቡድን አባላትን ውስጥ ሜዳሊያ ያላጠለቀውን ዝብርቅርቅ ባለ መልኩ በተናጥል በድንገት እየጠሩ የሰጡበት መንገድ መታረም የሚገባው ነው።

በተመሳሳይ ይህን ሁነት ለመዘገብ በስፍራው የተገኙ በርከት ያሉ የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን ስርዓት ባለው መልኩ መቆጣጠር ባለመቻሉ ሒደቱን በፎቶ ለማስቀረት ትርምሶች አስተውለናል። ይህም ለባለሙያዎቹ አመርቂ የሆኑ ምስሎችን እንዳያገኙ ከማስቻል ባለፈ በአጠቃላይ ይህን ታሪካዊ ዕለት ሰንዶ በማስቀመጥ ረገድ ክፍተቶችን ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል።

በአጠቃላይ አክሲዮን ማኀበሩ መሰል ሁነቶችን የማስተናገድ በቂ ልምድ እና አቅም አለማዳበራቸው ለመሰል ክፍተቶች ምክንያት መሆኑ ቢታመንም በዚህ ሥራ በቂ ልምድ ያላቸው ድርጅቶችን አወዳድሮ በመቅጠር ሁነቱን ይበልጥ የተሻለ ለማድረግ ሊሠራ ይገባል።

👉 የስሞች አፃፃፍ ጉዳይ

ለዘመናት የሀገራችን እግርኳስ የናፈቀው የጨዋታዎች ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ዘንድሮ በደቡብ አፍሪካ መቀመጫውን ባደረገው ግዙፉ የቴሌቪዥን ስርጭት ተቋም በሆነው በዲኤስቲቪ ዘንድሮ ተሳክቷል። መሳካት ብቻ ሳይሆን በላቀ የፕሮዳክሽን ጥራት ለሀገራችን እግርኳስ አዲስ ገፅታን እያላበሰ ይገኛል።

የመጀመሪያ የውድድር ዘመን እንደመሆኑ ብዙ ክፍተቶች ይኖራሉ ተብሎ ቢጠበቅም በውጭያዊ ምክንያቶች ከተፈጠሩ የተወሰነ ክፍተቶች ውጭ ይህ ቀረሽ የማይባል የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ስርጭት ተመልከተናል። ነገር ግን አንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች ስርጭቱ ላይ በተወሰነ መልኩ እንደ እንከን ሆነው ተመልክተናል።

በዋነኝነት ለማንሳት የወደድነው ጉዳይ በጨዋታ ወቅት በምንመለከታቸው የቡድን ስብስብ ማሳወቂያ ምስሎች እና በተለያዩ ሁኔታ ጥቅም ላይ በሚውሉ የተጫዋቾች ስም መግለጫዎች ላይ በስፋት የሚስተዋለው የተጫዋቾች የስም አፃፃፍ ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው የስህተቱ ምንጭ ማን እንደሆነ ለመለየት ቢያስቸግርም በቀጣዩ የውድድር ዘመን በትኩረት ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ለመጠቆም እንደወዳለን።

ስሞች በተለያዩ መንገድ ለመፃፍ ክፍት የመሆናቸው ጉዳይ ነገሩን ውስብስብ ቢያደርገውም የተቋሙ ሰዎች በቀጥታ ከየቡድኖቹ ስብስብ አባላት ትክክለኛውን የስማቸውን አፃፃፍ መንገድ ሊያገኙበት የሚችለውን መንገድ በማመቻቸት እንዲሁም ለቋንቋው ቅርብ የሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች በአርትኦት ሥራው ላይ ተሳታፊ በማድረግ በተሻለ ስህተቶችን የቀነሰ ሂደት መፍጠር ይቻላል።

ሌላው በእንግሊዝኛው የጨዋታ አስተላላፊነት የተመደቡ ባለሙያዎች የተጫዋቾችን ስም ሲጠሩ በሌላው ዓለም በተለመደው መልኩ በቤተሰብ ስም (Surname) የመጥራት ዝንባሌ ከሀገራችን የግለሰቡን፤ አስከትሎ ደግሞ የአባት ስምን ከመጥራት ባህል ጋር ሲጣጣም አልተመከትንም። በስክሪን ላይ በሚታዩ መረጃዎች ላይም ከተጫዋቹ ስም ይልቅ የአባቱን ስም ጎላ (Bold) ተደርጎ ሲፃፍ ይስተዋላል። ይህ የጨዋታ አስተላላፊዎቹ ስህተት ባይሆንም፤ ይህ መደረጉም ያን ያህል በሥራው ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር ባይሆንም የሚመለከታቸው አካላት በቀጣይ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ ላይ ማስተካከያ ቢያደርጉ ተመራጭ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው የስም አጠራር ጉዳይ ላይ ማስተካከያ ማድረግ በዓለማችን ላይ የተለየ የስም አጠራር ባህል ካላቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ይህ የተለየ መልኳን የማስተዋወቂያ አንድ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

👉 የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች

የውድድሩን የመጨረሻ ምዕራፍ እያስተናገደ በሚገኘው የሀዋሳ ከተማ መቀመጫውን ያደረገው ሲዳማ ቡና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የሊጉን ቆይታውን ያረጋገጠበትን ወሳኝ ድልን ጅማ አባ ጅፋር ላይ ተቀዳጅቷል።

ታድያ ይህን ለቡድናቸው በውድድር ዘመኑ ወሳኝ ከነበሩ ጨዋታዎች በዋነኝነት የሚሰለፈውን ግጥሚያ ለማየት ወደ ስታዲየም መግባት የቻሉት ውስጥ ገብተው ቡድናቸውን አበረታተዋል። የተቀሩት እና ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የክለቡ ደጋፊዎች በስታዲየሙ አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ ሁለት በሮች ላይ ሆነው መገለጫቸው የሆነው ክለብ ይህን ወሳኝ ድል ሲያሳካ በቻሉት መጠን በዓይናቸው ለመመልከት ጥረት ሲያደርጉ መስተዋሉ የሳምንቱ ትኩረት ሳቡ ጉዳይ ነበር።