ከዕለቱ የመጀመሪያው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
በወጣት ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለመሆናቸው
እጅግ በጣም !
በዓመቱ ወጣቶችን ስለመጠቀማቸው
ወጣቶች ላይ በመስራት ብዙ ልዩነቶች ይፈጠራሉ። ለአንድ ዓመት ብቻ ዕቅድ ይዘህ የምትነሳ ከሆነ ይከብዳል። ለሦስት አራት ዓመት አብረህ ብትሰራ የተሳካ ጊዜ ይኖርሀል። ያው በአካባቢው በሀዋሳም ብዙ ወጣቶች ስላሉ መጀመሪያ አስቤው ነበር። ግን ያው የሊጉ ውድድር አካሄድ በአንድ ከተማ ላይ በመሆኑ ትንሽ እርግጠኛ ባለመሆን ነው እንጂ አሁን ዘንድሮ ባሳዩት እንቅስቃሴ እና ባለንበት ደረጃ እጅግ በጣም ደስተኞች ነን ሁላችንም።
በቀጣይ ዓመት የውጪ ግብ ጠባቂዎችን ስለመጠቀም
እኔ የማስበው እንደ ሀገር ነው። ለሀገር የሚበጀውን ነገር ማድረግ ነው የመጀመሪያው አላማዬ። ደጋግሜ በረኞቼንም የማየው ቀጣይ ዓመታት ላይ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ግብ ጠባቂዎች ለማሰራት ነው። ሊበራታቱ እና ሊደገፉ ይገባል። እኔም በዚሁ ሀሳብ እጓዛለሁ።
ወንድምአገኝ ኃይሉ በሀዋሳ በዓመቱ የተለየ ተጫዋች ስለመሆኑ
ምን ጥያቄ አለው ? ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ መልስ የሚሆን ነው። ብዙ ወጣቶች አሉ እሱ ግን እንደመጀመሪያ ዓመት የተለየ ነበር።
አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለጨዋታው
ጥሩ ነበር ፤ ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል። ቅድም እንዳልኩት አዳዲስ ወጣቶችን ለማየት ፈልገናል። ከጨዋታው የሚገባውን አግኝተናል ብዬ አስባለሁ። አሁን ትኩረት ማድረግ ያለብን በቀጣይ ዓመት የተለየውን ድሬዳዋ ይዞ መቅረብ ላይ ነው።
የውጪ ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾች ቀጣይ የቡድኑ ዕቅድ ስለመሆናቸው
እኔ ግማሽ ላይ ነው የገባሁት ፤ እዛው ነው ያገኘኋቸው። በቀጣይ ምን መስራት አለብን በሚል ዕቅዶችን ለክለቡ አቅርበናል። በዛ መሰረት ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት የነበረውን ድሬዳዋ ሳይሆን የተሻለውን ድሬዳዋ ይዘን ለመምጣት ጥረት እናደርጋለን።
ስለሀዋሳ ቆይታቸው
እኛ ደስተኛ ነን። በቀደም ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ሲያነሳ እና እኛ በሊጉ ስንቆይ ተቀራራቢ ስሜት ይዘን ነው የሄድነው። እንደ ገደኛ ከተማ ነው የምናያት ሀዋሳን። ስለዚህ እዚህ በነበረን ቆይታ ስኬታማ ነበርን ብለን እናስባለን።
ስለቀጣይ ዓመት ውድድር
በዘንድሮውም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ነገር እያየን ነው። ተገደህ ኳሱ ላይ ተዘጋጅተህ እንድትመጣ ያደርግሀል። ምክንያቱም ዓለም ነው እግር ኳሱን እያየው ያለው። የጨዋታ ዕቅዳችን ላይ እንድናተኩር አድርጓል። ይሄ ጅምር ነው። በቀጣይ ዓመታት ግን ከዚህ የተሻለ ነበር።