ቅድመ ዳሰሳ | የ25ኛ ሳምንት የረቡዕ ጨዋታዎች

ከሊጉ የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ላይ የሚከወኑትን ሁለት ጨዋታዎች እንዲህ ዳሰናቸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ይህ ጨዋታ ለመርሐ ግብር ማሟያ ከሚደረጉ የ 26ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ የሚካተት ነው። እርግጥ ነው ሀዋሳ ከተማ የግብ ልዩነቱንም በነገው ጨዋታ ማሻሻል ከቻለ እስከ አምስተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል ያለው ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ አሁን የሚገኝበት የዘጠነኛ ደረጃን አሳልፎ ሳይሰጥ ለመጨረስ የጨዋታውን ነጥቦች ማግኘት ይኖርበታል።

ከድል ከራቀ ሦስት ጨዋታዎች ያለፉት ሀዋሳ ከተማ ዓመቱን በድል ከማገባደድ በላይ እምብዛም ዕድል ላላገኙ ወጣት ተጫዋቾቹን መጠቅምን ምርጫው ሊያደርግ ይችላል። ቡድኑ እስካሁን አመዛኙን ወጣቶች አብዝቶ ከመጠቀሙ አንፃር በመዝጊያው ዕለት ተመሳሳይ አካሄድን ቢከተል አስገራሚ አይሆንም። ከዚህ በተለየ እስትንፋሱ እንዲቀጥል በረዱት የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላገኘው ድሬዳዋ ከተማ ይህንን የመጨረሻ ሰዓት መልካም ጉዞ ሳይለቅ ለመጨረስ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያለው ነፃነት ሲታሰብ ግን ጨዋታው በማጥቃታ ላይ የተመሰሩ ጥሩ ፉክክር ሊያስመለክተን እንደሚችል ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 17 ጊዜ ሲገናኙ እኩል አምስት አምስት ጊዜ ተሸናንፈው በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ከተማ 16 ጎሎች በማስቆጠር ብልጫ ሲኖረው ሀዋሳ ከተማ 14 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልቂጤ ከተማ

የዚህ ጨዋታ ውጤት ለቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪኩ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ተስፋ ሊሆነው ይችላል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡናን ሽንፈት መጠበቅ እና በሰፊ የጎል ልዩነት የማሸነፍ ግዴታው ሲታሰብ የጊዮርጊስ የሁለተኛነት ዕድል የጠበበ ይመስላል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ወልቂጤ ከተማ ግን ለክብር ከመጫወት ያለፈ ዓላማ አይኖረውም።

የጨዋታው መንፈስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወት እንዲሁም በወልቂጤ ኳስ የመቆጣጠር ዘይቤ የሚከወን ይመስላል። ጊዮርጊሶች የግብ ልዩነታቸውን የማሳደግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑም ሁሉንም ነገር ወደ ፊት እንዲወረውሩ የሚገፋፋቸው ይሆናል። በመሆኑም ወደ ድል በተመለሱቡት የአዳማው ጨዋታ የተጠቀሙትን የ 3-4-3 አሰላለፍ ዳግም ሥራ ላይ በማዋል ጨዋታውን እንደሚከውኑ ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በቡድኖቹ የመጀመሪያው የተመዘገበ የሊግ ግንኙነት ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-3 በሆኑ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።