ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ ሦስት ግቦች ተስተናግደውበት ሀዋሳ ከተማን አሸናፊ አድርጓል።
የሀዋሳ ከተማው ዋና አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድናቸው ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ዳግም ተፈራ፣ ምኞት ደበበ እና ተባረክ ሔፋሞን በማሳረፍ ምንተስኖት ጊምቦ፣ ብሩክ በየነ እና አዲስዓለም ተስፋዬ ቋሚ አድርገዋል። ባለፈው ሳምንት አራፊ በነበረው ድሬዳዋ ከተማ በኩል የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። በዚህም አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በፍሬው ጌታሁን፣ በረከት ሳሙኤል፣ ሱራፌል ጌታቸው፣ አስቻለው ግርማ፣ ሙኸዲን ሙሳ እና ኢታሙና ኬሙይኔ ምትክ ወንድወሰን አሸናፊ፣ ሚኪያስ ካሣሁን፣ ሄኖክ ገምቴሳ፣ ረመዳን ናስር፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና ቢንያም ጥዑመልሳን በአሰላለፉ አካተዋል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ባለቤት ባለፈው ሳምንት ለባህር ዳሩ ተጫዋች ፍፁም አለሙ እና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እንዳበረከቱት ስጦታ ሁሉ በዛሬው ዕለትም ለድሬዳዋው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ፣ ለግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን እና ጥሩ አመትን ላሳለፈው ሙህዲን ሙሳ እንዲሁም በሀዋሳ በኩል ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና ለወጣቱ አማካይ ወንድማገኝ ኃይሉ ሽልማት አበርክተዋል።
የተመጣጠነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ብድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማስተናገድ ተስኖት ነበር። ቡድኖቹም በአብዛኛው መሐል ሜዳ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይቷል። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሀዋሳ ከተማ ወደ ግብ የቀረበበትን አጋጣሚ ፈጥሯል። በዚህ ደቂቃም ደስታ ዩሃንስ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ በየነ እና አለልኝ አዘነ በግንባራቸው ለመጠቀም ጥረው መክኖባቸዋል። ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ23ኛው ደቂቃ በራሳቸው በኩል ወደ ግብ የደረሱበትን ሁነት ፈጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጊምቦ ለተከላካይ አቀብላለው ብሎ የተሳሳተውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ አግኝቶት ወደ ግብ ቢልከውም ኳሱ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል።
በአንፃራዊነት የተሻለ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በ35ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩትም መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ወደ ግብ የላከውን ኳስ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የነበረው የግብ ዘቡ ወንድወሰን አሸናፊ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ግብ ተቆጥሯል። ግቡ ከተቆጠረ በኋላም የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ከሰሞኑን የልጅ አባት ለሆነው አዲስዓለም ተስፋዬ ደስታቸውን ሲገልፁ ታይቷል። ጨዋታው ቀጥሎም በ42 ደቂቃ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ኳስ በእግሩ ለመጫወት ሲጥር ድጋሜ ተሳስቶ ሀዋሳዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዚህም መስፍን በድጋሜ ግብ ለማስቆጠር ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ መረብ ላይ ሊያርፍ ሲል የመሐል ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ ደርሶ ከመስመር ላይ አድኖታል። አጋማሹም በሀዋሳ ከተማ መሪነት ተጠናቋል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በተለየ ሙከራዎችን ማስተናገድ የቻለው የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በተከታታይ ጥሩ ጥሩ ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በቅድሚያም ሪችሞንድ አዶንጎ ለሳሙኤል ዘሪሁን ያመቻቸውን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ብርሃኑ በቀለ አምክኖበታል። በመቀጠል ደግሞ በ54ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ሳጥን ውስጥ ከወንድማገኝ ኃይሉ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ወንደወሰን አውጥቶበታል። ከዚህ በተጨማሪም ደስታ ዩሐንስ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ኳስ ሞክሮ ነበር።
ተከታታይ ሁለት ጥሩ ሙከራዎችን የሰነዘሩት ሀዋሳ ከተማዎች አሁንም በጨዋታው ብልጫ ኖሯቸው መጫወት ቀጥለዋል። ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረውም በ69ኛው ደቂቃ ሙከራቸው ፍሬ አፍርቷል። በዚህም ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከቀኝ መስመር የመጣውን ኳስ ሳጥን ውስጥ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል። መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉት ሀዋሳዎች አሁንም ተጨማሪ ጎል ለማግኘት መታተር ይዘዋል። በቅድሚያም በ77ኛው ደቂቃ የመጀመሪያው ጎል ባለቤት መስፍን በግራ መስመር ወደ ሳጥን አምርቶ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ነበር።
ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ የመጣው ድሬዳዋዎች በ78ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። በዚህም ሪችሞንድ አዶንጎ በሩቁ ቋሚ ላይ በመገኘት ከሄኖን ኢሳያስ የደረሰውን እጅግ ጥሩ ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታው ቀጥሎም በ80ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ደቂቃም ከፍተኛ የትኩረት ማነስ ችግር የታየባቸው የድሬዳዋ ተጫዋቾች ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ወንድማገኝ ኃይሉ ከብሩክ በየነ የተቀበለውን ኳስ ወንድወሰን ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም ውጥናቸው እምብዛም ሳይሰምር ቀርቷል። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በጭማሪው ደቂቃ ላውረንስ ላርቴ ከቅጣት ምት በሞከረው ነገርግን የግቡ አግዳሚ በመለሰበት ኳስ አራተኛ ጎል ለማግኘት ጥረዋል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 35 በማድረስ ከ8ኛ ደረጃ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 28 ነጥቦች ቢሰበስቡም ዛሬ ባስተናገዷቸው ግቦች ከ9ኛ ደረጃ ወደ 10ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።