ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልቂጤ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ፈረሰኞቹን 3-2 አሸናፊ አድርጓል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዋና አሠልጣኝ ፍራንክ ናታል ባለፈው ሳምንት አዳማ ከተማን ከረታው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል። በዚህም አሠልጣኙ በሳላዲን ሰዒድ እና አቤል ያለው ምትክ ዳግማዊ አርዓያ እና ከነዓን ማርክነህን አሰልፈዋል። ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በሰበታ ከተማ ከተሸነፉበት ቋሚ ስብስብ አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ሲሳይ አብርሃ በያሬድ ታደሰ፣ ሄኖክ አየለ፣ ዮናታን ፍስሐ እና ሀብታሙ ሸዋለም ምትክ አህመድ ሁሴን፣ አሜ መሐመድ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ዮናስ በርታን ተክተዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው ከጅማሮው አንስቶ ነው። ጨዋታው ገና በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ላይም ፈረሰኞቹ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ከመልስ ውርወራ መነሻን ያደረገ ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ራሱን ነፃ አድርጎ ለነበረው ሀይደር ሸረፋ አቀብሎት የአማካይ መስመር ተጫዋቹ እጅግ ምርጥ ኳስ መረብን ላይ አሳርፏል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ወልቂጤ ከተማዎች ከመዓዘን ምት የተነሳን ኳስ በመጠቀም ግብ ሊያስቆጥሩ ነበር። ቡድኑም ያገኘውን የመዓዘን ምት በቶሎ በመጀመር ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ረመዳን የሱፍ አግኝቶት ወደ ግብ ቢመታውም ሔኖክ አዱኛ አክሽፎታል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ለማስቆጠር በነበረ ክፍት ጨዋታ ተጨማሪ የግብ ዕድሎች መስተናገድ ቀጥለዋል። በ7ኛው ደቂቃም አብዱልከሪም መሐመድ ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ለአማኑኤል አመቻችቶመት አማኑኤል ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ቶማስ ስምረቱ እንደምንም ኳሱን ከግብነት ታድጎታል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ወልቂጤዎች የያዙትን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በጎል ለማጀብ መታተር ይዘዋል። በቅድሚያም በ10ኛው ደቂቃ አሜ መሐመድ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ በድጋሜ ከቆመ ኳስ ግብ ለማግኘት ታትሮ ነበር። 15ኛው ደቂቃ ሲደርስ ግን ቡድኑ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ ግብ አግኝቷል። በዚህም አህመድ ሁሴን ከአሜ መሐመድ የደረሰውን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ በወጣው ባህሩ ነጋሽ አናት ላይ በመላክ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ ወደ መሪነት የሚወስደውን ጎል ለማግኘት የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ደርሷል። በተጠቀሰው ደቂቃም የግቡ ባለቤት አህመድ ከርቀት የተላከውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ባህሩ ነጋሽ አውጥቶታል።
ወደ ወልቂጤ የግብ ክልል ሲደርሱ አደገኛ ሙከራ አድርገው የሚመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ32 ደቂቃ መሪ ለመሆን ጥረው ነበር። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሀይደር አግኝቶት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢጥርም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ኳሱን አምክኖታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ጊዮርጊስ ሌላ ጥቃት ፈፅሟል። በዚህ ደቂቃም ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ ጀማል ጣሰው በተሳሳተ ጊዜ አጠባበቅ ሲወጣ ያገኘው ከነዓን ማርክነህ ለፍሪምፖንግ ሜንሱ አቀብሎት የመሐል ተከላካዩ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሙሉ የአጋማሹ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች መባቻ ላይም ሄኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር በኩል በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሮት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሀይደር ሸረፋ ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። አጋማሹም ሦስት ግቦች አስተናገዶ በጊዮርጊስ 2-1 መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ደግሞ ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያደርጉትን የነበረውን ጫና ቀነስ አድርገው መንቀሳቀስ ይዘዋል። ወልቂጤዎች ግን በቅድሚያም አሜ ከዛም አህመድ ከርቀት በሞከሯቸው ኳሶች ባህሩን ለመፈተሽ ሞክረዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች በተጨማሪ በ62ኛው ደቂቃ አህመድ ከአሜ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ይህ አጋጣሚ ከተፈጠረ ከደቂቃ በኋላ ግን አህመድ ከረመዳን የሱፍ የደረሰውን ኳስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ ብዙ ሙከራዎች ያልነበሩበት የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳቢነቱ ቀዝቅዞ ታይቷል። በአጋማሹም ወልቂጤ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው ሲገኙ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ቅዱስ ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። በዚህ ደቂቃም ረመዳን አማኑኤል ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ሀይደርም በጨዋታው ሀት-ትሪክ የሰራበትን ጎል አግኝቷል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 40 በማድረስ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል። ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በ22 ነጥቦች የውድድር ዓመቱን ቋጭተዋል።