ከቀናት በፊት ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር በስምምነት የተለያየው ባህር ዳር ከተማ የሦስት ተጫዋቾቹን ውል እንደማያድስ አስታውቋል።
በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ በቀጣይ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ በሊጉ ለመቅረብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ገልጿል። በቅድሚያም ለሁለት ዓመታት የቡድኑ አሠልጣኝ ከነበሩት ፋሲል ተካልኝ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ አሁን ፊቱን ወደ ተጫዋቾች በማዞር በክለቡ የቴክኒክ ኃላፊዎች በቀረበ ግምገማ መሠረት ተጫዋቾችን ለመቀነስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት ስምንት ተጫዋቾች በክለቡ እንደማይፈለጉ እና ሌላ ክለብ እንዲፈልጉ ተነግሯቸዋል። ከስምንቱ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ስማቸው ያልተጠቀሰ አምስት የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ያላቸው መሆኑ የተመላከተ ሲሆን የግብ ዘቦቹ ሀሪሰን ሄሱ እና ሥነጊዮርጊስ እሸቱ እንዲሁም በዓመቱ መጀመሪያ ክለቡን የተቀላቀለው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ምንይሉ ወንድሙ ግን ውላቸው ከቀናት በኋላ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በክለቡ እንደማይቀጥሉ ተረጋግጧል።
1170 ደቂቃዎችን በግብ ብረቶቹ መሐከል ቆሞ ያሳለፈው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ በተሰለፈባቸው 13 የሊጉ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ማስተናገዱ ይታወሳል። የቡድኑ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ የነበረው ሥነጊዮርጊስ እሸቱ ደግሞ አንድም ደቂቃ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሰልፎ አልተጫወተም ነበር። በተቃራኒ ሳጥን አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው ምንይሉ ወንድሙ በበኩሉ 1134 ደቂቃዎች ዘንድሮ ተጫውቶ አምስት ግቦችን (አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ) ማስቆጠሩ አይዘነጋም።