ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን ረቷል

ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡናን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ የጋለ ፉክክር ተስተናግዶበት በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተገባዷል።

የወላይታ ድቻው ዋና አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ባህር ዳር ከተማ ላይ ድል ካገኙበት ቋሚ ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም በደጉ ደበበ እና ዮናስ ግርማይ ምትክ ነፃነት ገብረመድኅን እና አንተነህ ጉግሳ በአሰላለፋቸው አካተዋል። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጅማ አባጅፋርን ካሸነፈው ስብስብ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተደረጉት ለውጦችም አማኑኤል እንዳለ፣ ሰንደይ ሙቱኩ፣ ያሳር ሙገርዋ፣ ብርሀኑ አሻሞ እና ቢንያም በላይ አርፈው ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ጊት ጋትኩት፣ ግሩም አሰፋ፣ ይገዙ ቦጋለ እና አበባየሁ ዮሐንስ በቋሚ አሰላለፍ ተካተዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል በውድድር ዓመቱ ጥሩ ነበሩ ላሏቸው የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው፣ ደጉ ደበበ እና ቸርነት ጉግሳ እንዲሁም ለሲዳማ ቡናው አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ዳዊት ተፈራ በሲዳማ ክልል የእግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ አማካኝነት ስጦታ አበርክተዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃም ግብ አስተናግዶ ገና በጊዜ መሪ አግኝቷል። በዚህም የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች የተሳሳቱትን ኳስ በፍጥነት ወደ ሳጥን ይዘው የተጓዙት ወላይታ ድቻዎች በተጠቀሰው ደቂቃ መሪ ሆነዋል። የአማካይ መስመር ተጫዋቹ እድሪስ ሰዒድም በቅብብል ስህተት እግሩ ስር የደረሰውን ኳስ ለኢዙ አዙካ አቀብሎት የመስመር አጥቂው ጥሩ የመጨረሻ ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው ስንታየው መንግስቱ አቀብሏል። ስንታየሁም ከኢዙ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች በአመዛኙ ቀጥተኛ አጨዋወትን በመተግበር ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ታይቷል። በዚህ አጨዋወትም በ24ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረው አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው አጨዋወትም መሀሪ መና ከርቀት የደረሰውን ኳስ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አሻምቶት ይገዙ ቦላለ በግንባሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ግቡ ከተቆጠረ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ አጨዋወት ግሩም አሰፋ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ይገዙ ለመጠቀም ጥሮ ነበር።

በተራቸው ግብ ካስተናገዱ በኋላ ተመልሰው የተነቃቁት ድቻዎች በ38ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህ ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እድሪስ ሰዒድ ለቸርነት ጉግሳ በተከላካዮች መሐከል ጥሩ ኳስ ያመቻቸለት ቢሆንም ቸርነት ግብ ጠባቂውን አልፎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ በመጠቀም የግቡ ባለቤት ስንታየሁ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ጥሮ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተገባዷል።

ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ማስመልከት የቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ያን ያህል የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች አልተስተናገዱበትም። አጋማሹ በተጀመረ በ50ኛው ደቂቃ ግን ወላይታ ድቻ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በቶሎ መሪ ለመሆን ዳድቶ ነበር። በዚህ ደቂቃም ቸርነት ከመሐል የተላከለትን ኳስ ለስንታየሁ አመቻችቶለት የነበረ ቢሆንም ቁመታሙ አጥቂ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ እድሪስ በፈፀመው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በማማዱ ሲዲቤ አማካኝነት ወደ ግብ መተውት የነበረ ቢሆንም ኳሱን ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ አምክኖታል።

ጨዋታው ቀጥሎ በ61ኛው ደቂቃ ሲዳማ ቡና መሪ ሆኗል። በተጠቀሰው ደቂቃም ከግራ መስመር መሀሪ ያሻገረውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብ ሲመታው የግቡ ቋሚ መለሰበት። የተመለሰውን ኳስም ይገዙ ቦጋለ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል። ግቡ ከተቆጠረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ድቻ ሁለት ያለቀላቀቸው አጋጣሚዎችን በመፍጠር ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ተንቀሳቅሰዋል። ሁለቱንም ዕድሎች የፈጠረው ቸርነትም በቅድሚያ በተከላካዮች መሐል የተላከለትን ኳስ ወደ ግብ መቶት ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ የመለሰው ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ ሞክሮት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

የጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ላይም ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ሲታትሩ የነበሩት ድቻዎች በጋቶች የርቀት ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። ሲዳማ ቡናዎች ግን ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረውት ያገኙትን ሦስት ነጥብ አስጠብቀው ወተዋል። በጭማሪው ደቂቃም የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች የመዓዘን ምት ለመጠቀም ነቅለው ሲሄዱ (ግ ጠባቂውን ጨምሮ) ሲዳማዎች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረው መክኖባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ሦስት ነጥብ አስረክበው የወጡት ወላይታ ድቻዎች በ33 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዘው የውድድር ዓመቱን ቋጭተዋል። ሦስት ነጥብ ቢያገኙም ደረጃ እንደማያሻሽሉ ቀድመው የሚያውቁት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ነጥባቸውን 31 በማድረስ ትናንት ያገኙት 9ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።