በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የረፋዱ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብሏል።
ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው?
ጨዋታው ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል ቀድመን አውቀናል። ማንኛውም ቡድን መሸነፍ እንደማይፈልገው ሁሉ ቡድኖቹም መሸናነፍ አይፈልጉም። በተለይ ደግሞ የወላይታ ድቻ እና የሲዳማ ቡና ትንሽ ጠንከር ይላል። ሁል ጊዜም ሲገናኙ ይሄ ይታያል። ዛሬም እንደገመትነው ትንሽ ውጥረት የበዛበት ነበር። እኛ ግን አመጣጣችን የመጨረሻውን ጨዋታ ለማሸነፍ ነው። ቡድናችን ያለፉትን ድክመቶቹን እያሻሻለ መጥቷል። በ31 ነጥብ ውድድሩን መጨረሳችንም ትልቅ ነገር ነው።
ስለ ይገዙ ቦጋለ ብቃት?
ይገዙ በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው። ያልከውን መፈፀም የሚችል ተጫዋች ነው። የሚባለውን ነገር ይከታተላል። ያንንም ለማረግ ይጥራል። ወደፊትም የተሻለ ነገር ይሰራል ብዬ አስባለሁ። ዛሬም ሁለት ጎል አግብቷል። እርግጥ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደ ሜዳ በገባበት ጊዜ ሁሉ ጥሩ ነገር እየሰራ ይወጣል። ቡድኑንም በተገቢው ሁኔታ ጠቅሞታል ብዬ አስባለሁ።
ስለ መሐሪ መና እንቅስቃሴ?
ዛሬ በመስመር አጨዋወታችን ሌሎቹንን ተጫዋቾች ለማየት ግሩምን አስገብተን ነበር። ግን የተጠበቀውን ያክል አልነበረም። አማኑኤልንም ቀይረን አስገብተናል። ብድናችን የመስመር አጨዋወቱ ጥሩ ነው። መሐሪ ደግሞ ብዙ የመሮጥ አቅም ያለው ነው። ዛሬም ጥሩ ነገሮች ሰርቷል። ከዚህ በፊትም ጎልም ማግባት ችሏል።
ስለ ቀጣይ ዓመት ቆይታ?
በህጉ ላይ የተቀመጠ አስገዳጅ ነገር አለ። ሲዳማ ለ6 ወር ነው የፈረምኩት። ይሄንን የፈረምኩበት ምክንያትም የትግራይ ክለቦች ይመጣሉ አይመጡም የሚለው ነገር ታሳቢ ተደርጎ ነው። እንግዲህ የእኔን እጣ ፈንታ የሚወስነው በቀጣይ ጊዜያት በሚፈጠሩት ነገሮች ነው። ግን ከሲዳማ ጋር ልቀጥል እችላለሁ ብዬ አስባለሁ።
ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው?
የመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ የተቀዛቀዘ ነበር። እኛ በጊዜ ጎል ብናገባም በሁለታችንም በኩል ሳቢ የነበረ እንቅስቃሴ አልነበረም። ከእረፍት በኋላ ግን ግቦች ተቆጥረዋል። ግቦቹም ከተቆጠሩ በኋላ ጨዋታው ትንሽ ለመፍጠን ሞክሯል። እኛም ጎል ከገባብን በኋላ እንቅስቃሴ አድርገናል። ይሄ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው ጀምሮ ማድረግ ቢቻል ኖሮ ምናልባል ውጤቱ ሊገለበጥ ይችላል።
ስለ ቀጣይ የውድድር ዘመን ዝግጅት?
ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው። ለማንኛውም እኔ የውል ዘመኔ ሀምሌ 30 ይጠናቀቃል። ከዛ በኋላ እንግዲህ እነዚህ ታዳጊዎች ላይ መስራት አንድ ነገር ነው። ምክንያቱም አካባቢው ጥሩ አቅም ያላቸው ልጆች ስላሉበት። አሠልጣኝም 50 ቦታ ከሚሄድ በአንድ ቦታ ቢቆይ ስኬታማ ለመሆን መነሻ ይሆነዋል። ረጅም ጊዜ ቆይታ በማድረግ ማለት ነው። ስለዚህ በቀጣይ የሚሆኑ ነገሮች ቆይታዬን ይወስኑታል።
በውድድር ዓመቱ ስለመረጣቸው ኮከቦች?
አሠልጣኝ የሊጉ አሸናፊ ከሆነው ክለብ ነው የመረጥኩት። አሠልጣኝ ስዩም ከበደን። እንደ ቡድን የእኛ ቡድን ሽልማት ይገባዋል። ምክንያቱም ከ4 ነጥብ ወደ 33 ነጥብ መምጣት ቀላል ስላልሆነ። ከዚህ ውጪ ተስፈኛ ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ ነው። ኮከብ ተጫዋች ከአንድ እስከ ሦስት ምረጥ ከተባልኩ ሦስቱንም ቦታ ላይ የአቡበከርን ስም እከታለሁ።