የከሰዓቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የአሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህን መሳይ ነበር።
አሰልጣኝ ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለጨዋታው
ብዙ ዕድሎች የፈጠርንበት ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ርቀን መሄድ ነበረብን። ያን ባለማድረጋችን ጨዋታውን ራሳችን ላይ አክብደናል። ነገር ግን ወደ ጨዋታው ለመመለስ እና ግብ ለማስቆጠር ተጫዋቾች ያሳዩት መነሳሳት አስደሳች ነበር። ያም በመጨረሻ የአሸናፊነቱን ጎል እንድናገኝ አድርጎናል።
ስለተደረጉት የተጫዋቾች ሚና ለውጦች እና ውጤታቸው
በዛሬው አሰላለፍ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ፈጥረናል። በአጋማሹ ጥሩ ስራ በመስራታችን ለውጦቹ መልካም ነበሩ።
ስለሀይደር ሸረፋ የዕለቱ ብቃት
ሀይደርን እንኳን ደስ ያለህ ማለት እፈልጋለሁ። እሱም በአሰላለፍ ውስጥ ስላካተትኩት እንሰሚያመሰግነኝ አስባለሁ።
የቡና የመጨረሻ ጨዋታ ስለሁለተኝነት በማሰብ እንደሚመለከቱ
አዎ እሱ እንዴት እንደሚሆን እንመለከታለን።
ለቀጣዩ ዓመት አዲስ ተጫዋቾችን ስለማስፈረም
ቡድኑን የተሻለ የሚያደርጉ ከሆኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ታመጣለህ። እሱ በጣም ወሳኝ ነው። ግን ለማምጣት ብቻ ብለህ አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድንህ አትቀላቅልም። ካሉት የተሻሉ መሆን ስላለባቸው ትክክለኛዎቹን ተጫዋቾች ለማግኘት ምርጫችን ላይ ጥንቁቅ መሆን አለብን።
አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀ – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው
እስካሁን ከነበሩን ጨዋታዎች እጅግ በጣም የተሻለ ነው። በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ ተጫዋቾቹም ደስተኛ ናቸው። እንዲህ ተጫውተን ውጤት ብናጣም ችግር የለውም። የኳስ አንዱ አካል ነው ፤ ባለቀ ሰዓትም ነው የተቆጠረብን። እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ቡድኑ ከጫና ነፃ ሆኖ ስለመጫወቱ
ያሌለህን አታመጣም ፤ መጀመሪያም አላቸው ። ግን አሁን ኃላፊነት ወስደው ልምምድ ላይ ስንሰራም ከጨዋታ በፊትም ስንነጋገር ‘ያላችሁን ነገር አውጥታችሁ ተጠቀሙ ዛሬ ነው ዕድላችሁ ‘ ብያቸዋለሁ። ለዚህ ነው በነፃነት ሲንቀሳቀሱ የነበረው። እንደሚታወቀው የተሻሉ እና ኳስ ላይ ችግር የሌለባቸው ተጫዋቾች ናቸው። ውጤቱ አይገባንም ዕውነት እናውራ ከተባለ።
ስለ አህመድ ሁሴን የዕለቱ ብቃት
አህመድ ሁሴን ወደፊት ጥሩ አጥቂ ይሆናል። ምክንያቱም በግል የሚሰራቸው ልምምዶች ያስፈልጉታል እንጂ ብዙ ነገር አለው። ፍጥነት አለው ፣ በግንባር ገጪ ነው ፣ አክርሮ መቺ ነው አንድ አጥቂ ያለው ብዙ ነገር አለው። ከሰራ የተሻለ አጥቂ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
ስለአብዱልከሪም ወደ ኋላ ተመልሶ መጫወት
ምንም አማራጭ አልነበረንም ፤ ተከላካዮቻችን በጉዳት ስለወጡ። የመከላከል ባህሪው ጥሩ ነው ኳስ ስንይዝ ደግሞ ከኳስ ጋር ያለው ነገር ጥሩ ስለሆነ ተነጋግረን ‘እኔ እመለሳለሁ’ ብሎ የተሻለ ነገር ሲያደርግ ነበር።
ስለቀጣዩ ዓመት
እኔ እንቆያለን ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም እኔ የመጨረሻውን ውሳኔ እስከምሰማ አለን ነው የምለው።