ነገ የሚከወኑትን ጨዋታዎች የተመለከተው ዳሰሳችንን እነሆ !
ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና
ጥሩ ፉክክር እንደሚያስተናግድ በሚጠበቀው የረፋዱ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ከሰንጠረዡ ወገብ በታች ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ተስፋን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል። ቡድኑ ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ያሳየውን መሻሻል ይዞ በሚጨርሰው ደረጃ ለማጀብም የነገው ጨዋታ አስፈላጊው ነው። በተመሳሳይ መሻሻሎችን እያሳየ እዚህ ለደረሰው ሲዳማ ቡና ግን የጨዋታው ውጤት ያለበትን 9ኛ ደረጃ የሚቀይረው አይሆንም።
ባህር ዳር ከተማን አሸንፎ ለዚህኛው ጨዋታ የቀረበው ወላይታ ድቻ ካለበት ከፍ ብሎ ዓመቱን ለመጨረስ አጥቅቶ እንደሚጫወት ይገመታል። በባህር ዳሩም ጨዋታ እንደታየው በአመዛኙ ቀጥተኛ አጨዋወቶችን በመተግበር ወደ ግብ ለመድረስ የሚደርገውን ጥረት ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል ጎሎችን ለማግኘት እንሰሚጥር ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ፈጣን ሽግግሮችን በተለይ ቸርነት ጉግሳ በሚሰለፍበት መስመር በማመዘን ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሊሞክር ይችላል።
ሲዳማ ቡናም በተመሳሳይ ቁመታቸው ዘለግ ያሉትን አጥቂዎቹን ያማከለ አጨዋወት ሊከተል እንደሚችል ይጠበቃል። በተለይ ደግሞ ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን የሚያዘወትርበት ዕድል ይኖራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጅማው ጨዋታ ድንቅ የነበረው ዳዊት ተፈራ መሐል ለመሐል ለሚደረጉ ጥቃቶች መነሻ ሊሆን ይችላል። በዚሁ ጨዋታ ሐት ትሪክ የሰራው ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢም ከድቻ የተከላካይ መስመር ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 13 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ስድስት ጊዜ አሸንፏል።
– በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 18 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 7 ፣ ሲዳማ ቡና 12 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ሰበታ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ዕድሉ ያመለጠው ሰበታ ከተማ ከዚህ ጨዋታ ነጥቦችን ማግኘት ያለበትን የአራተኝነት ደረጃ ይዞ ለመጨረስ ይረዳዋል። በአንፃሩ ለቻምፒዮኖቹ ፋሲሎች ነጥቦቹ ከሚሰጡት ጥቅም በላይ ለሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ያጡትን አሸናፊነት መልሶ ማግኘት ዋጋ ይኖረዋል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎቹ ሽንፈት ያላገኘው ሰበታ ከተማ ግብ ካስተናገደም ሁለት ዘጠና ደቂቃዎች አልፈውታል። ከዚህ ጥሩ አመጣጡ እና በነፃነት ከመጫወቱ አንፃርም ነገ በተለመደው አኳኋን በኳስ ቁጥጥር ላይ በተመሰረተው ጨዋታ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በመጨረሻ ጥሩ የሆነለትን የመከላከል ሪከርዱን አስጠብቆ ለመጨረስ ግን የአፄዎቹን ፈጣን ጥቃቶች የማቋረጥ አቅሙን ከፍ አድርጎ መገኘት ይኖርበታል።
ፋሲል ከነማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት ቻምፒዮንነቱን የሚመጥን አልነበረም። በስህተቶች ከተሞላው የድሬዳዋው ጨዋታ መልስ በሀዋሳ ብልጫ ተወስዶበት እና በርካታ ሙከራዎችን አስተናግዶ ነጥብ መጋራቱን ለመርሳትም ነገ በሙሉ ኃይሉ አጥቅቶ ለመጫወት እንደሚሞክር ይጠበቃል። በሌላ በኩል የቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች ዕድል እያገኙ ያሉበት መንገድ ነገም እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሊጉ የመጀመሪያ የተመዘገበ ግንሙነታቸውን ዘንድሮ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖሾች 1-1 ተለያይተው ነበር።