ቅድመ ዳሰሳ | የዘንድሮ የውድድር ዓመት የመዝጊያ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከተ ዳሰሳ

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፍፃሜን የሚያበስሩ ሁለት የነገ መርሐ-ግብሮችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ (4:00)

ከዚህ ጨዋታ የሚጠበቀው ብቸኛ ነገር ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ዓመት በኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ ያለውን የሰፋ ዕድል አረጋግጦ ይወጣል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው። በአሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመራው ቡድን አምስት እና ከዛ በላይ ግቦችን አስተናግዶ የማይሸነፍ ከሆነ በአፍሪካ መድረክ ከ10 ዓመታት በኋላ የሚያሳትፈውን ሁነት መፍጠር ይችላል። እርግጥ በእግርኳስ የሚፈጠረው ነገር ባይታወቅም ቡድኖቹ ካላቸው ወቅታዊ ብቃት አንፃር የቡና ለመረጋገጥ የተጠጋው ዕድል የሚኮላሽ አይመስልም። ይሄ ቢሆንም ግን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን የሆነው ቡና ነገም እንደለመደው ግቦችን ለማግኘት እንደሚታትር ይገመታል። በዚህም ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ያገኘውን ድል ነገም በመድገም የውድድር ዓመቱን በፌሽታ ለማገባደድ እንደሚጥር ይታመናል።

ለበርካታ ወራት በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የከረመው አዳማ ከተማ በበኩሉ ከመጀመሪያዎቹ የሊጉ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ደረጃውን ለማሻሻል (የጅማ ውጤት እስኪታወቅ) ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። በዋናነት ደግሞም ከሁለት ጨዋታዎች በፊት ከረጅም ጥረት በኋላ ያገኘውን ሦስት ነጥብ በድጋሜ አግኝቶ በድል የጀመረውን የውድድር ዓመት በድል ለመቋጨት እንደሚሞክር ይታሰባል። ግብ የማስተናገድ አባዜ ያለበት ቡድኑም በነገው ጨዋታ ፈጣኖቹን የቡና አጥቂዎች በመቆጣጠር ስል የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሊተገብር ይችላል። ከዚህ ውጪ ረጃጅም ኳሶችን አዘውትሮ ሊጠቀም እንደሚችል ይገመታል። ቡናዎች ግን ከኳስ ጋር ረጅሙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በማሳለፍ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የሚያስችላቸውን ስልት ዘይደው ሊመጡ ይችላሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 37 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 21ዱን ግንኙነት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው 9 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። ውጤት ተጠናቀዋል።

– 100 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 67፤ አዳማ 33 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ጅማ አባጅፋር ከ ሀዲያ ሆሳዕና (9:00)

ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት የሚደረገው የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነጥብ እና ደረጃን (ሀዲያ) ከማሻሻል የዘለለ ዓላማ የለውም። ይሄ ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ከጭንቀት የነፃ እንቅስቃሴን እንዲያደርጉ ሊገፋፋቸው ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ክፍት፣ አዝናኝ፣ መመላለስ የበዛበት እና በርካታ ሙከራዎች የበዙበት ጨዋታ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስር በእንቅስቃሴ ረገድ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የመጣው ጅማም በመጨረሻው የሲዳማ ጨዋታ ያሳየውን እጅግ ደካማ ብቃት ለመሻር እና 12ኛ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ ያለውን ፍላጎት ነገ የሚያሳይ ይሆናል። ከምንም በላይ ግን ባለፉት አስር የጨዋታ ሳምንታት ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር የተሳነው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ከፈለገ የፊት መስመሩን አሹሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። በተለይ ደግሞ የመልሶ ማጥቃቶችን እና ቀጥተኛ አጨዋወቶችን መርጦ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል።

በወጣት ተጫዋቾች የውድድር ዓመቱን ለማገባደድ የተገደደው ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ አራተኛ ደረጃን ለመያዝ የነገውን ጨዋታ አጥብቆ ይፈልገዋል። ሁለቱን የመዲናችን ክለቦች አስተናግዶ የመጣው ቡድኑም ወላይታ ድቻ ላይ ያገኘውን የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለመድገም ተግቶ ሊጫወት ይችላል። በተሸነፈባቸውም ሆነ ባሸነፈባቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ እጅግ ታታሪ የነበረው ቡድኑ ነገም በዚህ ባህሪው ጨዋታውን ሊቀርብ ይችላል። በዚህም በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ሆኖ ሊንቀሳቀስ እንደሚችል ይገመታል። ከሁሉም በላይ ግን የዳዋ ሆቴሳ አይደክሜነት በነገው ጨዋታ ለጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች የራስ ምታት ሊሆን ይችላል። በተለይ ተጫዋቹ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካይ አፈትልኮ የሚወጣበት መንገድ ለሀዲያ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ባገናኘው የዘንድሮው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና በአልሀሰን ካሉሻ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።