ሪፖርት | አሰልቺው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በሰበታ ከተማ እና ፋሲል ከነማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ጠንካራ ሙከራ ሳይታይበት 0-0 ተጠናቋል።

ሰበታ ከተማ ሰለሞን ደምሴ ፣ አዲሱ ተስፋዬ ፣ ያሬድ ሀሰን ፣ አብዱልባስጥ ከማል ፣ አብድልሀቪዝ ቶፊቅ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ዱሬሳ ሹቢሳ ወደ አሰላለፍ ሲያመጣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ ፍፁም ገብረማርያም እና ቡልቻ ሹራን አሳርፏል።

በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ ሰዒድ ሀሰን ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ መጣባቸው ሙሉ ፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና በረከት ደስታ ሚካል ሳማኬ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ይሁን እንዳሻው ፣ አቤል እያዩ እና ሙጂብ ቃሲምን በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል እጅግ ደካማ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር። በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረባቸውን ከራሳቸው የሜዳ ክልል ከመውጣት ያለፈ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ አልሩዳቸውም። የአንዳቸውን የማጥቃት ሂደት ሌላኛቸው እያቋረጡ አመዛኙ የጨዋታ ሂደት በሁለቱ ሳጥኖች መሀል ተገድቦ ቆይቷል። 33ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግንባር ለመግጨት ሞክሮ የወጣበት አጋጣሚ ብቻ በሙከራነት ሊጠቀስ ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን ተጋጣሚዎቹ ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች በብዙ ርቀት ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋቾች ፍጥነት ጨመር ብሎ ቢታይም የጨዋታ ሂደቱ ግን ሳቢ ሊሆን አልቻለም። ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በኳስ ቁጥጥራቸው ለግብ ክልሉ ይቀርቡ የነበሩት ሰበታዎች ግን ከባባድ የሚባሉ የግብ ዕድል አልፈጠሩም። 68ኛው ደቂቃ ላይ ኦሰይ ማዉሊ የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ከቅጣት ምት ቢያደርግም ለይድነቃቸው ፈታኝ አልነበረም። ተጫዋቹ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው ቡልቻ ሹራ ከቀኝ መስመር ያዞረለትን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ፊት መስመር ላይ የወትሮው አስፈሪነታቸው አብሯቸው ያልነበረው ፋሲሎች ግን የተጫዋቾች ለውጥ ቢያደርጉም ሜዳ ላይ ያሳዩት ብቃት ሳይሻሻል ጨዋታው ተጠናቋል። በጥቅሉ ሲታይ ጨዋታ በቅድድር ዓመቱ ከታዩ ደካማ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ሲሆን ቡድኖቹ በዓመቱ ብዙ ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን መጠቀማቸው ብቻ በመልካም ጎኑ ይነሳል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ54 ሰበታ ከተማ ደግሞ በ37 ነጥቦች ውድድሩን አጠናቀዋል።