የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የጅማ አባጅፋር እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ለነብሮቹ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ሰጥቶ ተጠናቋል።
ለበርካታ የጨዋታ ሳምንታት የነበረበትን 12ኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ማጠናቀቁን ያረጋገጠው ጅማ አባ ጅፋር ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና ከተረታበት ስብስብ ከአራት ተጫዋቾች በቀር ሁሉንም ለውጦ ወደ ሜዳ ገብቷል። ብቸኞቹ ለውጥ ያልተደረገባቸው ተጫዋቾችም ወንድማገኝ ማርቆስ፣ ዋለልኝ ገብሬ፣ መላኩ ወልዴ እና ተመስገን ደረሰ ብቻ ናቸው።
ደረጃውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ የሚገባው ሀዲያ ሆሳዕና በኩል በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈው ቋሚ ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም እሸቱ ግርማ በፀጋሰው ድማሙ ምትክ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካቷል።
በጥሩ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ገና ጨዋታው ሁለት ደቂቃ ሳይሞላው በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ዳዋ ወደ ግብ የመታውንም ኳስ የመጀመሪያ ጨዋታውን በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ እያደረገ የሚገኘው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ አድኖታል። ጅማዎች በበኩላቸው ቀስ በቀስ በጨዋታው ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እያሳደጉ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ቡድኑም ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሀዲያ የግብ ክልል እየላከ ቀዳሚ ለመሆን ቢጥርም ፍሬያማ መሆን ሳይችል ቀርቷል። ሀዲያዎች ግን በ20ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አርፊጮ በተሰለፈበት መስመር ከረጅም ርቀት የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶት የግቡ አግዳሚ በመለሰበት አጋጣሚ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።
ጨዋታው ቀጥሎም በ31ኛው ደቂቃ ሀዲያ ሌላ እጅግ ለግብ የቀረበበትን አጋጣሚ ፈጥሯል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይም የተገኘውን የቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ ወደ ግብ አሻምቶት የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው እሸቱ ግርማ በግንባሩ ሞክሮት ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እየተሻሻሉ የመጡት ጅማዎች ከተሻጋሪ ኳሶቻቸው በተጨማሪ በአመዛኙ ወደ ግራ ባዘነበለ መስመር በአንድ ሁለት ቅብብል ለመግባት ሲታትሩ ታይቷል። በዚህ መስመር ላይም በ43ኛው ደቂቃ ቤካም አበደላ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ የቡድኑን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። ቤካም በግራ እግሩ የመታውንም ኳስ የግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ አክሽፎታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ግብ ሳይቆጠርበት ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
አንድ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በዚህኛውም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የበዛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልታየም። በአንፃራዊነት ሀዲያ ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ ተሽሎ መገኘታቸው ገና ከጅምሩ ዋጋ ክፍሏቸዋል። አጋማሹ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም ቡድኑ መሪ የሆነበትን ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ደቂቃም የመሐል ተከላካዩ መላኩ ወልዴ ለግብ ጠባቂው በረከት አማረ ኳስ ወደ ኋላ እስጣለው ብሎ አሳጥሮ የላከውን ኳስ ፈጣኑ ተጫዋች ዱላ ሙላቱ አግኝቶታል። ዱላም ኳሱን ከተቆጣጠረ በኋላ ግብ ጠባቂውን አልፎ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላም ኳሱን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጅማዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ማግኘት የሚያስችላቸውን የማጥቃት አጨዋወት ሳያስመለክቱ ጨዋታው ቀጥሏል። ይባስ ብሎም ቡድኑ በ74ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃም ከተከላካዮች ፈትልኮ የወጣው ዱላ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት አሻግሮት እንዳለ አባይነህ አግኝቶታል። ራሱን ነፃ አድርጎ የነበረው እንዳለም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገ ጎል አስቆጥሯል።
የሀዲያን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል መፍትሄ ያልነበረው ጅማ በ75ኛው ደቂቃ መላኩ ወልዴ ከቆመ ኳስ በሞከረው ሙከራ ጥቃት ፈፅሟል። ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ ይዞ የገባው መላኩ ይሄንን ሙከራ ካደረገ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዱላ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ መባቻ ላይም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተመስገን ብርሀኑ ከሚካኤል ጆርጅ የደረሰውን ኳስ በመጠቀም ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 3-0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነጥባቸውን 38 አድርሰው ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ከሊጉ መውረዳቸውን ቀድመው ያወቁት ጅማዎች ደግሞ በ15 ነጥቦች 12ኛ ደረጃን በመያዝ የውድድር ዘመኑን ቋጭተዋል።