የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-3 ሀዲያ ሆሳዕና

ከመጨረሻው የውድድር ዘመኑ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች ለሱፐር ስፖርት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ኢያሱ መርሐፅድቅ – ሀዲያ ሆሳዕና

ተጫዋቾቹ ስላደረጉት እንቅስቃሴ?

በእንቅስቃሴያቸው እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። የምፈልገውን ብቻ ሳይሆን ከምፈልገውም በላይ ነው የተንቀሳቀሱት። ከሚጠበቅባቸው በላይም ሜዳ ላይ ስራ ሰርተዋል።

በሜዳ ላይ ጥሩ ስለነበሩት ወጣት ተጫዋቾች ተስፋ?

ወደ ሰባት የሚጠጉ ተጫዋቾች ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ የመጡ ናቸው። ተጫዋቾቹም ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው ትልቅ ትምህርት የሰጡት። ስለዚህ መስራት በምንችለው መንገድ ከሰራን ወጣቶቹ አስተምረውናል።

በውድድር ዘመኑ ጠንካራ ስለነበረው ቡድን?

ግልፅ ነው። ፋሲል ከነማ ነው ጠንካራው ቡድን። ከሁላችንም እጅግ በጣም ርቆ ነው ዋንጫውንም ቀድሞ ያረጋገጠው።

ዘንድሮ ስለታዩት ወጣት ተጫዋቾች?

የዛሬውን ጨዋታ እንኳን በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። ከእኛ ቡድን አንፃር በአጠቃላይ ተቀይረው የገቡትን ጨምሮ ስምንት ተጫዋቾቸ ወጣት ተጫዋቾች ናቸው። እነኚህን ማሳየት መቻል ትልቅ ዋጋ አለው።

ማመስገን ስለሚፈልገው ሰው?

ለማመስገን ጊዜ አይበቃኝም። ከፈጣሪ በታች እጅግ በጣም ብዙ አካላቶች አሉ። ለዛሬ ግን መታሰቢያነት ስጥ ከተባልኩ ለወላጅ እናቴ ሐረገወይን ገብረመስቀል እሰጣለሁ።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ስለ ጨዋታው?

ዛሬ ለውጤት ብቻ አይደለም የገባነው። የዓመቱን እንቅስቃሴያቸንንም ለማየት ብቻ አደለም ወደ ሜዳ የገባነው። በውጤት ደረጃም የሚቀይረን ነገር ባይኖርም በዓመቱ ውድድር ላይ ብዙ ያልተሰለፉ ተጫዋቾችን ለማሰለፍ ሞክረናል። ዓላማችንም ይሄ ነበር። የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ብዙ አልከፋኝም። በውጤት ደረጃ ግን ሀዲያዎች የተሻሉ ነበሩ። ዞሮ ዞሮ ጨዋታው ብዙም ዓላማ ባይኖረውም አሸንፈን ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር። ይህ ባይሆንም ዛሬ በቀጣይ በሚኖረው ውድድር ላይ ያለውን የቡድኑን ብቃት ከእኛ በበለጠ ክለቡ የተማረበት ነገር ይበዛል።

በውድድር ዘመኑ ጠንካራ ስለነበረው ቡድን?

እኔ ወደ ክለቡ የመጣሁት በመሐል ነው። ወደ ቡድኑ ከመጣው በኋላ ባየሁት እንደ ቡድን ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ውጤታቸውም ይሄንን ያሳያል። ዞሮ ዞሮ የዘንድሮ ውድድር ውጤታማ ነበር። ብዙ ነገርም ያየንበት ነበር። በአጠቃላይ ጥሩ ዓመት ነበር።