የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ራሱን በገቢ ለማጠናከር የህንፃ እና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ግንባታዎችን በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማሮ አንስቶ ያለፉትን ረጅም ዓመታት እየተወዳደረ የዘለቀው እና ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው ሀዋሳ ከተማ ራሱን በተሻለ ለማሳደግ ገቢ የሚያመነጭ ሱቅን ከሰባት ዓመት በፊት ገንብቶ በሥራ ላይ ማዋሉ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ላቅ ባለ ደረጃ ዘመናዊ ህንፃን ጨምሮ በርካታ ግንባታ የሚያካትት የመሠረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት አስቀምጧል።
መርሐ ግብሩ የተከናወነው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ፣ የክለቡ አመራሮች ፣ አሰልጣኞች ፣ ስፖርተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነበር፡፡ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ግንባታው በውስጡ ለበርካታ ተግባራት የሚውሉ ክፍሎችን እንደያዘ የሀዋሳ ከተማ የዲዛይን እና ግንባታ ቢሮ ተወካይ ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡ ተወካዩ በገለፃቸው ባለ አራት ደረጃ ህንፃው ቀዳሚው ሲሆን በውስጡ ለንግድ ሱቅ የሚሆኑ ክፍሎች እና ካፌን የያዘ ሲሆን ክለቡ ራሱን ችሎ ከመንግሥት እንዲላቀቅ ሱቆቹ እና ካፌዎቹ በኪራይ መልክ ገቢን እንደሚያስገኙ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ክለቡ ሌላ ባለ ሁለት ደረጃ ህንፃ ግንባታን የሚያደርግ ሲሆን በዚህ ህንፃ ውስጥ የክለቡ ተጫዋቾች እና አባላት የሚያድሩበት 250 ክፍሎችን የሚይዝ ይሆናል። ከዚህም ባለፈ የስፖርተኞች የመመገቢያ አዳራሽ ፣ ዘመናዊ የማብሰያ ክፍሎች ፣ ጅምናዚየሞች እና የስብሰባ አዳራሾችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን ከሁለቱ ህንፃ ግንባታ በተጨማሪ ለክለቡ የሚመጥኑ አነስተኛ የመለማመጃ ሜዳዎች መዋኛ ገንዳን ጨምሮ የሚካተቱ ይሆናል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ባደረጉት ንግግር “ከተማዋን ከፍ ላደረገው ክለብ አንድ ነገር ያስፈልገዋል ብለን በማሰብ ነው ይሄን ግንባታ ተግባራዊ ለማድረግ የተነሳነው። ይህ ክለብ ሀዋሳ ለደረሰችበት ዕድገት ትልቅ ድርሻ አለው። ስለዚህ ስለሚገባው አድርገናል። ይሄ ጅምር ነው፤ ከዚህም በበለጠ ወደ ፊት እየሠራን እንቀጥላለን። በቀጣይ በአጭር ጊዜ ሲጠናቀቅ ስፖርተኞች ሙሉ ጊዜያቸውን እዚሁ ነው የሚያሳልፉት። ይሄ ለእነሱ ትንሽ ነው። ቀጣይም በዚሁ የሚቀጥል ይሆናል። ህንፃው ሲጠናቀቅ አንዱ ክፍል በክለቡ ቀድመው የተጫወቱ እና ታሪክ ለሰሩ ተጫዋቾች ሙዚየም ይሆናል።” ብለዋል።