የ2013 የውድድር ዘመን ተጠናቋል። በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ትኩረትን የሳቡ ዓበይት የክለብ ትኩረቶችንም እነሆ ብለናል።
👉 የፋሲል ከነማ ቀጣይ የቤት ሥራ
በ2009 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደጉበት ጊዜ አንስቶ ፋሲል ከነማ በሊጉ ከፍተኛ እምርታን እያሰየ ይገኛል። የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆን የቻሉት ዐፄዎቹ በብዙ መመዘኛዎች ፍፁም የተዋጣለት የውድድር ዘመንን ማሳለፍ ችለዋል። በዚህም በባለፉት ጥቂት የውድድር ዓመታት በሊጉ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከተከታዮቻቸው በአስር ነጥቦች ርቀው የሊጉን ዋንጫ ማሳካታቸው የተለየ ያደርገዋል። ነገርግን ቻምፒዮንነቱን ተከትሎ እስከ አሁን ከመጣበቶ መንገድ ይልቅ ወደፊት የሚጓዝበት መንገድ ላይ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።
የዐፄዎቹ ተቀዳሚ የቤት ሥራ የሚሆነው ይህን ስኬታማ ስብስብ ለቀጣይ አመት ይበልጥ ማነቃቃት ይሆናል። በሀገራችን እግርኳስ ክለቦች ለዓመታት ውጤታማ ሆኖ መዝለቅ ከቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ ሌሎች የሊጉ አሸናፊ መሆን የቻሉ ቡድኖች አሸናፊ ከሆኑበት የውድድር ዘመን ቀጥሎ በሚመጣው የውድድር ዘመን የቀደመው የስኬት ረሀብ “Ambition” በተወሰነ መልኩ መቀዛቀዞችን ሲያሳይ፤ በዚህም የተነሳ በበቂ መጠን ቡድኖቻቸውን ማጠናከር ባለመቻላቸው ሆነ የተጫዋቾች ተነሳሽነት ከመቀነስ ጋር ተያይዞ ቡድኖች የነበራቸውን የሜዳ ላይ ብቃት እና ውጤታማነት ጠብቀው ለመቀጠል ሲቸገሩ ይስተዋላል።
በመሆኑም ቡድኑ ዘንድሮ ያሳየውን ጥንካሬ በቀጣዩቹ ዓመታት እንዲደግም የክለቡ አመራሮች ሆነ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የቡድኑን የተፎካካሪነት ደረጃ የሚያስጠብቁ ከተቻለም የሚያሳድጉ ተጫዋቾችን ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይ ቡድኑ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በነበረው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ከቅድመ ማጣርያዎች ያለፈ ጉዞ አልነበረውም። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫው አንድ ደረጃ ከፍ ባለው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እንደመሳተፉ ለዚህ ውድድር የሚመጥን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መሥራት ይኖርባቸዋል።
ዋንጫን ከማሸነፍ ይልቅ በቀጣዩ ዓመት ስኬትን የማስጠበቁ ነገር ከባድ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም በክለቡ አመራሮች ዘንድ ክለቡን ይህን ስኬት በማስመዝገቡ የተፈጠረን መነቃቃት ወደ ሀብት በመቀየር ቡድኑን በቋሚነት ሊጠቅም ወደሚችሉ ጉዳዮች ለማስገባት ጥረቶች መጀመራቸው እሰየው የሚያስብል ሲሆን በቀጣዩቹ ዓመታት ቡድኑ በእግርኳሳችን በሜዳም ከሜዳ ውጭ ያለውን ተፅዕኖ በማሳደግ ወደ ታላቅነት መሸጋገር ይኖርበታል።
👉 ከእቅድ በላይ ያሳካው ኢትዮጵያ ቡና
በ2011 ክረምት ነበር የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቦርድ ለሀገራችን እግርኳስ ያልተለመደ የሆነን ውሳኔ ያሳለፈው። በዚህም የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች እና አሰልጣኝ የነበረውን ካሣዬ አራጌን ዳግም ወደ ኃላፊነት በማምጣት ለሀገራችን እግርኳስ እንግዳ በሆነ መልኩ የአራት ዓመት ውል በመስጠት ኢትዮጵያ ቡናን የተሻለ የማድረግ ሥራቸውን የጀመሩት።
በውል ስምምነቱ ላይ እንደተገለፀው የመጀመሪያው የውድድር ዘመን ከአሰልጣኙ ብቸኛ ይጠበቅ የነበረው ቡድኑን በሊጉ ማቆየት ብቻ ነበር። አሰልጣኙም ቡድኑን በቀጣዩቹ ዓመታት በሊጉ የተሻለ መገለጫ ያለው ቡድን ለማድረግ እና በተባለ ደረጃ ሊጉን ለመልድ ጊዜ ሳይወስድበት ተስፋ ሰጪን የውድድር ዘመን በመጀመሪያው ሙሉ የውድድር ዘመን ቆይታ አስመስክሯል። እዚህ ላይ ታዲያ ዓምና የተሰረዘው የውድድር ዘመን ምንም እንኳን ባይጠናቀቅም ለቡድኑ ነገሮችን ለመታዘብ እድል መስጠቱ ሳይዘነጋ ማለት ነው።
ከየተያዘው የአራት ዓመት ትልም ውስጥ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን ከተቀመጠው ግብ በተቃራኒ ቡድኑ በመጀመሪያው ሙሉ የውድድር ዘመን በሊጉ በ41 ነጥቦች በሁለተኝነት በማጠናቀቅ የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫን ተሳትፎን ማረጋገጥ ችለዋል። ይህም ውጤት ከአራት ዓመቱ ትልቁ ትልም አንፃር በመጀመሪያው የውድድር ዘመን ቡድኑ በሁለተኝነት ማጠናቀቁ ከእቅድ በላይ የተመዘገበ ስኬት ነው።
የአዳዲስ ሀሳቦች እጥረት በነበረበት ሊጋችን ላይ አንዳች የራሱ የሆነ መገለጫ የሆነን የጨዋታ መንገድ ለመገንባት ጥረት እያደረገ የሚገኘው ቡድን በርከት ያሉ አዳዲስ ፊቶችን እንዲሁም በሌሎች የሊጉ ክለቦች በነበራቸው ቆይታ እምብዛም ውጤታማ ያልነበሩ ተጫዋቾች በማሰባሰብ ቡድኑ በውድድሩ የመጨረሻ ክፍሎች በተወሰነ መልኩ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተቸገረ እንጂ ጥሩ የውድድር ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል።
ከ2004 ወዲህ ከአስር ዓመታት ቆይታ በኃላ ዳግም በ2014 የውድድር ዘመን ወደ አፍሪካ የውድድር መድረክ የተመለሰው ቡድኑ በቀጣይ የውድድር ዘመን የጨዋታ መንገዱን ይበልጥ ለማጎልበት የሚረዱ ጥራታቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾች የሚያዘዋውር ከሆነ ቡድኑ በቀጣይ ዓመት ይበልጥ አድጎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
👉 ሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመናቸውን ያለዋንጫ ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ
በኢትዮጵያ የክለቦች እግርኳስ ታሪክ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃ በስኬት ያሸበረቀ ቡድንን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው. ሊጉ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት ከ1990 አንስቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሳተፈባቸው ሃያ ሁለት የውድድር ዘመናት በአስራ አራቱ የሊጉን ዘውድ በመድፋት ማጠናቀቅ ችሏል። በዚህም በተከታይነት ሁለት ሁለት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ከሚከተሉት ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድኖች ጋር ስናወዳድር የክለቡ በሀገሪቱ ክለቦች ላይ ያለውን የበላይነት በግልፅ መመልከት ይቻላል። ታድያ ይህ ክለብ አሁን ላይ ግን ከስኬት ከራቀ ሦስተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ ከ2006 እስከ 2009 የውድድር ዘመን በተከታታይ ለአራት ዓመታት የሊጉ አሸናፊ በመሆን ብሎም ከ2000 እስከ 2002 የውድድር ዘመን በተከታታይ ለሦስት የውድድር ዘመናት በተከታታይ አሸናፊ በመሆን ከፃፋቸው ደማቅ ታሪኮች በተቃራኒ ቡድኑ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ያለዋንጫ በማጠናቀቅ አሉታዊ ታሪክን ፅፏል።
ታድያ ከዚህ የሦስት ዓመታት የክለቡ ውጤት አልባ ጉዞ በስተጀርባ መሰረታዊ የሚባለውን ችግር ማወቅ ግን እጅግ በጣም አስቸጋሪ ይመስላል። ከቡድኖች ውጤታማነት በስተጀርባ ጠንካራ እና ጥራት ያለው ስብስብ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ መመዘኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተመለከትነው ለሁለት ቡድንነት የቀረበ የጥራታቸው ደረጃ ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን ያሰባሰበ ቡድን ነው።
በስብስብ ጥራት ጉዳይ ጥያቄ የማይነሳበት ቡድኑ ይህ ስብስብ ውጤታማ አንዳይሆን ያገደው አንዳች ከበስተጀርባ ያለ ምክንያት እስከሌለ ድረስ የዘንድሮው የውድድር ዘመን በገለልተኛ ሜዳዎች ያለደጋፊዎች እንደመደረጉ እና የቴሌቪዥን ሽፋን በማግኘቱ በቀደሙት ዓመታት በስሞታ መልክ እንደሚቀርበው ጨዋታዎችን ለማሸነፍ በሜዳ ውስጥ ካሉ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ባለፈ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ውጭያዊ ተፅኖች አለመኖርን ተከትሎ የተሻለ የስብስብ ጥራት ካለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ብዙ ተጠብቆ ነበር። ነገርግን ቡድኑ በዚህ ደረጃ ወጣ ገባ የሆነ አቋምን አሳይቶ በሊጉ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ግን የክለቡ ሰዎች ሌሎች ሊመረምሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ የሚጠቁም ነው።
ጥሩ ስብስብ ካለ ይህን ስብስብ እያዘጋጀ ወደ ውጤት የሚመራ ጥሩ አሰልጣኝ አስፈላጊነቱ እንዲሁ የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን ያለፉት ዓመታት የቡድኑ የአሰልጣኞች ቅጥር ሁኔታ በራሱ በግልፅ መፈተሽ የሚገባው ነው። በቀደሙት ዓመታት ቡድኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በክለቡ አመራሮች እና በቴክኒክ ኮሚቴው ጥቆማ የተጫዋቾችን ዝውውር ካጠናቀቂ በኋላ ለሀገራችን እግርኳስ ባይተዋር የሆነ የውጭ አሰልጣኝን የመቅጠር ዝንባሌ በከፍተኛ ደረጃ ቡድኑን ዋጋ ሲያከፍል ቆይታል።
አሁን ላይ ግን በተወሰነ መልኩ ከዚህ አካሄድ የተላቀቀ ይመስላል። እንግሊዛዊው ፍራክ ናታል በውድድሩ አጋማሽ እንደመምጣቱ ለቀጣይ ዓመት ሥራዎቹ በተወሰነ መልኩ ነገሮችን የሚያቀልለት ይመስላል። ነገርግን ሌላው ቡድኑን ሁሌም ቢሆን ሽግግር ውስጥ የሚከተው ለአሰልጣኞች ጊዜ ሰጥቶ የጀመሩትን ሥራ ውጤት በመመልከት ረገድ ቦርዱ ያለው ትዕግሥት አልባነት ሳይዘነጋ ማለት ነው።
በዓለም እግርኳስ በቀደሙው ጊዜ ታላላቅ የነበሩ ቡድኖች ቀስ በቀስ በጊዜ ሂደት ከታላቅነታቸው ተንሸራተው መደበኛ ቡድኖች ሲሆኑ ተመልክተናል። ይህም በሒደት ቡድኖቹ ያላቸውን አስፈሪነት (fear factor) ብሎም ሽንፈትን በሂደት በመለማመድ በሚመጣ የስነልቦና ውድቀት የሚከሰት ነው። አሁን ላይ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አብዛኞቹ የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥሙ በቀደሙት የውድድር ዘመናት ከነበረው በተቃራኒ ማሸነፍ እንደሚችሉ ማመን ጀምረዋል ታድያ ይህ የሚቀጥል ከሆነ ለቡድኑ መጪው ጊዜ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስላል።
በመሆኑም በክለቡ ዙርያ ያሉ ሁሉም አካላት ይህንን ውጤት አልባ ጉዞ እንደ መማርያ እና ቡድናቸውን ወደ ተሻለደረጃ ለማስፈንጠር እንደ መነሻ በመውሰድ በስክነት ውስጥ ሆነ በመነጋገር እና ለተግባራዊ መፍትሔም በመንቀሳቀስ ይህን ታላቅ ቡድን ዳግም ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ መትጋት ይኖርባቸዋል።
👉 አማካይ ስብስብ አመርቂ ውጤት – ሀዋሳ ከተማ
የውድድር ዘመኑ ሲጀምር ብዙዎች የዘንድሮውን የሀዋሳ ከተማ ቡድንን በጥርጣሬ ተመልክተዋል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተሻለ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ያላዛወረው ቡድኑ ጥቂት ባለልምድ ተጫዋቾችን በሚፈለገው ደረጃ እምርታ ማሳየት ካልቻሉ የክለቡ የእድሜ እርከን ቡድን ከተገኙ ተጫዋቾች ጋር በማዋሀድ ነበር የውድድር ዘመኑን የጀመሩት። ነገርግን በተለይ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት በተጋጣሚዎቻቸው ፍፁም የበላይነት እየተወሰደባቸው ያስተናገዷቸው አሰቃቂ ሽንፈቶች ብዙዎች እንዲጠራጠሩት ያስገደደው ሀዋሳ በሊጉ ፍፁም አስቸጋሪ ጊዜ እንዳያሳልፍ ተሰግቶለት ነበር።
ነገርግን ቡድኑ በተለይ በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያ ቡናን በአዲስ አበባ ስታዲየም የረቱበት ጨዋታ የቡድኑን ተጫዋቾች የስነልቦና ደረጃ ያነቃቃች እና የሀዋሳ ከተማን የውድድር ዘመን መልክ የቀየረ ጨዋታ ነበር። በሂደት ቡድኑም በሙሉጌታ ምህረት ተለዋዋጭ የጨዋታ አቀራረብ ውስጥ መሻሻሎችን በማሳየት ከውድድሩ መጀመር በፊት የተሰጡትን ግምቶች በሙሉ አፋልሶ በ35 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።
ቡድኑ በተለይ በሊጉ ከጨዋታ ሳምንት ሳምንት ይበልጥ እያደገ በመምጣቱ እንደሌሎች ቡድን የተጋነነ ወጪ ሳያወጣ እጁ ላይ ያለትን ግብአቶች ተጠቅሞ ጠንካራ እና ተፎካካሪ የነበረን ቡድን በመገንባት ለዚህ በመብቃቱ በክለቡ ዙርያ ላሉ አካላት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ከዚህ ስኬት በስተጀርባ በውድድር ዘመኑ ጅማሮ አካባቢ በክለቡ ዙርያ የነበረውን የስጋት ደመና ተወግዶ ቡድኑ የውድድር ዘመኑ አንገቱን ቀና አድርጎ መውጣቱ ከዘንድሮ የሊጉ ክስተቶች አንዱ ሆኖ የሚቀመጥ ይሆናል።
👉 ሀዲያ ሆሳዕና አካሄዱን ይቀይር ይሆን?
የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ አስቀድሞ የቀድሞውን የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩትን አሸናፊ በቀለን ጨምሮ ከደርዘን በላይ በላይ ተጫዋቾች ከአዳማ ከተማ በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ የማዘዋወራቸው ጉዳይ ከፍተኛ መነጋገርያ እንደነበር ይታወሳል። በሊጉ ጥሩ አጀማመር ያደረገው ቡድኑ ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ክለቡ ከተጫዋቾቹ ጋር አለመግባባቶች መፈጠር የጀመሩ ሲሆን ይህም አድጎ የተጫዋቾች እና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከልምምድ እስከማቆምም ድረስ ደርሶ ነበር።
ታድያ ይህ ልምምድ የማቆም ጉዳይ በክለቡ አመራሮች እና ተጫዋቾች መካከል ከፍ ወዳለ መካረር አምርቶ በዚህ ሂደት ተካፍለዋል ያላቸውን አካላት ክለቡ ማገዱ ይታወሳል። በዚህም የተፈጠረውን የተጫዋቾችን ክፍተት ለመሙላት በዘንድሮው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ጫና የተቋቋመው የቡድኑ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አፋጣኝ ምላሽን ይዞ መቅረብ ችሏል።
ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን 3-0 የረቱበት እንቅስቃሴን እንዲሁም በጥቅሉ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የቡድኑ ወጣት ተጫዋቾችን አስደናቂ ብቃት ለተመለከተ ቡድኑ እነዚህ ተስፈኛ ተጫዋቾች ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ መሥራት የሚችል ከሆነ የተሻለ ቡድንን በአነስተኛ ወጪ መገንባት የሚችልበት እድል ሰፊ ስለመሆኑ ተመልክተናል።
በመሆኑም የቡድኑ አመራር የሀገራችን እግርኳስ ችግር ውስጥ እየከተተ ከሚገኘው ተጫዋቾችን ለአጭር ጊዜ ዕቅድ በከፍተኛ ገንዘብ ከዓመት ዓመት በገፍ የማዘዋወር እሳቤ ተላቀው እነዚሁኑ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ወጣት እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ ተጫዋቾች የቡድኑ ተቀዳሚ ዕቅድ አካል በማድረግ ለሌሎች ቡድኖች ምሳሌ የሆነን ፈር ቀዳጅ ውሳኔን ወስኖ ሊንቀሳቀስ ይገባል።
👉 የወረዱት ቡድኖች መፃኢ ተስፋ
ከፕሪሚየር ሊጉ የወረዱት አዳማ ከተማ ፣ ጅማ አባጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ ምንም እንኳን በቀጣዩ የውድድር ዘመን ወደ ሊጉ ሊመለሱ የሚችሉበት እድል ጠባብ ይሁን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ባይሟጠጥም ነገሮች ከተገመቱት በተቃራኒ እንኳን ቢሄዱ ለመጪው ጊዜ ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
የመለያ ጨዋታዎች ጉዳይ በትግራይ ክለቦች የመሳተፍ እና ያለመሳተፍ ጉዳይ ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ቡድኖቹ በፍጥነት ዳግም ወደ ሊጉ ሊመለሱባቸው ስለሚችሉበት አግባብ ከወዲህ እንቅስቃሴዎችን መጀመር ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከፕሪምየር ሊጉ ፍፁም የተለየ ባህሪ ያለው ውድድር እንደመሆኑ ቡድኖች ከፍተኛ ፍጥነት እና ጉልበት እና ፍትጊያዎችን ለሚፈልገው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ስብስቦቻቸውን ዳግም በመቃኘት በፍጥነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ስራዎችን ከወዲሁ መጀመር ይኖርባቸዋል።
ከጨዋታ መንገድ ይልቅ ውጤት አጥብቆ በሚፈልግበት እና ሁሉም ውድድሮች የፍፃሜ ያክል ዋጋ ባላቸው በዚህ ውድድር ቡድኖች በፍጥነት ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ ካልቻሉ ተለዋዋጭ በሆነው የኃይል ሚዛን ሌሎች በፋይናንስ ፈርጠም ያሉ የከተማ አስተዳደር ቡድኖች የፉክክር ሚዛን እየተወሰደባቸው በውድድሩ የቁጥር ሟሟያ እንዳይሆኑ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መሥራት ይኖርባቸዋል።
👉 ከረፈደ የተሻሻለው አዳማ ከተማ
በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛው ሳምንት ላይ መውረዳቸውን ያረጋገጡት አዳማ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ሳምንታት እያሳዩ ያሉት እንቅስቃሴ ትኩረትን ስቧል። በእርግጥ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር አዲስ አሰልጣኝ እና አዳዲስ ተጫዋቾች በማምጣት ደካማውን አካሄዱን ለማስተካከል ጥረት አድርጓል። ያም ቢሆን ‘የሁለተኛውን ቡድን’ አዋህዶ ጠንካራ በማድረግ ከመውረድ ለመትረፍ ያደረገው ጥረት መሳካት አልቻለም። ያም ቢሆን በተለይ መውረዱን ካረጋገጠ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳያት የወረደ ቡድን መሆኑን የሚያስረሳ ፉክክር ሲያደርግ ታይቷል።
ቡድኑ ከድሬዳዋ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ መውረዱ ዕውን ሲሆን በመቀጠል ሀዋሳ ከተማን ገጥሞ ማሸነፍ ችሏል። በሰበታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፈባቸውም ጨዋታዎች እንደመጀመሪያው ዙር ደካማ አቋም አላሳየም። በዚህ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥሙ ደግሞ እስከ መጨረሻው ድረስ 1-0 መምራት ችለው በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ነበር ነጥብ የተጋሩት። የቡድኑ ተሰላፊዎች በሊጉ አለመቆየታቸውን ካረጋገጡ በኋላ በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ ራሳቸውን በነፃነት ለመግለፅ መቻላቸው ለቡድኑ መሻሻል መነሻ የሆነ ይመስላል። ሁኔታውን ላጤነም ‘ይህ ለውጥ ቀደም ብሎ መጥቶ ቢሆን ኖሮ አዳማ በሉጉ ይቆይ ነበር ?’ የሚል ጥያቄን ያጭራል።