የውድድር ዘመኑ መጋረጃ መዝጊያ በነበረው 26ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው የትኩረት ማዕከል የነበሩ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 ሐት-ትሪክ ሠሪው አማካይ – ሐይደር ሸረፋ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት መውረዱን ያረጋገጠውን ወልቂጤ ከተማን 3-2 ሲረቱ አማካዩ ሐይደር ሸረፋ የትኩረቶች ሁሉ ማዕከል ነበር። በ2013 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ሐት-ትሪክ የሠራ የአማካይ ተጫዋች መሆን የቻለው ሐይደር በጨዋታው ቡድኑ ያሸነፈባቸውን ሦስት ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል።
መቐለ 70 እንደርታን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተቀላቀለ ወዲህ ከጥልቀት በመነሳት በቅዱስ ጊዮርጊስን የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በጎ ተፅዕኖን እያሳረፈ ይገኛል። በግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖረውም በአጠቃላይ የቡድኑ የማጥቃት ሒደትን በማስጀመር እንዲሁም የተመጠኑ ረጃጅም ኳሶችን እንዲሁ ለቡድን አጋሮቹ በማድረስ ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ አሳልፏል።
በተጨማሪም ተጫዋቹ በማጥቃቱ ወቅት ዘግይቶ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ አደጋ የሚፈጥርበት መንገድ የተለየ ነው። እጅግ አስደናቂ የውድድር ዘመን የማሳረጊያ ጨዋታ ያሳለፈው ተጫዋቹ ሁለት እጅግ ማራኪ የሆኑ ግቦችን እንዲሁም በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል መጠለፉን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።
👉 መጥፎ ቀን ያሳለፈው ወንድወሰን አሸናፊ
በተሰረዘው የውድድር ዘመን በስሑል ሽረ ጥሩ ቆይታን ማድረግ የቻለው የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና የግብ ዘብ የነበረው ወንድወሰን አሸናፊ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ወልዋሎ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የውድድር አጋማሹን ክለብ አልባ ሆኖ ቢያሳልፍም በውድድሩ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ድሬዳዋ ከተማን መቀላቀል ችሏል።
ምንም እንኳን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማን ቢቀላቀልም እስከ ሊጉ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት መሰለፍ ሳይችል ቀርቷል። መሰለፍ እድልን ባገኘበት እና ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ የ3-0 ሽንፈትን ባስተናገደበት ጨዋታ ተጫዋቹ ከይፋዊ የፉክክር ጨዋታዎች መራቁ ባሳደረበት ተፅዕኖ በሚመስል መልኩ ከባባድ ስህተቶችን የፈፀመበትን የጨዋታ ቀን አሳልፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በ35ኛው ደቂቃ የሀዋሳው የመስመር አጥቂ መስፍን ታፈሰ በደካማው የግራ እግሩ ከግራ መስመር ያሻማውን ቀላል ኳስ መቆጣጠር ተስኖት ግብ ያስተናገደው ግብጠባቂው በ41ኛው ደቂቃ እንዲሁ ኳስ ከኋላ ለማስጀመር መገኘት በማይገባው ስፍራ ተገኝቶ በጫና ውስጥ ለቡድን አጋሩ ኳስ ለማቀበል ሞክሮ የተሳሳተው አደገኛ ኳስ የቡድን አጋሩ ፍሬዘር ከግቡ አፋፍ አዳናት እንጂ ለሁለተኛ ግብ ምክንያት ለመሆን ቀርቦ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማአገኝ ኃይሉ ባስቆጠራት የሀዋሳ ግብ ላይ የነበረው የጊዜ እና የቦታ አያያዝ ችግሮች ለግቡ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሲሆን በተመሳሳይ በተጨማሪ ደቂቃ ላውረስ ላርቴ ከሜዳ አጋማሽ ግቡን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የሞከረው እና ወንድወሰን እንደምንም ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ የተጫዋቹ ስህተቶች ነበሩ።
👉 ዳግም የተወለደው መሐሪ መና
ሁለት መልኮች በነበሩት የሲዳማ ቡና የውድድር ዘመን ላይ ትኩረት ሳቢ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል መሐሪ መና አንዱ ነው። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ፣ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር ተከላካይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው የመጨረሻ ወቅቶች ለረጅም ጊዜ በጉዳት አገልግሎት መስጠት ያልቻለ ሲሆን ዘንድሮ ለግማሽ ዓመት ያለ ክለብ አሳልፎ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ የእግርኳስ ህይወቱ ያበቃለት መስሎ የነበረው መሐሪ መና በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ከዚህ ቀደም ለተጫወተበት ሲዳማ ቡና ከፈረመ ወዲህ ዳግም አብቦ ታይቷል። እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴን ለተመለከተም ለረጅም ጊዜ ከፉክክር ጨዋታ የራቀ ተጫዋች አይመስልም ነበር።
ከፍተኛ ግለት በነበረው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ ሲዳማ ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ ያስቻሉ ሁለት ጎሎች ላይ ተሳትፎ ከማድረጉ ባሻገር መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው መሐሪ በጥቅሉ ክለቡን ከተቀላቀለ ወዲህ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ያልሆነ ቀን ያሳለፈበትን ጨዋታ ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው።
ከቡድኑ አጨዋወት ጋር በፍጥነት የተዋሀደው መሐሪ በአጠቃላይ በቀጣዩ ዓመት ይበልጥ የብቃቱ ጫፍ የነበረበት ጊዜን የሚያስታውስ አቋሙን ዳግም እንደሚያሳይ ፍንጭ የሰጠበትን ጊዜ አሳልፏል።
👉 አህመድ ሁሴን ይህ ነውን ?
የተሻለ አጥቂ የመሆን እምቅ አቅም ያለው ስለመሆኑ ብዙዎች ያናገሩለታል። ነገርግን አህመድ ሁሴን አሁንም ቢሆን ከእምቅ አቅምነት ባለፈ በሚገባው ደረጃ ራሱን እያሻሻለ ይገኛል ብሎ ለመናገር ግን አይቻልም።
የአስደናቂ ፍጥነት እና ጉልበት ባለቤት የሆነው አጥቂው ከጨዋታ ጨዋታ ተስፋ የሚጣልበት የግብ አምራች መሆን አልቻለም። ለዚህም በተወሰነ መልኩ የቡድኑ ኳስን መሠረት ያደረገ አጨዋወት ተግዳሮት ቢሆንበትም በግሉ በአጨራረስ ረገድ አሁንም ከሚጠበቅበት እጅጉን ባነሰ የስኬት ደረጃ ላይ ይገኛል።
ነገርግን በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ምንም እንኳን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢሸነፍም በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ አንጠልጥሎ ግሩም ግብ ያስቆጠረው ተጫዋቹ በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁ ሦስት የጊዮርጊስ ተከላካዮችን አልፎ ያስቆጠረበት መንገድ አስገራሚ ነበር።
ከሁለቱ ግቦች ውጭ መልካም እንቅስቃሴን ያደረገው አህመድ እስከዛሬ ከተመለከትነው ማንነቱ በጊዮርጊሱ ጨዋታ የተመለከትነው አህመድ እጅግ የተሻለው ነበር። ታድያ ይህም ጨዋታ እምቅ አቅሙን አውጥቶ መጠቀም ቢችል የተሻለው አህመድ ሁሴን ምን ያህል አስፈሪ አጥቂ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ ጨዋታ ነበር።
👉የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በመጨረሻ ሳምንት ያደረጉ ተጫዋቾች
ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ አይነተኛ ሚናን የተወጣው ግብጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ ወዲህ ግን እስካሁን የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቆይቷል። በተሰረዘው የውድድር ዘመን የዳንኤል አጄይ ተጠባባቂ የነበረው ግብጠባቂው ዘንድሮ ደግሞ ከምንተስኖት አሎ እና ፋሲል ገብረሚካኤል ቀጥሎ የቡድኑ ሦስተኛ ግብጠባቂ በመሆን የውድድር ዘመኑን አሳልፏል። ነገርግን ቡድን በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ከሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የመሰለፍ እድል አግኝቶ የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን አድርጓል።
በዚሁ ጨዋታ ላይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ክለቡን የተቀላቀለው ታዳጊው ቶማስ ትዕግስቱ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍ ችሏል።
በመጀመሪያው ዙር ክለብ አልባ የነበረው እና በአጋማሹ ጅማን የተቀላቀለው ግብጠባቂው በረከት አማረ እንዲሁ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ለክለቡ የመጀመሪያው ጨዋታ ሲያደርግ ተከላካዩ ላውረንስ ኤድዋርድ ለአዳማ ከተማ፣ ተስፋ የተጣለበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ዳግማዊ አርዓያ (በቋሚነት)፣ የሀዋሳው ግብጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ፣ የድሬዳዋዎቹ ሚኪያስ ካሣሁን እና ቢኒያም ጥዑመልሳን (በቋሚነት) እና ሳሙኤል ዘሪሁን (በቋሚነት) የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።
👉 ደምቀው የዋሉት የሀዲያ ሆሳዕና ተስፈኞች
የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቡድናቸው ሰበታ ከተማን ሲገጥም ያደረጉት በድንገት ከሀዲያ ሆሳዕና የ20 ዓመት በታች ቡድን ወደ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች የተሸጋገሩት ተስፈኞቹ ወጣቶች እጅግ ፈጣን የሚባል መሻሻልን ባለፉት ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት አሳይተዋል።
ከጨዋታ ጨዋታ ቀስ በቀስ የመላመድ ምልክትን ያሳዩት ተጫዋቾቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው ጅማ አባጅፋርን 3-0 ሲረታ ጥሩ ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን ስድስት ተጫዋቾች በቋሚነት ሁለት ተጫዋቾች ከተጠባባቂነት ተነስተው ቡድናቸውን ማገልገል በቻሉበት ጨዋታ እንዳለ ዓባይነህ እና ተመስገን ብርሃኑ ሁለቱን ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።
👉 ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ተቀያሪዎች በመጀመርያ ተሰላፊነት…
በዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተቀይረው በመግባት በጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር መነጋገርያ የሆኑት ዱላ ሙላቱ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ይገዙ ቦጋለ በዚህ ሳምንት የመጀመርያ ተሰላፊ ሆነው ተጫውተዋል።
በእርግጥ የሀዲያ ሆሳዕናው የመስመር ተጫዋች ዱላ ሙላቱ በቡድኑ በተፈጠረው ትርምስ አስራ አምስት ተጫዋቾች አለመኖራቸውን ተከትሎ በተከታታይ ጨዋታዎች በመጀመርያ ተሰላፊነት እየተጫወተ ይገኛል። በዚህ ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ ግሩም የሆነ ቀን ያሳለፈው ዱላ የመክፈቻውን ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለሁለተኛው ጎል ማመቻቸት ችሏል። በጨዋታው ያሳየው እንቅስቃሴም ፈጣን እግሮቹ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት የጨዋታ ፍጥነት በተዳከመበት ሰዓት ተቀይሮ በመግባት ብቻ ሳይሆን ከጅምሩም ሲሰለፍ እንደሆነ ያሳየ ነበር።
ሌላው በመጀመርያ ተሰላፊነት ግሩም ቀን ያሳለፈው ይገዙ ቦጋለ ነው። በጉዳት ካሳለፈው አስከፊ ጊዜ አገግሞ ዳግም ቀና ያለው አጥቂው ባለፉት ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት ጎሎችን አስቆጥሮ የነበረ ሲሆን ከወላይታ ድቻ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ መግባት ችሏል። ቡድኑ አሸናፊ የሆነባቸው ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሩም ወቅታዊ አስደናቂ አቋሙ በአጋጣሚ የመጣ እንዳልሆነ ያሳየ ነበር።
ሰበታ ከተማ አሁን ያለበትን ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉ ድሎች ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተው ወጣቱ ዱሬሳ ሹቢሳ በዚህ ሳምንት በመጀመርያ ተሰላፊነት ጀምሯል። ሆኖም ከዚህ ቀደም ተቀይር ሲገባ የነበረው ተፅእኖ ሳይታይ ቀርቷል። በእርግጥ አጠቃላይ ጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ የተደረገበት በመሆኑ ዱሬሳ ተለይቶ ጥሩ ብቃት እንዲያሳይ መጠበቅ የማይቻል ነው።