ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ26ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎችን በመንተራስ ሶከር ኢትዮጵያ ይህንን የምርጦች ቡድን ሰርታለች።

አሰላለፍ: 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ተክለማርያም ሻንቆ – ኢትዮጵያ ቡና

በመጨረሻው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከታዩ የግብ ዘቦች መካከል በአንፃራዊነት የተሻሉ ዕድሎችን ሲያመክን የታየው ተክለማርያም ሻንቆ ነው። እርግጥ ተጫዋቹ በ12ኛው ደቂቃ የፈፀመው የኳስ ቅብብል ስህተት ዋጋ ሊያስከፍለው የነበረ ቢሆንም ስህተቱን ለማረም ሁለተኛ ዕድል አግኝቶ ኳሱን ተቆጣጥሮታል። ከዚህ ውጪ በጨዋታው ጠንካራ የነበሩት የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች የሰነዘሯቸውን ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ኳሶችን ከመረብ ጋር እንዳይገናኙ ያደረገበት መንገድ መልካም ነበር።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ቡድኑ ወልቂጤ ላይ ድል ሲቀዳጅ የነበረው ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ነበር። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ተሳትፎ በጨዋታው ሲያደርግ የነበረው ተጫዋቹም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሲያደርጋቸው የነበሩ የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ለወልቂጤዎች ፈታኝ ነበሩ። ከምንም በላይ በጨዋታው በአብዛኛው ወደ ቀኝ ያዘነበሉ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ለነበረው ቡድኑም የሄኖክ ሩጫዎች ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። በተጠቀሰው አጨዋወትም ሁለተኛውን ጎል ሀይደር እንዲያስቆጥር የመጨረሻ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

ላውረንስ ኤድዋርድ – አዳማ ከተማ

በመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለክለቡ (ግማሽ ዓመት ላይ ክለቡን ተቀላቅሎ) ያደረገው ላውረንስ ኤድዋርድ ከጨዋታ የራቀ እስካይመስል ድረስ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። ቁመታሙ ተከላካይ በጨዋታው ኳሶችን በማቋረጥ፣ በማስጣል፣ በመመለስ እንዲሁም በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ቡና የሚነሱ የመሐል ለመሐል ጥቃቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የአምሮ እና የአካል ፍጥነት ላይ ሆኖ ሲጫወት ታይቷል። ከዚህ ውጪ አብረውት ከነበሩት የቡድን አጋሮቹ ጋር ሲናበብ የነበረበት መንገድ የሊጉ ብዙ ጎል አስተናጋጁን ክለብ ለአንድ ጨዋታም ቢሆን ጠጣር አድርጎት ነበር።

በረከት ወልደዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና

የአሠልጣኝ እያሱ መርሀፅድቅ ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ነጥብ እና ጎል ከጅማ ሲያገኝ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። እርግጥ በጨዋታው ጅማዎች የሰላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባያስመለክቱም በዋናነት ግብ ለማስቆጠር ሲጠቀሙበት የነበረውን ተሻጋሪ ኳሶች በማምከን፣ በማውጣት እና በማፅዳት በረከት መልካም ስራን ሰርቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የጅማ ተጫዋቾች የቆሙ ኳሶችን በምቾት እንዳይጠቀሙ ሲከለክል ታይቷል። ከዚህ ውጪ ጅማዎች ሲሰነዝሯቸው የነበሩትን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እርጋታን በተሞላበት አጨዋወት ሲያከሽፍ የነበረበት መንገድ ድንቅ ነበር።

መሐሪ መና – ሲዳማ ቡና

በ26ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሀሪ መና ነው። በተሰለፈበትን ግራ መስመር አልቀመስ ብሎ የታየው መሀሪ በአራቱም የጨዋታ ወሳኝ እንቅስቃሴዎች (ማጥቃት፣ መከላከል፣ ከማጥቃት ወደ መከላከል እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት ያሉ ሽግግሮች) የነበረው ብቃት ድንቅ ነበር። በተለይ የተሳኩ ምጣኔ ያላቸው ኳሶችን ወደ ሳጥን በማሻገር እና የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎችን በማሸነፍ ለቡድኑ ጠቀሜታን ሲያመጣ ነበር። ተጫዋቹ ይገዙ ቦጋለ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ላይም ቀጥተኛ (አንዱን አሲስት በማድረግ) ተሳትፎን አድርጓል።

አማካዮች

ኢሊሴ ጆናታን – አዳማ ከተማ

የአዳማ ከተማው የተከላካይ አማካይ ኢሊሴ ጆናታን ሌላው ጥሩ ጊዜ በሳምንቱ ያሳለፈ ተጫዋች ነው። የቡድኑን ሚዛን በመጠበቁ ረገድ የተዋጣለት ጊዜ የነበረው ጆናታን የተከላካይ ክፍሉ እንዳይጋለጥ በአብዛኛው በራሱ ሜዳ ተገድቦ ሲንቀሳቀስ ታይቷል። በተለይም የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ መስመር እና የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች የሚገናኙበትን መስመር ለመዝጋት ሲታትር ተስተውሏል። ጆናታን በመከላከሉ እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቁ ረገድ ብቻ ሳይሆን የሚያቋርጣቸውን ኳሶች በቶሎ ወደ ፊት በመላክም የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያስጀምር ነበር። ከዚህ አልፎም በ20ኛው ደቂቃ የቡናን ተጫዋቾች የኳስ ቅብብል አቋርጦ በራሱ ከርቀት ወደ ግብ የላከው ኳስ መረብ ላይ ሊያርፍ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

ሐይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ሀይደር ሸረፋ በውድድር ዓመቱ ሀት ትሪክ የሰራ ብቸኛው የአማካይ መስመር ተጫዋች የሆነበትን ሁነት የፈጠረው ቡድኑ ወልቂጤን ሲረታ ነው። በጨዋታው ላይም ተጫዋቹ ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረግ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ድንቅ ነበሩ። ከምንም በላይ ከፍፁም ቅጣት ምቱ ውጪ በተቆጠሩት ጎሎች ላይ ሀይደር ያሳየው የአጨራረስ ብቃት እና የተከላካዮችን አቋቋም አይሰቶ ራሱን ነፃ ያደረገበት መንገድ ድንቅ ነበር። ከጎሎቹ በተጨማሪም የቡድኑን የኳስ ፍሰት በማሳለጥ ረገድ ሀይደር የነበረው ተሳትፎ ከፍ ያለ ነበር።

ወንድማገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከታዩ ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ወንድማገኝ ኃይሉ ሊጉን በጥሩ ብቃት አገባዷል። ቡድኑ ሀዋሳም በመጨረሻ ጨዋታው ሦስት ነጥብ ሲያገኝ የወንድማገኝ ብቃት ለድሬዳዋ ተጫዋቾች ፈተና ነበር። ከምንም በላይ ተጫዋቹ በድሬዳዋ አማካዮች እና ተከላካዮች መሐከል እየገባ በመስመሮች መካከል ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ልዩ ነበር። የሚያገኛቸውንም ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት በማድረስ የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭ ለመሆን ሲታትር ተስተውሏል። ከዚህ በተጨማሪም በ80ኛው ደቂቃም የአምሮ ብስለቱን ያሳየ ጎል አስቆጥሯል።

አጥቂዎች

ዱላ ሙላቱ – ሀዲያ ሆሳዕና

በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ እጅግ ምርጥ ብቃት ላይ ከነበሩ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ዱላ ሙላቱ ነው። ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ዱላ የቡድኑ ሁነኛ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ ከሆነ ሰነባብቷል። በጅማውም ጨዋታ ከመስመር እየተነሳ ሥል፣ ፈጣን እና አደጋቸው ከፍ ያሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ታይቷል። ተጫዋቹም የመጀመሪያውን ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ሁለተኛውን ጎል እንዳለ ዓባይነት እንዲያስቆጥር አመቻችቶ አቀብሏል። ከዚህ ውጪም ተጫዋቹ የተከላካዮችን አቋቋም እየተረዳ ከሚያደርጋቸው የኳስ ጋር እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ከኳስ ውጪም ታትሮ በመጫወት ቡድኑን በመከላከሉ ረገድ ሲያግዝ ታይቷል።

ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተቀይሮ ወደ ሜዳ እየገባ ጎሎችን ያስቆጠረው ይገዙ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ከ12 ጨዋታዎች በኋላ በቋሚነት ተሰልፎ ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉ ሁለት ኳሶች ከመረብ ጋር አዋህዷል። ከምንም በላይ ተጫዋቹ የሚያገኛቸውን የመጫወት ዕድሎች ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። ይሄ ጥረቱም በወላይታ ድቻው ጨዋታ ቀጥሎ ሁለት ጎሎችም አስቆጥሯል። ተጫዋቹም አንዱን ጎል በግንባሩ አንዱን ደግሞ በእግሩ ሲያስቆጥር የታየበት የቦታ እና ጊዜ አጠባበቅ እንዲሁም የአጨራረስ ብቃቱ ልዩ ነበር።

አህመድ ሁሴን – ወልቂጤ ከተማ

ሁለት ድንቅ ጎሎችን በመጨረሻው ሳምንት ያስመለከተን አህመድ ሁሴን የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል። ቁመታሙ አጥቂ ፍጥነት እና ጉልበት የታከለበት አጨዋወቱ ፍሬያማ ሆኖ የታየው በዚህኛው ሳምንት ነበር። እርግጥ ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢረታም ተጫዋቹ በግሉ ያደረገው እንቅስቃሴ የሚያስደንቀው ነው። በ15ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች አፈትልኮ ወጥቶ በግብ ጠባቂው ባህሩ አናት በማላክ እንዲሁም በ63ኛው ደቂቃ ተከላካዮችን በእንቅስቃሴ ሸውዶ መረብ ላይ ያሳረፋቸው ጎሎች ድንቅ ነበሩ።

አሠልጣኝ

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

የሲዳማ ቡናው አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ፉክክሩ እጅግ ከፍተኛ በነበረው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ ቡድናቸው ያሳየው ብቃት አስደናቂ ነበር። በጨዋታውም ቡድኑ ቀደም ብሎ ግብ አስተናግዶ የነበረ ቢሆንም ሳይደናገጥ ወደ ጨዋታ የተመለሰበት ሂደት መልካም ነበር። አሠልጣኙ ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር ለማስከፈት የሚያስችል እንቅስቃሴ ቡድናቸው እንዲከተል በማድረግ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ከእጃቸው የወጣውን ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ ማድረጋቸው የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችንን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።

ተጠባባቂዎች

ያሬድ በቀለ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ደስታ ጊቻሞ (አዳማ ከተማ)
ሄኖክ አርፊጮ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ደሳለኝ ደባሽ (አዳማ ከተማ)
ሚካኤል ጆርጅ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ኤፍሬም አሻሞ (ሀዋሳ ከተማ)
በላይ ዓባይነህ (አዳማ ከተማ)