የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የሚያገኙት ገቢ መጠን ታውቋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ለሊጉ ተሳታፊዎች ያከፋፈለውን የገንዘብ መጠን ታውቋል።

አክሲዮን ማኅበሩ በካፒታል ሆቴል እያደረገ በሚገኘው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሊጉ የስያሜ እና የስርጭት መብቱን በመሸጡ በዚህ ዓመት የተገኘው ገቢ ይፋ የተደረገ ሲሆን በምን መልኩ እንደተከፋፈለም ገለፃ ተደርጓል።

የካምፓኚው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የክፍፍሉን አካሄድ ከሌሎች ሀገራት በተለይም የእንግሊዝ ልምድ መውሰዳቸውን ጠቁመው ከገቢው 60 በመቶ ሁሉም ክለቦች እኩል እንዲከፋፈሉ፣ 25 በመቶ በደረጃቸው እንዲሁም 15 በመቶ ለሊግ ካምፓኒው የስራ ማስፈፀሚያ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል። በመቀጠል ደግሞ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊዋ ወ/ሮ ማስተዋል አስረስ ክፍፍሉን በዝርዝር አብራርተዋል።

እንደ ወ/ሮ መስተዋል ገለፃ ለዚህ ዓመት ከስያሜ እና ስርጭት መብት ሽያጩ የተገኘው አራት ሚልዮን ዶላር በሁለት ጊዜ ክፍያ ለካምፓኒው ገቢ የተደረገ ሲሆን የመጀመርያው ሁለት ሚልየን ዶላር በወቅቱ ምንዛሪ 78,486,400 (ከቫት ጋር) እንዲሁም ቀጣዩ ሁለት ሚልየን ዶላር በወቅቱ ምንዛሪ 84,770,400 (ከቫት ጋር) ገቢ መደረጉን ገልፀዋል። በአጠቃላይም 163,256,800 ብር (ከቫት ጋር) ገቢ ተደርጓል ተብሏል። ከዚህ ውስጥ የተጣራው 141,962,434.78 ብር ሲሆን ለመንግሥት ገቢ የሚደረግ የቫት ተቆራጭ ደግሞ 21,294,365 ብር ሆኗል። 2,839,248 ብር ደግሞ የዊዝሆልድ ተቆራጭ ይሆናል።

ለክፍፍል ከሚውለው የተጣራ ገንዘብ (141,962,434 ብር) ላይ 60% እኩል እና 25% በደረጃቸው መሠረት ተሰልቶ በሚከተለው መልኩ ተፋፍሏል።

ፋሲል ከነማ – 10,346,877
ኢትዮጵያ ቡና – 10,169,424
ቅዱስ ጊዮርጊስ – 9,991,971
ሀዲያ ሆሳዕና – 9,814,518
ሰበታ ከተማ – 9,637,065
ሀዋሳ ከተማ – 9,459,612
ባህር ዳር ከተማ – 9,282,159
ወላይታ ድቻ – 9,104,706
ሲዳማ ቡና – 8,927,253
ድሬዳዋ ከተማ – 8,749,800
ወልቂጤ ከተማ – 8,572,347
ጅማ አባ ጅፋር – 8,394,893
አዳማ ከተማ – 8,217,440

ከዚህ ጋር በተያያዘ ለውድድር ወጪ ከክለቦች በድምሩ 16,761,066 ብር የሚቀነስ ሲሆን ለሁሉም ክለብ በቅድሚያ በድምሩ 24,188,360 ብር መከፈሉ ተገልጿል። ከክፍፍሉ በተጨማሪም ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ እንደ ደረጃቸው 1 ሚልየን, 700 ሺህ እና 500 ሺህ የሚከፈላቸው ይሆናል። ለቀጣይ ዓመት ግን ይህ ሽልማት እንደማይኖርም ተገልጿል።