” የደሞዝ ጣርያው እንዲነሳ ወስነናል” – መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

በተጫዋቾች ላይ የተቀመጠው የደሞዝ ጣርያ እንዲነሳ መወሰኑን እና ውሳኔው ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚቀርብ የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ገልፀዋል።

ዛሬ በካፒታል ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘው የሊግ ካምፓኒው ጠቅላላ ጉባዔ ከተነሱት አጀንዳዎች መካከል በተጫዋቾች ላይ ተጥሎ የቆየው የደሞዝ ጣርያ ጉዳይ ነበር። ነሐሴ 3 ቀን 2011 ቢሾፍቱ ላይ በተደረገ ስብሰባ ላይ የተወሰነው በዚህ አወዛጋቢ ደንብ ዙርያ ጉባዔተኛው ሀሳብ የሰጠበት ሲሆን ሰብሳቢው መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ በሰጡት ሀሳብ ከጅምሩ የሰው ደሞዝ ላይ ገደብ ማውጣት ህገወጥ መሆኑን ጠቅሰው የባሰ ከጠረጴዛ በታች እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል።

በመቀጠል የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ስለ ደሞዝ ጣርያው ድክመቶች ማብራርያ የሰጡ ሲሆን “በአንዳንድ ክለቦች በኤጀንት አማካኝነት በሚደረግ ድርድር የተጫዋቾቹን ደሞዝ በአንድ ጊዜ በማስገባት፤ ለይስሙላ ወይም የሚከፈልበትን 50ሺህ ብር ፔይሮል ሲያስፈርሙ ይታያል። በጣም ጥቂት ክለቦች በፌዴሬሽኑ የተቀመጠውን እና አሰፈላጊውን ጥቅማ ጥቅም ብቻ የሚከፍሉ ሲሆን ሌሎች ክለቦች ደግሞ የተቀመጠውን የደሞዝ ጣርያ በመክፈል እና ጥቅማጥቅም ከፍ በማድረግ ለፊርማ የሚለውን እሳቤ ለማስቀረት ብቻ የሚደረግ ስምምነት አለ። ይህም ውድድሩ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል፣ የተጫዋቾች ዝውውር ፕሮፌሽናል አካሄድ እንዳይኖረው አድርጓል፣ በተጫዋች እና ክለቦች መካከል በየጊዜው አለመግባባት እንዲፈጠር አድርጓል፣ የተወሰኑ ክለቦችን ተጎጂ አድርጓል፣ ክለቦች የሚከፍሉት ደሞዝ እንዳይታወቅ አድርጓል። ” የሚል ይዘት ያለው ማብራርያ ሰጥተዋል።

ቀጥሎ ከክለቦች ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አቶ ነዋይ በየነ ” እንደጊዮርጊስ ከጅምሩም አልተቀበልነውም። ይሄን የሚሞግት ጠንካራ የተጫዋቾች ማኅበር ባለመኖሩ ነው እንጂ ይሄ ልክ አልነበረም። የግለሰቦችን መብትም መንካት ነው፣ ፈረንጆቹ የፋይናንሻል ገደብ ያሉት የየግለሰቡን መብት መገደብ ሳይሆን በአስተዳደር ደረጃ በፐርሰንት ነው የሚቀመጠው። ግለሰቦች ሁሉም እኩል ይከፈላቸው የሚባል አሰራር የለም። ይሄን ስንል በነፃገበያ ስም ዝም ብሎ ይለቀቅም አንልም፣ በጅምላም በብዛት ከፍ ያለ ይከፈል ማለትም ልክ አይሆንም። የተጫዋቾች ኮንትራት አጭር ጊዜ ነው። በቅርቡ ቡና ላይ ነው ያየሁት ከዚያ በላይ። ተጫዋቾቹ ብዙ ጊዜ እሺ አይሉም። ገበያው ያኔ ወደ የት እንደሚሄድ ስለማያውቁት። እንደቀጣሪም የተቀጣሪን ደሞዝ ተሰብስቦ መወሰን ትክክልም አይደለም። ማሰሪያው የሚሆነው ክለቦች ኦዲትድ የሆነ ሪፖርት ለሊግ ሼር ካምፓኒው ቢያቅርቡ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ከቡና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ “አሰልጣኞቻችን፣ የክለብ ኃላፊዎቻችን ለምን አንድ ዓመት እናስፈርማለን በአንድ ዓመት እንዴት ቡድን ይሰራል? ሳለሪ ካፕ የሚባል 50ሺህ የውሸት ስለሆነ ቢቀር። ይህ ሲባል ግን ቅድም ከአቶ ነዋይ እንደቀረበው በዛ አማራጭ ቢታይ” የሚል ይዘት ያለው ሀሳብ አንስተዋል።

ከወልቂጤ ተወካይ በተነሳ ሀሳብ ደግሞ « የሰው መብት ሳንጥስ ገደብ ብናስቀምጥ፣ ሜዠርመንቱ በደንብ መቀመጥ አለበት። የግድ ሁሉም እኩል ይከፈለው አላልንም። የሀዲያ ሆሳዕና ይፋ ስለወጣ ነው እንጂ እኛም ጋር ሁላችንም ችግሩ ነበር። ቤቱ መድፈር አለበት ጣሪያ ለማስቀመጥ።” ሲሉ ሊግ ካምፓኒው የዳሰሳ ጥናት ቢያደርግ፣ ተስፋ ቡድን ላይ ትኩረት ቢደረግ የሚሉ ተሳቦችም ተነስተዋል።

በመጨረሻም በቀረበው አጀንዳ ዙርያ ማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ክለቦች በራሳቸው አቅም በራሳቸው ኪስ ይተዳደሩ፤ ስለዚህም የደሞዝ ጣርያው እንዲነሳ ወስነናል። እያንዳንዱ ክለብ ባለው በራሱ ኪስ እና አቅም እንዲደራደር ወስነናል። ወደላይ ለፌዴሬሽኑ እና ለሚመለከታቸው አካላት እናደርሳለን። አብዛኞቹ ያነሳችሁት ደግሞ ክለቦቻችን ለተጫዋቾች የሚከፍሉትን ደሞዝ ብዙ ድክመት አለው። ስለዚህ የሊግ ካምፓኒው አጥንቶ የመፍትሄ ሀሳብ ያቅርብ” ብለዋል።