በውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ትኩረታችን ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን ዳሰናል።
👉 የውድድር ዘመኑ ፍፃሜውን አግኝቷል
በታህሳስ 3 ቀን 2013 ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ሀ ብሎ የጀመረው የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግንቦት 20 ቀን 2013 ሀዲያ ሆሳዕና ከጅማ አባ ጅፋር ባደረጉት ጨዋታ ፍፃሜውን አግኝቷል።
አንድ መቶ ሃምሳ ስድስት ጨዋታዎችን ያስተናገደው ውድድር የስያሜ መብቱን ቤትኪንግ ለተባለው አወራራጅ ተቋም የቴሌቪዥን ስርጭት መብቱን ደግሞ ለዲኤስቲቪ መሰጠቱ ከወትሮው የውድድር ዘመናት ለየት ያለ ገፅታን አላብሰውታል።
ከቀደሙት ዓመታት በተለየ በአምስት የተመረጡ ከተሞች (አዲስአበባ ፣ ጅማ ፣ ባህር ዳር ፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ) በተደረገው ውድድሩ ከመጫወቻ ሜዳዎች አመቺነት ጋር በተገናኘ መሻሻል ከሚገባቸው ጉዳዩች እና የጨዋታ ዳኝነት ክፍተቶች ውጪ ከሞላ ጎደል ስኬታማ የሚባል ጊዜ ማሳለፍ ችለናል።
በውድድሩም ፋሲል ከነማ ከሌሎች ቡድኖች እጅጉን የተሻለ ሆኖ ከተከታዩ በሁለት አሀዝ የነጥብ ልዩነት በመራቅ አሸናፊ መሆን ሲችል ደካማ የውድድር ዘመን ያሳለፉት አዳማ ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከሊጉ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።
👉 የአቡበከር ናስር ቤተሰብ…
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን የተረከበው የአቡበከር ናስር ቤተሰቦች ቡድኑ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በመገኘት ታድመዋል።
ወላጅ አባት እና አናቱን ጨምሮ እህቱ እንዲሁም ሁለቱ እግርኳስ ተጫዋች ወንድሞቹ (ሬድዋን እና ጂብሪል) በድንገት በስታዲየሙ ታድመዋል። ከጨዋታው ቀደም ብሎ የቤተሰቡ አባላት ሜዳ ላይ ተገኝተው ለአቡበከር ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና የቡድን አባላት ጋር ደስታቸውን የተጋሩበት እና በጋራ ፎቶ የተነሱበት ሂደት ልዩ ክስተት ነበር።
ከአቡበከር ናስር ጋር በተያያዘ አንድ ታዳጊ የተጫዋቹን ስዕል በስታዲየም ያበረከተበት ክስተት ትኩረት የሚስብ ነበር። ታዳጊው ያብስራ ዳንኤል ይባላል። ነዋሪነቱ በሀዋሳ የሆነው ታዳጊው ለአቡበከር ያለውን ፍቅር ለመግለፅ ተጫዋቹን በመሳል ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንባ ባዘለ ደስታ አበርክቶለታል፡፡
👉 በርከት ያሉ ታዳሚያን ወደ ሜዳ መግባት
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ከሁለት ሺህ ሦስት መቶ በላይ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ ፍቃድ ማግኘታቸው ይታወሳል። ነገርግን በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በወል የማይታወቅ በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ጨዋታዎችን ሲከታተል ተመልክተናል።
የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ መዘናጋት በርካታ ቁጥር ያላቸው የእግርኳስ ተመልካቾች በበር በኩል እያለፉ በሩጫ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተደጋጋሚ መታዘብም ችለናል። በተመሳሳይ ከስታዲየሙ በቅርበት በሚገኝ ዛፍ ላይ ሆነውም ጨዋታ ሲመለከቱ የተስተዋሉ ጥቂት ደጋፊዎች የነበሩበት ሳምንት ነበር።
👉የሴንትራል ሆቴል ሽልማት
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና አማካዩ ፍፁም ዓለሙ ሽልማት በማበርከት የጀመረው የሀዋሳው ሴንትራል ሆቴል ባለቤት የእውቅና መርሐግብር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ ቀጥሏል።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተደረጉ ሁሉም ጨዋታዎች መጀመር አስቀድሞ በየክለቦቹ መልካም ውድድር ላሳለፉ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የሆቴሉ ባለቤት በግላቸው ያሰሯቸውን የማበረታቻ ሽልማቶች አበርክተዋል።