አቡበከር ናስር ስለ ቀጣይ ዓመት ቆይታው ፍንጭ ሰጠ

በስካይ ላይት ሆቴል ምሸቱን በተካሄደው የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ልዩ ሽልማት የተበረከተለት ኮከቡ አቡበከር ናስር በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ ቡና እንደሚቆይ ፍንጭ ሰጥቷል።

በ2013 የውድድር ዘመን አብዛኛዎችን የክብር ሽልማት ጠቅልሎ የወሰደው አቡበከር ናስር በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው የዕውቅና ሥነ ስርዓት ላይ ኮከብ ተጫዋች ልዩ ዋንጫ እና አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሱዙኪ 2021 ሞዴል መኪና መሸለሙ ይታወቃል። በሽልማቱ ወቅት የተሰማውን ስሜት የገለፀው አቡበከር በቀጣይ ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የመቆየት ፍላጎት እንዳለው እንዲህ በማለት ገልጿል።

” ይህ ዓመት ለኔ የተለየ ስኬታማ ዓመት ነው። ይህ ስኬት እንዲመዘገብ የቡድን አጋሮቼ፣ የአስልጣኞች አባላት እና የክለቡ አመራሮች ላደረጉልኝ እገዛ አመሰግናለሁ። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም ሁሌም ከጎኔ በመሆናቸው አመሰግናለሁ። እንዲሁም በ2009 የነበሩ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን አባላት በሙሉ አመሰግናለው። ከቡድን አጋሮቼ መካከል በተለይ ለእኔ እንደ ወንድሜ የማየው ኢያሱ ታምሩ ሁሌም ስለሚመክረኝ እና ከጎኔ የነበረ በመሆኑ እጅግ በጣም አመሰግነዋለሁ። ስለ እርሱ መልካምነት ተናግሬ አልጨርስም።

” ይህ የዛሬው ሽልማት ያልጠበቅኹት ነው። በጣም ደስ ብሎኛል። በቀጣይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከዘንድሮ በተሻለ ጊዜ በማሳለፍ ዋንጫ ማሳካት ስለምፈልግ በቀጣይ ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ውጭ የትም አልሄድም።”

ያጋሩ