መከላከያ ስፖርት ክለብ ሲምፖዚም አካሂዷል

መከላከያ ስፖርት ክለብ “ከየት እሰከ የት” በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም አካሂዷል።

የመከላከያ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ገዘፍ ያለ ታሪክ አላቸው ከሚባሉ ክለቦች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከተመሰረተ 79 ዓመት ያስቆጠረውና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል በሀገሪቱ በርካታ ዋንጫዎችን ያሸነፈው ክለቡ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ሲወዳደር ቆይቶ በ2011 ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዱ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ወደ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሱን ያረጋገጠው ክለቡ ከእግርኳስ በተጨማሪ በበርካታ የስፖርት ዘርፎች ከፍተኛ በጀት መድቦ በመንቀሳቀስ የሚታወቅ እንደመሆኑ በሚያወጣው ገንዘብ ልክ በቀጣይ በተሻለ እና ላቅ ባለ ደረጃ ስኬታማ ይሆን ዘንድ “መከላከያ ከየት እስከ የት” በሚል ርዕስ በሸራተን አዲስ በትናንትናው ዕለት ከረፋድ እስከ አመሻሽ ከቀደመ እስከአሁን ጥንካሬና ድክመቱን እና ቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ ውይይቶች እና ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታ እና የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ ፍስሐ ወልደሰንበት ፣ ከፍተኛ የክለቡ አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የፌዴሬሽን ተወካዮች እና በርከት ያሉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ አስቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር እና የክለብ ላይሰንሲንግ ኃላፊው አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የመከላከያን እግርኳስ ታሪክ ከአጀማመሩ አሁን እስካለበት ቁመና ድረስ፣ የነበሩትን ውጣ ውረዶች፣ ድክመት እና ጥንካሬውን እንዲሁም በቀጣይ ውጤታማ መሆን የሚችሉበትን መንገዶች በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በመቀጠል አቶ ቢልልኝ መቆያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌድሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ በክለቡ መዋቅራዊ ለውጥ አስፈላጊነት ዙርያ ዝርዝር ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ዘላለም መልካሙ (ዶ/ር) ደግሞ በአትሌቲክሱ ዙርያ ጥናታቸውን አቅርበዋል።

ጥንታዊ ፅሁፉን በሁለተኝነት ያቀረቡት አቶ ቢልልኝ መቆያ የክለቡ የመጠሪያ ስያሜ ዙርያ በአንክሮ ገለፃን አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው መከላከያ ስፖርት ክለብ የሚለው ስያሜ ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ተግባርና ግዳጅ አፈፃፀም ጋር እየተጋጨ በመሆኑ እና ክለቡ በስፖርቱ ሲሸነፍ ሠራዊቱ ተሸነፈ የሚለው ጋር እየተጋጨ በህዝቡ ዘንድ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በስፋት ወደ ሚታወቅበት “መቻል ስፖርት ክለብ” ወደሚለው ቢመለስ የሚል ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበት ታዳሚውን ማስማማቱ ታውቋል፡፡

በመጨረሻም ያለፉትን አምስት ዓመታት የውጤት መዋዠቅ እየታየበትና ወጣ ገባ አቋም እያሳየ በመሆኑ በተለይ እግር ኳሱ ላይ ጠንከር ያሉ የመፍትሔ ሥራዎች የተባሉ ሀሳቦች ቀርበው ክለቡ በውጤት የታጀቡ ጉዞዎች እንዲኖሩት ዕቅድ የቀረበ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለመለወጥ ክለቡ ቆርጦ እንደተነሳ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ደሱ ታደሰ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም በተመሳሳይ የክለቡ የበላይ አካላት በ2014 ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ውይይት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

የአስራ አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮኑ መከላከያ ስፖርት ክለብ በ1990ዎቹ መጀመርያ በዚህ መጠርያ በአዲስ መልክ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ ጦር ሠራዊት፣ መቻል፣ ምድር ጦር እና ሌሎች ስያሜዎች ሲጠራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን የስያሜ ምክረሀሳቡ ከፀደቀ ከ1948 ጀምሮ እስከ ሰባዎቹ መጨረሻ ድረስ ሲጠቀምበት ወደነበረው ዝነኛ ስሙ “መቻል” የሚመለስ ይሆናል።