የአአ ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር የዛሬ ውሎ

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ሦስተኛ የጨዋታ ቀን መድን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ጠዋት ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ መድን እና መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ በመድን አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክር ባስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወደ ጎል በመድረስ እና ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የተሻሉ የነበሩት መድኖች የነበሩ ቢሆንም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት መከላከያዎች ናቸው። በ27ኛው ደቂቃ ከርቀት የቡድኑ አንበል አሸናፊ አበራ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ መከላከያዎች መምራት ችለው ነበር። 

ጎሉ ይቆጠርባቸው እንጂ በእንቅስቃሴ ሆነ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ የአቻነት ጎል የፈለጉት መድኖች ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ወደ ፊት በመሄድ ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ በሚገር መሁኔታ ተረጋግቶ ዮናታን እሸቱ ኳሱን በግብጠባቂው አናት ላይ ቺፕ በማድረግ በ36ኛው ደቂቃ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በአቻ ውጤት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ ከእረፍት ሲመለሱ የውድድሩን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በ30 ጎል እየመራ የሚገኘው እና የወደፊቱ ትልቅ አጥቂ መሆኑን እያስመለከተን የሚገኛው ድሬዳዋ ተወልዶ ያደገው ሳላዲን አብደላ አላስፈላጊ የሆነ ንትርክ ከዕለቱ ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ጋር በመግባቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሳላዲን ገና ወደ ፊት ብዙ የሚጠበቅበት ወጣት ታዳጊ ተጫዋች እንደመሆኑ መጠን እና ወደፊት ራሱን እያሻሻለ ትልቅ ተጫዋች እንዲሆን አላስፈላጊ ከሆኑ ወጣ ያሉ ባህሪዎቹን ከወዲሁ እንዲያስተካከል የአሰልጣኙ ከፍተኛ ክትትል ያስፈልገዋል።

ይህ ድርጊት ከተፈፀመ በኃላ በቁጥር ማነሳቸው ምንም ጫና ያላሳደረባቸው በአሰልጣኝ መስፍን አህመድ (ጢቃሶ) የሚመሩት መድኖች ቁልፍ አጥቂያቸው ከወጣ ከአራት ደቂቃ በኃላ በ60ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ልዩነት መፍጠር የቻለው እስማኤል ረሽድ የመጀመርያ ጎል ባስቆጠሩበት መንገድ የግብጠባቂውን አቅጣጫ በማሳት ጎል በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። ጨዋታውን ተቆጣጥረው መጫወት የቀጠሉት መድኖች ሌላ ተጫዋቻቸው በቀይ ካርድ ዳግም መውጣቱ ጫና እንዲደርስባቸው አድርጓል።

የመከላከያው ተከላካይ ቃልዓብ ብርሐኑ እና የመድኑ አማካይ ዳዊት አውላቸው ከኳስ ውጭ በፈጠሩት ጉሽሚያ ሁለቱም በቀይ ካርደ ከሜዳ እንዲወጡ ተደርጓል። በኢትዮጵያ መድን የእስካሁን ጉዞ ውስጥ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑት ሳላዲን እና ዳዊት በቀይ ካርድ ቀጣይ ጨዋታ የሚያልፋቸው መሆኑ በራሳቸውም ሆነ በቡድኑ ላይ ተፅእኖ እንዳያደርጉ ተሰግቷል።

ሁለት ተጫዋች በቀይ ካርድ ማጣታቸውን ተከትሎ በቀሪው ደቂቃዎች በጥንቃቄ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መከላከል ላይ የተጠመዱት መድኖች መከላከል ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 2–1 አሸንፈው ወጥተዋል። ውጤቱን ተከትሎ መድኖች በቀጣይ ጨዋታ አዳማ ከተማ ነጥብ ጥሎ እነርሱ አሸናፊ መሆን ከቻሉ ውድድሩን አንድ ጨዋታ እየቀራቸው አሸናፊ በመሆን የሚያጠናቅቁ ይሆናል።

በማስከተል አምስት ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር አሳይቶ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ለምን አሸናፊነት ተጠናቋል። በርከት ያሉ ተመልካቹች በታደሙበት በዚህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናው ዋና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከቡድን መሪው ጋር በመገኘት ጨዋታውን ተከታትለዋል።

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ደግፌ የቡድኑን ቁልፍ አራት ተጫዋቾችን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ማስቀመጣቸው በዛሬው ሽንፈት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በኤልፓዎች በኩል አብዱልከሪም ማሙሽ እና ፍቃዱ ለማ ከሚፈጥሩት ጥሩ እንቅስቃሴ ባሻገር የቡናን አጨዋወት በመቆጣጠር አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መዝለቅ ችለው ነበር። ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች በተገኙት አጋጣሚዎች ወደ ጎል በመድረስ በሚፈጥሩት አደጋ በ36ኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም የቡናው መስመር አጥቂ ሀምዛ ሱልጣን ቢመታውም የኤልፓ ግብጠባቂ አብዱልላኪፍ ሬድዋን አድኖበታል። ይህን ፍፁም ቅጣት ምት ቡናዎች ካመከኑ በኃላ ሌላ ጎል መሆን የሚችል ግልፅ እድል ወንድማገኝ መላኩ መፍጠር ቢችልም ግብጠባቂው በአስደናቂ ሁኔታ አድኖበታል።

የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኃላ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋቾች ከተጠባባቂ ወንበር በማስነሳት ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ብልጫ በመውሰድ ሀምዛ ሱልጣን ከቀኝ ጠርዝ ተጫዋቾችን በመቀነስ ለአላምዱ ነጋሽ አቀብሎት ራሱ መጠቀም ሲችል ተቀይሩ ለገባው ዮሐንስ ሙራድ አቀብሎት ተከላካዮች ተደርበው እንደምንም ያወጡት ኳስ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር። ኤልፓዎች ብልጫ በተወሰደባቸው አገጣሚ በ54ኛ ደቂቃ ያገኙትን ማዕዘን ምት ተጠቅመው በአሸነፊ አበራ የግንባር ኳስ መምራት ችለዋል። ጨዋታውን የበለጠ መቆጣጠር የሚችሉበትን ዕድል በኤልፓዎች በኩል በፍቃዱ ለማ አማካኝነት ግልፅ የጎል አጋጣሚ ቢፈጥሩም ለጥቂት በግቡ አናት ወጥቶባቸዋል።

ቡናዎች በኩል ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በተደጋጋሚ ወደ ጎል ቢደርሱም የኤልፓን የመከላከል ጥንካሬን ሰብረው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል። ይልቁንም ከመስመር እየተነሳ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ወንድማገኝ ከቀኝ መስመር ተነስቶ ተጫዋች እያለፈ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ ግሩም ምት መቶ የግቡ አግዳሚ ታኮ የወጣው ቡናን አቻ ማድረግ የሚችል ነበር። በሙሉ አቅማቸው ሲከላከሉ የቆዩት ኤልፓዎች ጥረታቸው ተሳክቶ ጨዋታውን አሸንፈው ሲወጡ ቡናዎች በአንፃሩ ከዋንጫው ፉክክር ውጭ መሆን ችለዋል። በኤልፓ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው አብዱልከሪም ማሙሽ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን ተመልክተናል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሰባት ሰዓት አዳማን ከዲኤፍቲ ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ የበላይነት 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። እጅግ የተሟላ ቡድን መሆናቸውን ያስመለከቱን አዳማዎች ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ገና ከ12ኛው ደቂቃ ጀምሮ ነበር። ጎሉንም የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየተፎካከረ የሚገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ሲያስቆጥር ጎሉንም ካስቆጠረ በኃላ ዋና አሰልጣኙ እና ምክትል አሰልጣኙን በአንድ ላይ እጅ ወደ ላይ አድርጎ አክብሮቱን የገለፀበት መንገድ አስገራሚ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ አዳማዎች በአጥቂያቸው ሰይፈዲን ረሺድ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ለዚህ ጎል መቆጠር ዮሴፍ ታረቀኝ ኳሱን ያቀበለበት መንገድ ልዩ ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች በ27ኛው ደቂቃ በልማደኛው አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ማስገኘት ችሏል። ዮሴፍ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረውን ጎል 23 ማድረስም ችሏል። ከአጥቂ ጀርባ የሚጫወተው ዮሴፍ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል እና ጎል በማስቆጠር ረገድ አቅሙን እያሳያሳየ የሚገኝ ሲሆን ወደፊትም ትልቅ ተጫዋች እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ነው።

ከመጀመርያው ደካማ እንቅስቃሴያቸው ተሽለው የቀረቡት ዲኤፍቲዎች በ68ኛው ደቂቃ በዳዊት ሽፈራው አማካኝነት ጎል አስቆጥረው አዳማዎችን ውጥረት ውስጥ ቢከቱም አዳማዎች በፈታ ሰፋ የ76ኛው ደቂቃ አራተኛ ጎል ጨዋታውን መልሰው እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። ፈታ ሰፋ ጎሉን ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ አስገራሚ እና የግል ችሎታውን የተመለከትንበት ነበር። ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል በመጨረሻው ደቂቃ አልሐምዱ ሙሐጅር ለዲኤፍቲ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ 4–2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዳሜ ግንቦት 28 ቀን

03:00 | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ
05:00 | ዲኤፍቲ ከ ኢትዮጵያ መድን
07:00 | አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

* ጨዋታዎቹ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳሉ