የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ በ2013 ክለቡን ውጤታማ ላደረጉ ስፖርተኞች በሁለቱም ፆታ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በኃይሌ ሪዞርት በነበረው የእራት ግብዣ ለክለቡ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች እና ሌሎች አባላት የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በሥነ ስርአቱ ላይ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ምክትል ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሚልኪያስ ብትሬ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት አካላት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡቴሳ ኡጋሞ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፕሮግራሙ ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን በመቀጠል የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሚልኪያስ ብትሬ በክለቡ እየታየ ያለው ሥራ አመርቂ መሆኑን ጠቁመው ሀዋሳ ከተማን በስፖርቱ ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመቀጥል የዕለቱ የክብር እንግዳ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ “ከተማችን ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ትልቁን ቦታ ይወስዳል። በቀጣይ በስፖርቱ ላይ በደንብ ብንሰራ የተሻለ መድረስ ይቻላል። ከደገፍናችሁ ከረዳናችሁ የማይደረስበት ቦታ የለም። ይህ ታሪካዊ ቡድን እንደመሆኑ በቀጣይ በተሻለ ውጤት ላይ እንዲገኝ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል። ለሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ካሰብን የተወሰነውን ከዚህ ክለብ ማግኘት እንችላለን። በ2013 ለነበረው ትልቅ ትግል የከተማ አስተዳደሩ ምስጋናውን እያቀረበ በ2014 የተሳካ የውድድር ዓመት እንዲኖረን እመኛለሁ።” ብለዋል፡፡
ከከንቲባው ንግግር በመቀጠል የሽልማት መርሀ ግብር የተከናወነ ሲሆን ለክለቡ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የሰርተፍኬት ስጦታ ቀጥሎም በዓመቱ በክለቡ ኮከብ ለተባሉ ተጫዋቾች ሽልማት በተለየ መልኩ ተበርክቷል፡፡ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ጨምሮ መስፍን ታፈሰ፣ ብሩክ በየነ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ምኞት ደበበ እና ላውረንስ ላርቴ በፕሪምየር ሊጉ ላሳዩት እንቅስቃሴ በልዩ ሁኔታ ከ10 እስከ 40 ሺህ ብር ሲሸለሙ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሆኖ ለጨረሰው ቡድን አሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ ከተጫዋች ሳራ ኪዶ፣ መሳይ ተመስገን እና ትዝታ ኃይለ ሚካኤል ከ10 እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ ተሸልመዋል፡፡ ለሌሎች የቡድን አባላት ከአምስት እርከ አስር ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል።
ከእነኚህ ሽልማቶች በዘለለ ለሁለቱም ላሉ ቡድን መሪዎች፣ ምክትል አሰልጣኞች፣ ወጌሻዎች እና የቡድን አባላት በአጠቃላይ ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡