የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የአዲስአበባ ስታዲየምን ለማሳደስ እና ኢንተርናሽናል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ያወጣው ጨረታ መከፈቱድ አስታውቋል።
ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ይህንን ይመስላል:-
የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየምን ዘመናዊ ለማድረግ አማካሪ ድርጅት ለይቶ አጠቃላይ የስታዲየሙን ዲዛይን ማስጠናቱ ይታወቃል። በተሰራው ዲዛይን መሰረት በቅድሚያ ካፍ በሰጣቸው አስተያየቶች መሠረት እድሳት ለማድረግ ለግንባታ ተቋራጮች ጨረታ አውጥቷል። እድሳቱ በዋናነት የመጫወቻ ሜዳው፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የተመልካች መፀዳጃ እና የኤሌክትሪክ እና የሳኒተሪ ሥራዎችን የሚያካትት ይሆናል።
በጨረታው 8 ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3 ድርጅቶች ቴክኒካል ግምገማውን ማለፋቸውን ተከትሎ ፋይናንሻል ጨረታው በዛሬው ዕለት ተከፍቷል። በቀረበው ፋይናንሻል ሰነድ መሠረት ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ ኃ.የተ. የግል ኩባንያ 34,644,748.93 ብር እድሳቱን ለማከናወን ያቀረበው ዋጋ ሲሆን፤ በሬቻ ፊጣ ህንፃ ሥራ ተቋራጭ 50,336,995.69 ብር እንዲሁም ቢ ጂ ኤም ኮንስትራክሽን 54,929,226.43 ብር ዋጋ አቅርቧል። በዚሁ መሠረት የእያንዳንዱ ድርጅት ያቀረቡት የዋጋ ግምቶች የሂሳብ ስህተት መኖሩ እና አለመኖሩን በአማካሪ ድርጅቱ ተፈትሾ ከተረጋገጠ በኃላ ዝቅተኛ ዋጋ ካቀረበው ድርጅት ጋር ውል በመዋዋል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል።
የእድሳት ሥራው በተሰራው ዲዛይን መሰረት የሚቀጥል ሲሆን የሚዲያ ክፍሎች ፣ የክብር ትሪቡን መቀመጫ ፣ የወንበር ገጠማ እና ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎችን የማደስ እና ለአገልግሎት ምቹ እንደሚደረግ በኮሚሽኑ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው ገልፀዋል ።